ስለአዲሱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ጥቂት እንንገርዎ

የፎቶው ባለመብት, ኢንጂነር ክፍሌ
ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ተሾሙ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩትን ኢንጅነር ስመኘው በቀለን ህልፈት ተከትሎ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ኢንጂነር ኤፍሬም ወ/ኪዳን የርሳቸውን ቦታ ተክተው ላለፉት ሁለት ወራት በጊዜያዊነት ሲያገለግሉ ነበር።
በትናንትናው ዕለት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ የግድቡን የግንባታ ፕሮጀክት ለሚመሩ ግለሰቦች ኃላፊነት ሰጥተዋል።
በመሆኑም ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሾሙ ኢንጅነር ኤፍሬም ወ/ኪዳንና አቶ ፈቃዱ ከበደ ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሰሩ መመደባቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ማን ናቸው?
ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ በምንህንድስና ሙያ በተለያዩ ቦታዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
*በግቤ አንድ ፕሮጀክት ላይ በምህንድስ ሙያ ሲያገለግሉ፤ በዚያው ፕሮጀክት ላይ ከ1999 -2004 ድረስ ምክትል ስራ አስፈፃሚ በመሆን ሰርተዋል።
በኢትዮጵያ መብራት ኃይል ድርጅት የኤሌክትሮ መካኒካል ክፍል ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉም ነበር።
ኢንጂነር ክፍሌ ከ2006-2010 ድረስ በጣና በለስ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል።
በ2011 የታላቁ ህዳሴ ግድብ ከተጀመረ በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ የፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ መካኒካል ክፍል ዋና ስራ አስኪያጅ ነበሩ።
ኢንጅነር ስመኘው በቀለ የህዳሴው ግድብ ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሾሙ ኢንጅነር ክፍሌ ደግሞ ከ1000 ኪሎሜትር በላይ የሚረዝመውን ኢትዮጵያና ኬንያን የሚያገናኘውን የመብራት ኃይል ዝርጋታ ፕሮጀክት ከ2013-2014 ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲሰሩ ነበር።
ከዚያ በኋላም እስከ 2016 የኢትዮጵያ የኃይል ማመንጫ ውስጥ የፕሮግራም ኃላፊ ( Generation program officer) ሆነዋል።
የስራ አስፈፃሚው አማካሪ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ወደ ግል ስራ ተመልሰው እየሰሩ ሳለ ነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት
የትምህርት ደረጃ
ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ወለጋ ተወልደው ያደጉ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በመንዲ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በቤተል ደምቢዶሎ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
በ1984 በኤሌክትሪካል ምህንድስና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
ከዚያም በተለያዩ ቦታዎች ሲያገለግሉ ቆይተው በ1999 ለስልጠና ወደ ጀርመን አገር አቅንተው ለ15 ወራት ተጨማሪ ስልጠና ተከታትለዋል።
በ2015 ከእንግሊዝ ሳል ፎርድ ዩኒቨርሲቲ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ሁለተኛ ድግሪያቸውን ተቀብለዋል።
* ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የዘመን አቆጣጠሮች እንደ አውሮፓውያኑ ናቸው።















