የሕዳሴ ግድብ ድርድር የት ደረሰ?

የፎቶው ባለመብት, GRAND ETHIOPIAN RENAISSANCE DAM
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ሊጀመር ጥቂት ቀናት ቀርተውታል። ቢሆንም ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በግደቡ ሙሊትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት አልደረሱም።
ሃገራቱ ድርድራቸውን ባለፈው ሳምንት በቪድዮ ኮንፈረንስ አማካይነት እንደ አዲስ ጀምረው ነበር። ነገር ግን ስምምነት ላይ ባለመድረሳቸው ምክንያት ረቡዕ ዕለት ድርድሩ እንዲቋረጥ ሆኗል።
ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት አትቀበልም ብለዋል።
ሶስቱ ሃገራት በግድቡ የውሃ አሞላል ያደረጉት ድርድር በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ወደ ስምምነት እንዲቃረቡ ቢያደርጋቸውም፤ ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ግን ልዩነቶች ተንፀባርቀዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታደርገው ድርድር ግድቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች እንጂ በቀጣይ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ የመልማት መብቷን አያካትትም ብለዋል። ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገውን ድርድር በማስታከክ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የሚኖራትን መብት ለመገደብ እየሞከረች መሆኗንም አስረድተዋል።
ግብፅ ከመጨረሻው ዙር ድርድር አፈንግጣ ወጥታለች የሚሉት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስምምነቱ የወንዙን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ማዕከል ያደረገ ነው ብለዋል።
ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ድርድር ግድቡን ብቻ እንደሚመለከትና ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌላ ግድብ የመገንባትም ይሁን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወንዙን የመጠቀም መብቷን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አቶ ገዱ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን ምንም ዓይነት ውጫዊም ይሁን ውስጣዊ ችግር ግድቡን ውሃ ከመሙላት እንደማያግዳት አቶ ገዱ አሳስበዋል።
ግብፅ
የግብፁ ፕሬዝደንት አብልድ ፋታህ አል-ሲሲ ሃገራቸው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አለመግባባት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነች ሲሉ ተደምጠዋል።
የግድቡ ሙሌት ሊጀመር የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። ግብፅ ባለፈው አርብ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ጥያቄ ማቅረቧ አይዘነጋም።
ሲሲ እኛ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ማምራት የፈልገነው ጉዳዩን እስከ መጨረሻው ድረስ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ስለምንሻ ነው ማለታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
አልፎም ስምምነት ላይ መድረስ ይገባናል፤ የሁሉንም ጥቅም የሚያስከብር መፍትሄም ያስፈልገናል ብለዋል።
የግብፁ ፕሬዝደንት ይህንን ንግግር ያሰሙት በሃገሪቱ አየር ኃይል ተቋም ውስጥ ነው። ሲሲ የሃገሪቱ ሠራዊት ሃገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ወታደራዊ እርምጃዎችን ለመውሰድ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርበዋል።
ብዙዎች ሲሲ ከወታደራዊ ኃይላቸው ጋር መታየታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ፍጥጫ ያጦዘዋል ቢሉም የአረቡ ዓለም ሚድያዎች ግን ግብፅ፤ ሊቢያ ውስጥ ከቱርክ ኃይሎች ጋር ፍጥጫ ውስጥ ትገኛለች በማለት እየዘገቡ ነው።
ሱዳን
ሱዳን በበኩሏ ግብጽ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በድርድር ሂደት ላይ እያለ ጉዳዩን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ ውጥረቱን እንደሚያጦዘው አስታውቃለች።
የሱዳን መስኖና ውሃ ሚኒስትር ያሲር አባስ "እኛ ውጥረት አንፈልግም፤ ስምምነት እንጂ" ብለዋል ሲል የዘገበው አህራም ኦንላይን የተሰኘው ሚድያ ነው።
ሱዳን ግድቡ ከመሞላቱ በፊት ስምምነት ላይ እንዲደረስ እንደምትፈልግ ሚኒስትሩ ተናግረዋል ሲል የዜና ምንጩ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የመጀመሪያ የውሃ ሙሌትን በሚቀጥለው ወር ለመጀመር የማንም ፈቃድ እንደማያስፈልጋት ማስታወቋ አይዘነጋም።
በሌላ በኩል የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናንት ጀኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ጎብኝተው መመለሳቸው አይዘነጋም።
ጄኔራሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር በተለያዩ የመሠረተ ልማት ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ቢዘግቡም በሕዳሴ ግብድ ዙሪያ ውይይት ስለመደረግ አለመደረጉ የተባለ ነገር የለም።

















