ለህዳሴ ግድብ ግንባታ መዘግየት ምን አይነት መፍትሔዎች እየተሰጡ ነው?

የፎቶው ባለመብት, ENN
በአገርና በህዝብ ሃብት የሚካሄድ ትልቅ ብሄራዊ ፕሮጀክት በመሆኑ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሁሌም የኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ነው።
ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሁለት አጋጣሚዎች የህዳሴው ግድብ ከመቼውም የበለጠ መነጋገሪያ ሆኗል።
በመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እስካሁን እየሄደ ባለበት ፍጥነት ግድቡ በመጭው አስር ዓመትም አይጠናቀቅም ብለዋል የሚል መረጃ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በብዛት መንሸራሸሩን ተከትሎ ግድቡ የሁሉም መነጋገሪያ ሆነ።
ከዚያ ደግሞ የግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑትና የግድቡ ምልክት ተደርገው የሚወሰዱት ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ግድያ የግድቡ ጉዳይ ብዙዎችን አነጋገረ፣ አሳሰበም ጭምር።
በኢንጅነር ስመኘው ህልፈት ማግስት መግለጫ የሰጡት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሃይል ሚኒስቴሩ የህዳሴው ግድብ የሲቪል ኢንጅነሪንግ ክፍሉ ግንባታ በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ክፍሉ ማለትም የጀነሬተርና ተርባይን ተከላ ስራ መዘግየቱን ገልፀው ነበር።
ሌላው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ክፍል ውስጥ ያለው የማመንጫ ጣቢያ ነው።
በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ችግር የሆነ ነገሮችን መፍታት የሚያስችሉ እርምጃዎችን እየተመለከቱ መሆኑንም አመልክተው ነበር።
ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ ግድቡ በተያዘለት የግንባታ ሂደት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁትን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አዜብ አስናቀን የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍል ከመዘግየቱ አንፃር አሁን የግድቡ ግንባታ ምን ላይ ነው ስንል ጠይቀናቸው ነበር።
"ግንባታው በአንድ ሰው ላይ ሳይሆን አሰራር(ሲስተም)ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ሌላ ሰው ሃላፊነት ይረከባል ስራውም ይቀጥላል እየቀጠለም ነው"በማለት
የግንባታው የዘገዩ ስራዎች መኖራቸውን ነገር ግን ይህ የተለየ ሳይሆን በዓምስት ተብሎ በአስር ዓመት እንደሚጠናቀቁ የመንገድም ይሁን የሃይል ፕሮጀክቶች እንደሆነ በመግለፅ መልስ ሰጥተዋል።
ፕሮጀክቶች ለምን ይዘገያሉ ለሚለው ክፍያን ጨምሮ የተለያየ ምክንያት ይቀመጣል።በህዳሴው ግድብም ተመሳሳይ ነገር መከሰቱን ተናግረዋል።
የህዳሴው ግድብ የሲቪልና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታ ሂደቶች ተቀባብተው(ኢንተርፌስ አድርገው) ነው መሰራት ያለባቸው።
ብረታ ብረቱ ሲሰራ ኮንክሪቱ ይቀጥላል።ኮንክሪቱ ሲሰራ ብረታ ብረቱ ይቀጥላል።እንደዚ እንደዚ እያለ ነው የሚሄደው።
የግድቡን ግንባታ ችግር ለመፍታት መፍትሄ የተባለው ስፔሻላይዝ ያደረጉ ሰብ ኮንትራክተሮችን ማስገባት ሲሆን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራውን የሚያግዝ ተቋራጭ በማስገባትም የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ክፍል ግንባታ ችግር ለመፍታት እየተሞከረ እንደሆነ ኢንጅነር አዜብ ያስረዳሉ።
እንደ አውሮፓውያን በቀጣዩ ወር ሁለት ተርባይኖች ሃይል ማመንጨት እንዲጀምሩ እቅድ እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገቡን በማስመልከት ጥያቄ ያነሳንላቸው ኢንጅነር አዜብ እንደዚህ ያሉ ነገሮች ላይ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ከፕሮጀክቱ ውስብስብ ተፈጥሮ አንፃር ከባድ እንደሆነ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER
"ፕሮጀክቱ በጣም ውስብስብ ነውና ይህ በዚህ ጊዜ ለማለት ይቸግራል።ከዚህ አንፃር መስከረም ላይ ይሄ ይሆናል አይሆንም ማለት አይቻልም።ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዩኒቶች ስራ ጀምረው ሃይል እንዲያመነጩ የተለያዩ የማፋጠን እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው"ይላሉ።
ሳሊኒ በግንባታ መዘግየት ለደረሰበት ኪሳራ ካሳ የመጠየቁ ነገር እየተሰማ ሲሆን የዚህ አይነቱ የተቋራጮች የካሳ ጥያቄ የሚጠበቅ ነው ይላሉ ኢንጅነሯ።
ጊቤ ሶስት እንዲሁም ገናሌ ደዋሌን በምሳሌነት በመጥቀስም የኮንትራክተሮች ካሳ ጥያቄ የተለመደ እንደሆነ ያመለክታሉ።
ክፍያ ሲዘገይ ተቋራጩ ሰውና ማሽን ያለ ስራ ያስቀመጠበትን ጉዳት ደርሶብኛል ደርሶብኛል ብሎ የካሳ ጥያቄ ያቀርባል።
በሌላ በኩል ወደ ስራ የሚገባው ያለቀለት ሳይሆን መሰረታዊ ዲዛይን ተሰርቶ በመሆኑና በመሰረታዊ ዲዛይኑም በተወሰነ መልኩ እንጂ መሬት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ምን እንዳለ ማወቅ ባለመቻሉም ኋላ ላይ የሚነሳ የካሳ ጥያቄ እንደሚኖር ያስረዳሉ።
ስለዚህም መሬት ላይ ወደ ስራ ሲገባ ያልተጠበቀ ነገር ሊያጋጥም ይችላል።በተመሳሳይ ህዳሴው ግድብ ላይም ያልተጠበቀ ጂኦሎጂካል ሁኔታ አጋጥሞ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
"አንድ ቢሊየን ሜትር ኪዩብ እቆፍራለው ተብሎ ውል ቢገባ በእጥፍ ሊያስኬድ ይችላል። በዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ተቋራጩ ካሳ ይጠይቃል።አሁንም ከህዳሴው ግድብ ተቋራጭ ሳሊኒ መሰል ጥያቄ አለ"
ቀደም ሲል የመጀመሪያ ኮንትራት ሲፈረም ሁለት ጀነሬተሮች እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ስራ እንዲጀምሩ በዚሁ መሰረትም በአሁኑ ወቅት (2018)ደግሞ ሁሉም ጀነሬተሮች ይጀምራሉ ተብሎ ታስቦ እንደነበር ለፕሮጀክቱ ቅርበት ያለቸው የቢቢሲ ምንጮች ይናገራሉ።
ነገር ግን ከ2014 እስከ አሁንም የግድቡ ግንባታ በሂደት እያለ ስራ ይጀምራሉ የተባሉት ጀነሬተሮች አሁንም ስራ አለመጀመራቸው የግንባታውን በጣም መዘግየት እንደሚያሳይ ምንጮቹ ያስረዳሉ።
በዚህ አካሄድ በቀጣዩ ዓመትም ሁለቱ ጀነሬተሮችን ወደ ስራ ማስገባት ፈታኝ እንደሚሆን ስጋታቸውን ይገልፃሉ።
ምንጮቹ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በሲቪል ስራው በኩል ችግር የለብንም እንደሚፈለገው ሊሄድ ይችላል የጎተተው ኤሌክትሮ ሜካኒካሉ ነው ሊባል ይችላል።ነገር ግን ሲቪል ስራውም በጊዜው ሄዷል ማለት አይቻልም።
ስለዚህም በከፍተኛ ጉልበትና አቅም ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።














