በአርባ ምንጭ የሃገር ሽማግሌዎች ውድመትን ተከላከሉ

የፎቶው ባለመብት, Facebook
በጋሞ ባህል መሠረት ማንኛውም ሰላምን የሚያደፈርስ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ ረብሻ፣ ግጭት በሚኖርበት ጊዜ፤ ሁኔታውን ለማብረድና ለመፍታት የሃገር ሽማግሌዎች ያላቸው ተቀባይነት ከፍተኛ ነው።
በባህሉ መሠረት በተለይ በርካታ ሕዝብ ባለበት ቦታ፤ ሕዝብ መደማመጥ፣ መነጋገር፣ መግባባትና 'አንተም ተው፤ አንተም ተው' ማለት በማይቻልበት ቦታ ላይ የትኞቹም የባህል አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ በእድሜ የገፉ አዛውንቶች እርጥብ ሳር አሊያም ቅጠል ይዘው ከቆሙ ማንኛውም የሚደረግ እንቅስቃሴ ይቆማል።
መደማመጥና መነጋገር ይጀመራል፤ ይህም ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና ማህበረሰቡ ሰላምን የሚያረጋግጥበት አንዱ እሴት ነው።
ሳር አሊያም እርጥብ ቅጠል የሰላም ምልክት ሲሆን ሰላም ማውረድ፣ ረብሻና ብጥብጡን ማቆም የሚል ትርጓሜ አለው።
በሳምንቱ የመገባደጃ ቀናት በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካቶች ለሞት ሲዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩት ቀያቸውን ጥለው ሸሽተዋል።
ብሔር ላይ ያነጣጠሩ ናቸው በተባሉትና አሸዋ ሜዳ፣ ከታ፣ ቡራዮ አካባቢዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች የንብረት መውደምና ዝርፊያ መፈፀሙም ተገልጿል።
ድርጊቱ በርካቶችን ያስቆጣ ነበር። በዚህም በአዲስ አበባና በአርባምንጭ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በነቂስ የወጡት ወጣቶችም በአካባቢው በወገኖቻቸው ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ግድያና የደረሰው እንግልትን አውግዘዋል።
በአካባቢው የሚገኙ በኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክና በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ላይ ድንጋይ በመወርወር ስሜታቸውን የገለፁም ነበሩ።
ሁኔታው ያላማራቸው የአገር ሽማግሌዎች በጋሞ ባህል መሠረት የባሰ ጉዳት ሊደርስባቸው በነበሩት ንብረቶች ፊት ለፊት በመንበርከክና እርጥብ ሳር በመያዝ በቁጣ የገነፈሉትን ወጣቶች ከጥቃት ራሳቸውን እንዲያቅቡ አረጋግተዋል።
በአካባቢው የአገር ሽማግሌ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ሰዲቃ ስሜ፤ "የሰላማዊ ተቃውሞው ዓላማ ንብረት ማውደምና በሰው ላይ ጥቃት ማድረስ አልነበረም፤ ሙከራው እንዳለ ስናይ የባንኮቹን ጠባቂዎች በማግባባትና እርጥብ ሳር ይዘን በመንበርከክ ወጣቶቹ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አድርገናል" ይላሉ።
እኝህን የአገር ሽማግሌ ባነጋገርናቸው ሰዓት ጥቃት ሊደርስባቸው በነበሩት ባንኮች ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱን እያረጋገጡ እንደነበርም ነግረውናል።

የፎቶው ባለመብት, Facebook
በተቃውሞው ወቅት ከወጣቶቹ መካከል ነበርኩ ያለን ገነሻ ማዳ "በጋሞ የለቅሶ ባህል በጭፈራ መልክ ለሞቱት የሚያለቅሱ ነበሩ፤ በሌላ በኩል የተፈፀመው ድርጊት አግባብ አይደለም፤ ጋሞ ሰው አይገድልም፤ ቢበደል እንኳን ይቅር ይላል የሚሉ ድምፆችን በጋሞኛ ሲያሰሙ ነበር" ብሎናል።
ገነሻ እንደሚለው በዚህ ጊዜ ድንጋይ በመያዝ ንብረት ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩት ወጣቶች የሃገር ሽማግሌዎች ተንበርክከው ባደረጉት የመጨረሻ ተማጽኖ በርዷል።
በባህሉ መሠረት ይህንን ልመና የተላለፈ እርግማን ይደርስበታል ተብሎ ስለሚታመን ወጣቱ ይህንን ከመተላለፍ ተቆጥቧል።
በመሆኑም እንደተፈራው በንብረትና በሰው ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ አልፏል። አደባባይ የወጣው ሕዝብም ተቃውሞውን በሰላም ገልፆ ወደየመጣበት ተመልሷል በማለት ይናገራል።
ሌላኛው ያነጋገርናቸው የሐገር ሽማግሌ አቶ አንጀሎ አርሾ "በጋሞ ተወላጆች ላይና በሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጥቃት፣ መደፈር፣ ንብረት ማውደምና ላይ የደረሰው በደል በማውገዝ ሕዝቡ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቷል" ይላሉ።
በጋሞ የለቅሶ ባህል መሠረትም በእንብርክክ እየሄዱ በርካቶች ሃዘናቸውን ሲገልፁም አስተውለዋል።
ይሁን እንጂ ሁኔታውን ወደ ሌላ ብጥብጥ ለማሸጋገር የሚሞክሩ እንደነበሩ ያልሸሸጉት የአገር ሽማግሌው፤ "በአርባ ምንጭ ከተማ በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት ለመፈፀም ተነሳስተው ፊት ለፊት ያገኟቸውን ባንኮችና የግለሰብ ቤቶች ለመግባት ወጣቱ ገንፍሎ ተነስቶ የነበረ ቢሆንም፤ በጋሞ ባህላዊ ሥርዓት ተማፅኖና ልመና ሁኔታውን በሰላማዊ ሁኔታ ለማለፍ ተችሏል" ብለዋል።
በአካባቢው በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይም ጉዳት እንዳይደርስ በጋሞ ሽማግሌዎች የተደረገው የመከላከል ሥርዓት ለሌሎችም ትምህርት የሚሆን ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ፍትህ፣ ፀጥታና ደንብ ማስከበር ፅ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ገበየሁ ጣራ በበኩላቸው ሕዝቡ በጋሞ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ሕጋዊ ጥያቄ ያቀረበና ፈቃድ እንደተሰጠው ገልፀዋል።
ነገር ግን በመካከላቸው የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሮ ወደ ስታዲየም በመሄድ ፋንታ ንብረት ለማውደም ያመሩት እንደነበሩ ይናገራሉ። የፀጥታ ኃይሎችም ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለመከላከል ወደ ሰማይ ሲተኩሱ እንደነበር ተናግረዋል።
በዚህም ወቅት በባረቀ ጥይት የ2 ሰዎች ሕይወት ሲያፍ፤ 3 ሰዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሶዶ ሆስፒታል ተልከው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በንብረት ላይ የደረሰ ውድመት አለመኖሩን የተናገሩት ኃላፊው አጋጣሚውን በመጠቀም ብጥብጥ ለመፍጠር የሞከሩ 20 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ ገበየሁ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
በከተማዋ ዛሬ መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩና በሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል።

















