ሱዳን ለምን የኢትዮጵያን የስምምነት ሃሳብ ተቃወመች?

የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሱዳን የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያቀረበችው አዲስ የስምምነት ሃሳብ የሚቀሩት ነገሮች አሉ በማለት እንዳልተቀበለችው ተሰምቷል።

በዚህ የስምምነት ሃሳብ ላይ ግብጽም አለመስማማቷ የተገለፀ ሲሆን፤ ከአሜሪካ ጋር በአቋም በመመሳሰል በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ስምምነት ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት እንደሌለባት ቀደም ሲል የተደረጉ ስምምነቶችን በመጥቀስ አቋሟን ገልጻለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ በዕቅድ የያዘችውን ግድቡን በውሃ የመሙላት ተግባር ከሁለት ወራት በኋላ እንደምትጀምር አስታውቃለች።

ለመሆኑ ሦስቱ አገራት 2008 ዓ. ም ላይ የፈረሙት የመርሆች ስምምነት ኢትዮጵያ ግድቡን መሙላት በመጀመር በኩል ሊፈጥር የሚችለው እንቅፋት እንዳለ የምሥራቅ ናይል አካባቢ ቀጠናዊ የቴክኒክ ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑትን ለአቶ ፈቅ አህመድን ጠይቀናል።

እርሳቸውም ይህ ስምምነት "ኢትዮጵያ ያለሌሎች አገራት ስምምነት ግድቡን ውሃ መሙላት እንዳትጀምር የሚል ግዴታ አይጥልባትም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ እንዳትሞላ የሚከለክላት የገባችውም ግዴታ እንደሌለና የኢትዮጵያ መንግሥት የታላቁን የሕዳሴ ግድብ በእቅዱ መሠረት ውሃ መሙላት እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

በአባይ ጉዳይ ዙሪያ በርካታ ምርምሮችን ያካሄዱት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖም በ2008 ተፈርሞ የነበረው የጋራ አቋም መግለጫ ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ ከመሙላት እንደማያግዳት ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያን ሃሳብ አልቀበልም ያለችው ሱዳን ከሳምንታት በፊት የአረብ ሊግ አገራት የግብጽን ፍላጎት በሚያስጠብቅ መልኩ የአቋም መግለጫ ባወጡበት ወቅት መግለጫውን ተቃውማ እራሷን አግልላ ነበር።

ሱዳን በህዳሴ ግድብ የምታገኘው ጥቅም በርካታ እንደሆነ በዝርዝር የሚጠቅሱት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፤ "አንደኛ ጎርፍ ለመቆጣጠር፣ ሁለተኛ ደለልን በመቀነስ፣ ሦስተኛ የተረጋጋ ውሃ ዓመቱን ሙሉ አግኝታ ሠፊ መሬቷን በመስኖ ማረስ በመቻል፣ አራተኛ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል የምታገኝበትን ዕድል ይፈጥርላታል" ይላሉ።

ስለዚህም ነው ሱዳን በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ ግድብ በተለያዩ አጋጣሚዎች ስትደግፍ የቆየችው። ቢሆንም ግን ዋሽንግተን ላይ በተደረጉት ድርድሮች ወቅት አንዳንድ ጊዜ ወደ ግብጽ የሚያዘነብሉ አቋሞችን ታንጸባርቅ እንደነበረ ሲነገር ቆይቷል። አሁን ግን በይፋ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ላይ ተቃውሞዋን አቅርባለች ለምን?

እንደ ዶክተር ያዕቆብም ሆነ አቶ ፈቅ አህመድ ሱዳን ከተጽዕኖ ነጻ አገር ልትሆን አትችልም። በተለይ የሱዳን መንግሥት አዲስ መሆኑና ገና መሰረቱ ያልፀና መሆኑ ለተጽዕኖ በቀላሉ እጅ እንዲሰጥ ያደርገዋል ባይ ናቸው።

"ብዙ ተጽዕኖ ስላለባት ሊሆን ይችላል። የሱዳን መንግሥት አዲስ ነው ከተለያዩ ኃይሎች ጋር በመሆን በጥምረት የተመሰረተ አስተዳደር ነው። የሚገላምጣቸው ብዙ ነው። አሜሪካም የጣለችውን ማዕቀብ ላንሳ አላንሳ እያለች ነው" ይላሉ ዶ/ር ያዕቆብ።

አክለውም "ታዲያ ከዚህ ሁሉ የተነሳ ሱዳን ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ አናውቅም" በማለት በዚህ ምክንያት የተነሳ አቋሟን ቀይራ ሊሆን ይችላል ይላሉ።

አቶ ፈቅ አህመድም ይህንኑ ሃሳብ ካረጋገጡ በኋላ "አዲሱ የሱዳን መንግሥት መሠረቱ ወደ ውስጥ በደንብ ዘልቆ ስላልገባ ማንንም ማስከፋት አይፈልግም። ሌላው ደግሞ በዚህ ዘርፍ ላይ የነበሩና ቀድሞ ከኢትዮጵያ ጋር ሲሰሩ የነበሩ ከፍተኛ ባለሙያዎች አሁን በቦታቸው ላይ የሉም" ይላሉ።

"ያሉት ሹማምንት አዳዲስ መሆናቸው የሱዳን ባለስልጣናት በቂ መረጃ እንዳይኖራቸው ሳያደርጋቸው አልቀረም" በማለት ሱዳን ከውጪ ከሚደረግባት ጫና በተጨማሪ የተካሄደው የመንግሥት ለውጥ የፈጠረው ክፍተት እንዳለ አመልክተዋል።

አሜሪካ እና ግብጽ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ውሃ መሙላት የለባትም ብለዋል። ሱዳን በበኩሏ ኢትዮጵያ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያቀረበችውን አዲስ የስምምነት ሃሳብ አልቀልም ብላለች። ኢትዮጵያ ደግሞ በያዘቸው ዕቅድ መሰረት ግድቡን ውሃ መሙላት እጀምራለሁ ብላለች። ታዲያ መጪው ጊዜ ምን ይዟል?

አቶ ፈቅ አህመድ አሜሪካ በዚህ ድርድር ውስጥ ስትሳተፍ መጀመሪያውኑ የገንዘብ ሚኒስትሯን መመደቧ ስለጉዳዩ ስለማይመለከታቸው፣ በቂ ልምድና እውቀት ስለሌላቸው ተገቢ አልነበሩም ይላሉ።

"ምናልባት የፖለቲካ ጫና ሊኖር ይችላል" የሚሉት አቶ ፈቅ "ከዚያ ውጪ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ታበላሻለች ብዬ አላስብም" ብለዋል።

ዶ/ር ያዕቆብ ደግሞ "ግድቡ ውሃ መያዝ ሲጀምር ማንም መሸበር ያለበት አይመስለኝም" ይላሉ። "ጦርነትና ግጭት ሊፈጠራል ይችላል የሚሉ አካላትንም የተሳሳተ ግምት ነው" በማለት "ይህ ከሆነም በውሃ ምክንያት ወደ ግጭት በመግባት የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን" ይላሉ።

አገራቱን በማሸማገል ባለፉት ወራት ወደ ጉዳዩ የገባችው አሜሪካ ሲካሄደው የነበረው ድርድር መልሶ እንዲጀመርና ስምምነት ላይ እንዲደረስ እየወተወተች ትገኛለች።