የሕዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትና የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a
ቀደም ብላ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ኢትዮጵያ ግንባታው ወደ መጠናቀቁ እየተቃረበ ያለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌትን ባለፈው ሰኞ ሰኔ 28/2013 ዓ. ም መጀመሯን ይፋ አድርጋለች።
ግብፅና ሱዳን ከመጀመሪያው የግድቡ የውሃ ሙሌት ጀምሮ ሕጋዊና አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረግ የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዳይጀመር ሲወተውቱ ቢቆዩም፤ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን ኢትዮጵያ ማሳወቋ ይታወሳል።
ሁለቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ የሚያቀርቧቸው ጥያቄዎች በተፈጥሮ ሀብቴ ከመጠቀም እንድታቀብ የሚያደርጉ ናቸው የምትለው ኢትዮጵያ፤ የግድቡን ግንባታ በማፋጠን ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን በምትዘጋጅበት ጊዜ በውዝግቡ ውስጥ ሌሎች አካላት ጣልቃ እንዲገቡ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።
ሱዳንና ግብፅ ሁለተኛው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት አሳሪ የሆነ ስምምነት ሳይደረግ እንዳይጀመር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ኢትዮጵያ በዕቅዷ መሰረት ውሃ መሙላቱን መጀመሯን ለግብፅ ባለሥልጣናት ስታሳውቅ ተቃውሟቸውን የገለጹት ወዲያው ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ጥቂት ቀናት ሲቀሩት የተጀመረው የውሃ ሙሌት "በዓለም አቀፍ ወንዞች ዙሪያ የሚሰሩ ግንባታዎችን በተመለከተ የተቀመጠውን ሕግና ደንብ የጣሰ የተናጠል እርምጃ ነው" ስትል ግብፅ ተቃውሞዋን ገልጻለች።
ዛሬ የሚሰበሰበው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አንስቶ ውይይት እንደሚያደረግ ባለፈው ሳምንት አሳውቆ ነበር።
ሱዳንና ግብፅ በተለያዩ ጊዜያት ጉዳዩን በሚመለከት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አቤቱታቸውን ሲያሰሙ የነበሩ ሲሆን ዛሬ የሚካሄደውን የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቀችው ሱዳን ናት።
የሱዳኗ የውጭ ሚኒስትር ዛሬ ሐሙስ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ወደ ኒው ዮርክ የተጓዙት ከቀናት በፊት ባለፈው ሰኞ ሲሆን የግብፅ ባለሥልጣንትም እንደሚገኙበት ይጠበቃል።
እንደ ግብፅ ሁሉ ሱዳንም ኢትዮጵያ ከስምምነት በፊት ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት እንዳታከናውን አጥብቃ ስትቃወም ነበር።
የኢትዮጵያ ተቃውሞ
የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡ ድርድር ጉዳይ ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት የሚቀርብ እንዳልሆነ በመግለጽ ጉዳዩን በያዘው አህጉራዊ ድርጅት በኩል የመጨረሻ እልባት ሊያገኝ የሚችል ነው ሲል ሂደቱን ተቃውሞታል።
ኢትዮጵያ ዛሬ ከሚካሄደው የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ቀደም ብላ የአፍሪካ ሕብረት በሦስቱ አገራት መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት እያካሄደ ያለው ጥረት "እንዲከበር" ጠይቃለች።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "የግድቡ ድርድር በጸጥታው ምክር ቤት የኃላፊነት ክልል ውስጥ የማይገባ በመሆኑ" በሦስቱ አገራት ተሳትፎ በአፍሪካ ሕብረት በኩል የሚካሄደውን ጥረት እንዲያከብር ጥሪ አቅርቧል።
ጨምሮም በግብፅና በሱዳን አማካይነት የአረብ ሊግን በማስተባበር የግድቡ አለመግባባት ወደ ጸጥታው ምክር ቤት እንዲሄድና ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊና የደኅንንት ጉዳይ ለማድረግ ሞክረዋል ሲል ወቅሷል።
የጸጥታው ምክር ቤት
ዛሬ በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ስብሰባ በሱዳንና በግብፅ ጥያቄ የተጠራ ነው።
ቢሆንም ግን ስብሰባው ከውይይትና ሐሳብ ከማቅረብ በዘለለ በየትኛውም ወገን ላይ ተጽእኖን የሚያሳድር ውሳኔ ላይ የሚደርስ እንዳልሆነ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት በተባበሩት መንግሥታት የፈረንሳይ አምባሳደር ኖኮላስ ደ ሪቪዬር፤ ባለፈው ሳምንት የጸጥታው ምክር ቤት በሚያደርገው ስብሰባ ጉዳዩን በተመለከተ የጎላ ሚና እንደማይኖረው ተናግረው ነበር።
ምክር ቤቱ በሚያደርገው ውይይት ሦስቱን አገራት በመጋበዝ በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን "ስጋት እንዲገልጹና ከስምምነት ሊያደርሳቸው ወደሚችለው ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ሊያደረግ የሚችለው ነገር የለም" ብለዋል።
ነገር ግን የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ከዚያ የዘለለ ሊያከናውን የሚችለው ነገር እንደሌለ ሰብሳቢው ጨምረው መግለጻቸው ይታወሳል።
አረብ ሊግ
በሱዳንና በግብፅ ጥያቄ መሠረት ባለፈው ወር ኳታር ዶሃ ውስጥ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚኒስትሮች ደረጃ የተወያየው የአረብ ሊግ የአባሎቹን ጥቅም ለማስከበር ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጾ ነበር።
ሊጉ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብቶ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቋል።
ኢትዮጵያ ሊጉ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ዙሪያ ጣልቃ መግባቱን በመቃወም ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ልካለች።
ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፤ የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ያሳየው ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያን እንዳስቆጣ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተዋል።
ጨምረውም ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግብድ ግንባታን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት የሦስትዮሽ ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የአረብ ሊግ ጣልቃ ገብነት ተገቢ አለመሆኑ በመጥቀስ ሚኒስትሩ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር ሲከናወን የቆየው ድርድር አንዳቸው ሌላኛውን በመውቀሳቸው ከስምምነት ሳይደረስ አስካሁን የቆየ ሲሆን፤ ግብፅና ሱዳን አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብርትና የተባበሩት መንግሥታት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ ቢጠይቁም ከኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል።
ቢሆንም ግን ሁለቱ አገራት በቻሉት አቅም በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ያስችለናል ያሏቸውን የተለያዩ ጥረቶችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። አሁንም እያደረጉ ነው።
ቀደም ሲል የአረብ አገራት ማኅበር በሆነው የአረብ ሊግ በኩል ተመሳሳይ አቋም እንዲያዝ ለማድረግ የቻሉ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በመውሰድ ውይይት እንዲደረግበት ጠይቀዋል።
ታላቁ ሕዳሴ ግድብ
ከአስር ዓመት በፊት ግንባታው ተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደሚደረግበት የተነገረ ሲሆን ሙሉ ገንዘቡ ከሕዝብ መዋጮና ከመንግሥት በጀት የሚመጣ ነው።
ግንባታው እየተፋጠነ ያለው ግድቡ ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመጭ ሲሆን ይህም ለአገሪቱ እንዲሁም ለጎረቤት አገራት የኃይል አቅርቦት ምንጭ ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ ከሰማኒያ በመቶ በላይ ግንባታው እንደተጠናቀቀ የተነገረለት ግድቡ በዚህ ሳምንት ከተጀመረው ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት በኋላ በሚቀጥለው ዓመት የመጀመሪያ ዙር ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሏል።
ግድቡ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚው እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን በዓለም ዙሪያ ካሉ ታላላቅ ግድቦች መካከል የሚመደብ ነው።















