ልንቀበላቸው የማንችላቸውን ነገሮች እንድንቀበል ግፊት ሲደረግ ነበር ፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

ኢትዮጵያ እገነባችው ባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ለዓመታት ሲደረግ የነበረው ድርድር እስካሁን መቋጫ ሳያገኝ ቆይቷል። ተስፋ ተጥሎበት የነበረውና አሜሪካና የዓለም ባንክን ያካተተው ድርድር ታሰበውን ውጤት ሳያሳካ በመጨረሻው ላይ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚነካ ነው ያለችውን ሰነድ ሳትፈርም በእንትልጥል ቀርቷል።

ይህ ዋሽንግተን ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ድርድር ግብጽን የሚደግፍ ኢትዮጵያ ላይ ደግሞ ጫናን የሚያሳድር እንደነበረ በስፋት ሲነገር ቆይቷል። በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ሲካሄድ ስለቆየው ድርድር የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙርያ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ውይይቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውይታወቃል። እነዚህ ውይይቶች ምን ደረጃ ላይ ነው ያሉት?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸውየሕዳሴ ግድብ የድርድር ሒደት አሁን ወደ መጨረሻ አካባቢ ደርሷል። ይህ የድርድር ሒደት የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ከዛሬ ዘጠኝ ዓመት አካባቢ አንስቶ የነበረ ነው። ግድቡን እንደጀመርን ግብጾችና ሱዳኖች የሚያሳስበን ጉዳይ አለ የሚል ጥያቄ በማነሳታቸው ግድቡ የታችኞቹ አገራትን የመጉዳት ምንም ዓይነት ችግር የሌለበት መሆኑን ለማስረዳት ሞክረናል።

ከዚህ አኳያ የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ይህንን እንዲያውቁትና ውይይቶች እንዲካሄዱ፣ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች ካሉ ግልፅ እንዲሆኑ፣ የሚያስፈልግ ጥንቃቄ አለ የሚሉትም ጉዳይ ካለ ለዚህ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ በጣም ግልፅ በሆነ መንገድ ነው ኢትዮጵያ አቅዳ ግድቡን የጀመረችው፤ ከዚያ እነርሱ ጥያቄ ሲያነሱም ወደ ውይይት ያመራችው።

ግድቡ እንደተጀመረ ከጥራቱ ጋር በአካባቢ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፣ አይኖረውም በሚለው ጉዳይ ላይ የግድቡን ደኅንነት በተመለከተ ጥያቄዎችን ሲያነሱ ይህንን ለማረጋገጥ ከአውሮፓ የጀርመን፣ የፈረንሳይ፣ የእንግሊዝ አንዲሁም ከአፍሪካ የደቡብ አፍሪካ፣ የግብፅ፣ የሱዳን እና የኢትዮጵያ ባለሞያዎች እንዲገምግሙት ኢትዮጵያ ዝግጁ ሆናለች።

ከዚያ በኋላ በተለያዩ ዙሮች በተለያዩ አካላት ድርድሮች ሲካሄዱ ቆይቷል። ድርድሩ አንዳንድ ጊዜ ደህና ሲሄድ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሲቋረጥ እ.ኤ.አ እስከ መስከረም 2018 ድረስ ሲከናወን ቆየና መስከረም ላይ አንድ ደረጃ ላይ ተደረሰ። ለመፈራረም ዝግጁ ሆኖ እንፈራረም ሲባል የግብጽ ተደራዳሪዎች አሁን አንፈራረምም አገራችን ሄደን መመካከር አለብን ብለው ለፊርማ የተዘጋጀን ሰነድ ትተው ሄዱ። በእርሱ ምክንያት ተቋርጦ ቆየ፤ ቀጥሎም ሱዳን ውስጥ አብዮት ተነሳ።

በኋላ እ.ኤ.አ. ኦገስት አንድ 2019 ግብጾቹ ድርድሩን ለማስቀጠል የሚያስችል ረቂቅ ሃሳብ አለን ብለው ይዘው ቀረቡ። ይህ ሃሳብ ግን ከዚያ ቀደም ከነበሩ ድርድሮች ጋር ግንኙነት ያልነበረው ነው። ኢትዮጵያ የውሃ መጠን ዋስትና ትስጠን የሚል እንዲሁም አስዋን ግድብ በሚጎድልበት ጊዜ በሚሞላበት ሁኔታ ላይ ስምምነት ላይ እንድረስ የሚሉ ተቀባይነት የሌላቸውን ሃሳቦችን ይዘው ቀረቡ።

ይሄንን ተከትሎ ኢትዮጵያም የራሷን፣ ሱዳንም የራሷን ሃሳቦች ይዘው መስከረም 2019 ድርድር ተጀመረ። በተወሰኑ ጉዳዮች ስምምነት ሲኖር፣ በተወሰኑት ላይ መፋጠጥ ሲመጣ፣ የግብጽና የኢትዮጵያ መሪዎች ሩሲያ፤ ሶቺ ውስጥ ተገናኝተው የቴክኒክ ውይይቱ እንዲቀጥል ተስማሙ።

በዚህ መኃል የአሜሪካ መንግስት ድርድራችሁን ላግዛችሁ የሚል ጥያቄ አቀረበ። እኛም ግብዣው ሲቀርብልን ወደዚያው ሄድን። የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ እያገዙ ዋነኞቹ ተደራዳሪዎች ማለትም ሦስቱ አገራት ደግሞ በነጥብ በነጥብ እየተወያዩ ብዙ ልዩነቶችን ማጥበብ ተቻለ። ወደ መጨረሻው ግን ስምምነት ላይ ሙሉ በሙሉ ሳንደርስ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እንፈራረምም የሚል ሃሳብ ይዘው ቀረቡ። ስምምነት ሳያልቅ ልዩነት ባለን ጉዳዮች ላይ እንድንፈራረም ማድረጉ ተገቢነት የለውም ብለን ነገርናቸው።

ይህ በዚህ እንዳለ ሌላ ዙር ውይይቱ ቀጠለ። አሁንም ያንኑ አቋም ያዙ። ይሄኔ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር 'እናንተ መስማማት ስላልቻላችሁ እኔ በዓለም ባንክ አጋዥነት ሁላችሁንም የሚያስማማ የስምምነት ሰነድ አዘጋጅቼ አቀርባለሁ' አሉ። 'ይህ በፍፁም አይሆንም፤ ተደረዳሪዎቹ እኛ ነን። እኛው ተደራድረን፥ ተነጋግረን መፍታት ነው ያለብን እንጂ፤ ሌላ ወገን አዘጋጅቶ በዚህ ተስማሙ ብሎ የሚሰጠን ከሆነ እኛ አንቀበለውም' አልን።

በተለይ ግብጾቹ ወዲያውኑ እንቀበለዋለን አሉ። እኛ ደግሞ እንደዚህ ያለ አሰራር መርኅን የተከተለ አይደለም። መጀመሪያ የተነሳንበትን ዓላማ የሚያሳካ አይደለም። አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ታዛቢዎች ናቸው እንጅ ፅሁፍ አዘጋጅተው ለእኛ የሚያቀርቡ አይደሉም። ሚናቸው ተቀላቅሏል፤ ድርድሩ አቅጣጫውን ስቷል። በዚህ ዓይነት አካሄድ እኛ ልንገባ አንችልም' የሚል ሃሳብ አቀረብን። በዚህ ምክንያት ድርድሩ አሁን ቆሟል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከድርድሩ ጋር በተገናኘ ከዚህ በኋላ ምንድን ነው የሚጠበቀው ?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፡ እኛ ተደራድሮ መስማማት ይቻላል ብለን እናምናለን። ለዚህ ግን ከግብጾች የሚጠበቅ አንድ ነገር አለ። ይህ ውሃ የኢትዮጵያም፣ የግብፅም፣ የሱዳንም ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚህ ውሃ የመጠቀም መብቷ የተከበረ ነው ብለው አምነው በጋራ ፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የጥቁር አባይን ውሃ ለመጠቀም ዝግጁ እስከሆኑ ድረስ ሌላ አሸማጋይም ሳያስፈልግ መስማማት ይቻላል። በሚያለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይቻላል።

ስምምነት መድረስ የማይቻለው አንዱ የሌላውን መብት ሲክድ ነው፤ በተለይ በግብጽ በኩል የቅኝ ግዛት ዘመንን ውርስ ለማስቀጠልና እ.ኤ.አ በ1959 ከሱዳን ጋር የተፈራረሙትን ኢፍትሃዊ የሆነ የውሃ ድርሻን ጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ስምምነት ለመድረስ የሚያደርጉትን ሙከራ ማቆም ይኖርባቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ከውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ጋር የተያያዙ እንዲሁም መሰል ጉዳዮች ላይ የታጠረ ንግግር አድርጎ መስማማት እስከተቻለ ድረስ በኢትዮጵያ በኩል መቼውንም ቢሆን በራችን ክፍት ነው። ሌላ አካል ረቂቅ አቅርቦልን፣ በዚያ ረቂቅ ላይ መደራደር ሳይሆን እኛው የየራሳችንን ፍላጎት በሚያንፀባርቅ መንገድ አንድ በአንድ ተነጋግረን ስምምነት ላይ መድረስ ይቻላል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

በዚህ ድርድር ላይ የአሜሪካን እና የዓለም ባንክን ተሳትፎ እንዴት ገመገማችሁት? የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ ስምምነት እንድትፈርም ጫና ለማሳደር ሞክሯል የሚሉ ዘገባዎች ወጥተው ነበርና በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ምልከታ ምን ይመስላል?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፡መጀመሪያ አካባቢ አሜሪካኖቹ በታዛቢነት በድርድሩ ተራርቀው የነበሩ አቋሞችን እያጠበብን እንድንመጣ አግዘውናል። ይሄ የሚካድ አይደለም። ነገር ግን በሒደት አሜሪካኖቹ ድርድሩ ቶሎ እንዲቋጭ ፈለጉ። ድርድሩ ቶሎ አልቆ አንድ ትልቅ ነገር እንደቋጩ አድርገው ለማየት ፈለጉ።

በእኛ በኩል ደግሞ ይሄ የአባይ ስምምነት በአሁኑ ትውልድ ብቻ ሳይሆን በመጪው ትውልድም ላይ የራሱ ተፅዕኖ የሚኖረው ስምምነት ስለሆነ በጥንቃቄ መታየት አለበት ብለን ነው የምናመነው። 'በጥድፊያ መሆን የለበትም፤ እንደገና ደግሞ በድርድሩ ሒደት ዋነኞቹ ተዋናዮች መሆን ያለብን ባለቤቶቹ ሦስቱ አገራት ነን፤ በመሆኑም የእናንተ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ በእኛ ላይ ማሳደር ፍትሃዊ የሆነ ስምምነት ላይ እንድንደርስ አያደርገንም' የሚል ነው ልዩነታችን።

መጀመሪያ አካባቢ በሄዱበት አካሄድ በሰከነ መንገድ ሦሰቱም አገራት በየራሳቸው ከሚለከታቸው አካላት ጋር እየተመካከሩ ስምምነት ላይ መድረስ የሚቻልበት ዕድል ነበረ። ነገር ግን በአቋራጭ አንዳንዶቹን በፍፁም እኛ ልንቀበላቸው የማንችላቸውን ነገሮችንም እንድንቀበል ግፊት ማድረጉ እየተጠናከረ ሲሄድ ይሄ ልክ አይደለም አልናቸው፤ እነርሱ ደግሞ መስማማት አለባችሁ የሚል አቋም ያዙ።

ወደመጨረሻ አካባቢ ሙሉው የአሜሪካ መንግሥት ብዬ ለመውሰድ ባልችልም በተለይ የገንዘብ ሚኒስትሩ (የትሬዠሪ ዲፓርትመንት ኃላፊው) ግፊታቸውን ጠንከር እያደረጉ መጡ። ይሄ ደግሞ ትክክል አይደለም፤ ተቀባይነትም የለውም።

ስለዚህ ኢትዮጵያ አሜሪካ ወይንም የዓለም ባንክ ወደ አደራደሪነት ቢመለሱ ችግር አይኖርባትም ማለት ነው?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፡ማንኛውም የሚካሄድ ድርድር በመርኅ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት የሚል እንጂ፤ ኢትዮጵያ በአደራዳሪነት ማን መጣ? ማን ሄደ አይደለም ዋናው ጉዳዩዋ። ይህ ድርድር ደግሞ ሦስቱን ባለጉዳይ የሆኑትን አገራት የሚተካ መሆን የለበትም። እንዲህ ያለ ሙከራ ጠቃሚ የሆነ ድርድር ላይ እንድንደርስ አያደርገንም። ለወደፊቱም ጠንቅ ጥሎ የሚያልፍ ድርድር ነው የሚሆነው። ሌሎች ሊያግዙን ይችላሉ፤ ሊደግፉን ይችላሉ። እኛን ሊተኩን ግን አይችሉም።

ግብጽ ዘጠና ከመቶ ገደማ የንፁህ ውሃ ፍላጎቷን የምታሟላው ከአባይ ውሃ ነው። ስለዚህ ግድቡ የውሃ ፍላጎቴ ላይ አደጋ ይጋርጣል የሚል ስጋት አላት። ይህንን ስጋቷ ተገቢ አይደለም?

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፡ግብጾች እኛ ፍትሃዊ አይደለም ያልነውን ስምምነት እንድንፈርም ይፈልጋሉ። እኛ ደግሞ የአገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ስለሆን አንፈርምም ብለናል። ይህንን መሰረት አድርገው የተለያዩ ዘመቻዎች እያካሄዱ ነው። ይህ ዘመቻ ይሳካላቸዋል፣ አይሳካላቸውም ሌላ ጉዳይ ሆኖ፤ የያዙት መንገድ ግን ትክክል አይደለም የሚል እምነት አለን።

እኛ ተደራድረን ችግሩን ማቃለል ስንችል፣ በዲፕሎማሲ ጫና፣ በተለያየ መንገድ በሚደረግ ግፊት ኢትዮጵያ የሚጎዳትን ስምምነት ትፈርማለች ብለው እያሰቡ ከሆነ ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም አልተጋፋችም። የማንንም ጥቅም አትጋፋም። ይህ ግድብ እየተገነባ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው።

በዚህ ግድብ የሚከማቸው ውሃ ከኢትዮጵያ መንጭቶ የሚከማች ነው፤ የኢትዮጵያን የራሷን ድርሻ ነው እንጂ የግብጽን ድርሻ አይደለም የምታከማቸው። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ድሃውም ሳይቀር አዋጥቶ እየተሰራ ያለ ግድብ ነው። ይህንን ግድብ በሚመለከት የሚደረግ ስምምነት የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ መልኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላ በማንኛውም ጫና፣ በማስፈራራት በመሳሰለው የማይሆን ነው።

የሚሻላቸው ከወንድሞቻቸው ጋር ተመካክሮ ጉዳዩን ለማቃለል መሞከር ነው። የኢትዮጵያ ዓላማ አባይን የግጭትና የንትርክ አጀንዳ ማድረግ አይደለም። እርሱ ያለፈና ኋላቀር በሆነ አኳኋና ሲሄዱበት የነበረው ነው። አባይ የትብብር ምንጭ እንዲሆን ነው የኢትዮጵያ ፍላጎት።

ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል ለኢትዮጵያም፣ ለሱዳንም ከፈለጉ ለግብጾችም ሊሆን የሚችል ነው። ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ለማሳደግ ደፋ ቀና እያለች ያለች አገር ናት። ብቻዋን ሳይሆን ከጎረቤቶቿ ጋር ተሳስራ ለማደግ ነው እየሰራች ያለችው። በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ አባይ የትብብር ምንጭ፣ የትብብር ወንዝ እንዲሆን ነው ፍላጎታችን። የግብጾች ብዙ ቦታ መንቀሳቀስ ብዙ ጥቅም ያለው አይመስለኝም።