የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ስለ ሕዳሴ ግድቡ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, UN TV
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እና ሥራን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን አለመግባባት ላይ መክረዋል።
ለመሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ምን አሉ?
የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝደንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበርን ወክለው ንግግር ያሰሙት ፖል ሎሶኮ የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያን ኃይል ማመንጨት አቅም የሚያሳድግና ሌሎችንም አገራት የሚጠቅም ነው ብለዋል።
ምንም እንኳ ግድቡ በአፍሪካ ቀዳሚው የመሆን አቅም ቢኖረውም ለሱዳንና ግብፅ ስጋት ይዞ መጥቷል ያሉት ተወካዩ ለዓመታት የተደረጉ ውይይቶች አለመሳካታቸውን አውስተዋል።
ተወካዩ፤ የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት መሪ ፕሬዝደንት ፌሊክስ አንትዋን ሺሴኬዲ በሦስቱ አገራት መካከል መተማመን ለማምጣት እንዲሁም የጋራ ጥቅምን ለማጎልበት እየሠሩ ናቸው ሲሉ ለታዳሚዎች ተናግረዋል።
የወቅቱ የሕብረቱ መሪ መፍትሄ እስኪመጣ ድረስ ሦስቱ አገራት ሁኔታዎችን የሚያወሳስብ አቋም ከማራመድ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል ብለዋል ተወካዩ።
አገራትምን አሉ?
የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መታየት አለበት ስትል ጉዳዩን ወደ ምክር ቤቱ ያመጣችው ቱኒዚያ፤ የዓባይ ወንዝ የሦስቱ አገራት ሕዝቦች ጥገኛ የሆኑበትና የዕድገት መሠረት ነው ስትል ተደምጣለች።
ቱኒዚያ በተወካይዋ ታሪክ ላዴብ አማካይነት የሦስቱ አገራት ውይይት በአፍሪካ ሕብረት በኩል መቀጠል አለበት ብትልም የፀጥታው ምክር ቤት ሕብረቱን ሊያግዝ ይገባል ስትል አክላለች።
ዩናይትድ ኪንግደምን ወክለው የተገኙት ባርብራ ዉድዋርድ አገራቸው ሦስቱ ተደራዳሪዎች የጋራ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አጥብቃ እንደምትመኝ አሳውቀዋል።
ቱኒዚያም ሆነች ዩናይትድ ኪንግደም ሦስቱ አገራት በፈረንጆቹ 2015 ከስምምነት የደረሱት የጋራ ስምምነት ማዕቀፍን [ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ] ተገን አድርገው እንዲደራደሩ ጥሩ አቅርበዋል።
የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል የሆነች ጎረቤት አገር ኬንያ፤ ግብፅና ሱዳን የሚያነሱት ስጋት ትክክል ቢሆንም የሦስቱም አገራት ሕዝቦች እኩል ዕድገትና ብልፅግና እንደሚያስፈልጋቸው እናምናለን ብላለች።
የኬንያው ተወካይ ማርቲን ኪማኒ አገራቸው፤ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን "ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካ መፍትሄ" በሚለው መርህ መሠረት መፍትሄ እንደሚሹ እንደምታምን አስታውቀዋል።
ሩስያና ቻይና
የሩስያው ተወካይ በበኩላቸው አገራቸው በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን ሁኔታ በአንክሮ እየተከታተለች እንደሆነ ጠቁመው፤ የሕዳሴው ግድብ በሚሊዮን ለሚቆጠረውና የኤልክትሪክ ችግር ላለበት የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ጠቀሜታ እንደሚረዱ አስታውቀዋል።
ሆኖም ግን ከግብፅና ሱዳን በኩል ያለውን ስጋት እንረዳለን ሲሉ የሩሲያው ተወካይ ጠቁመዋል። ሆኖም ጉዳዩን በውይይት መፍታት እንጂ የኃይል አቅምን ማሳየት ሊቀር እንደሚገባ አሳስበዋል።
ተወካዩ ሦስቱ አገራት በፈረንጆቹ 2015 ካርቱም ላይ የተደረሰውን 'ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ' መሠረት አድርገው እንዲወያዩም ጥሪ አቅርበዋል።
በግድቡ ሙሌት ዙሪያና በቀጣይ እርምጃዎች ላይ ከስምምነት መድረስ ሦስቱን አገራት ካላስፈላጊ ንትርክ ያስቀራቸዋል ብላ ሩሲያ እንደምታምን ተወካይዋ አስታውቀዋል።
ሩስያ ሌሎችም የዓባይ ተፋሰስ ሃገራት የተካተቱበት ውይይት መደረግ አለባት እንደምታምን ተወካይዋ በፀጥታው ምክር ቤት አባላት ፊት ተናግረዋል።
ተወካዩ የሦስቱ አገራት ውይይትን ለማስቀጠል የአፍሪካ ሕብረት እያደረገ ያለውን ጥረት እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። አክለው ተጨማሪ አወያዮችና አሸማጋዮች መካተታቸው የሚጨምረው ነገር እንደሌለው ሃገራቸውን ወክለው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የቻይናው ተወካይ ሦስቱ አገራት በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ከስምምነት ከደረሱ ታላቁ የሕዳሴ ለሶስቱም አገራት ጠቃሚ የሆነ ፕሮጀክት ይሆናል ብላ ቻይና እንደምታምን ተወካዩ ለፀጥታው ምክር ቤት ተናግረዋል።
እንደ አብዛኛዎቹ የምክር ቤቱ ቋሚና ተለዋጭ አባላት ሦስቱ አገራት በ2015ቱ 'ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ' ላይ እንዲመረኮዙ ጥሪ አቅርባ የአፍሪካ ሕብረትን ጥረት አድንቃለች።












