ግብጽ የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጀመርን ተቃወመች

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብጽ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ የሚጥል ነው ስትል እርምጃውን ተቃወመች።

የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ ከኢትዮጵያ በኩል የውሃ ሙሌቱ ስለመጀመሩ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ እንደደረሳቸው አመልክተው ውሳኔውን ግን አንቀበለውም ብለዋል።

ሚኒስትሩ ባወጡት መግለጫ "የተናጠል ውሳኔው" የዓለም አቀፍ ሕጎችን የሚጥስ እንዲሁም የናይል ወንዝን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ወንዞች ተፋሰስ ሃገራት ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን አሰራርም ያላከበረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ የወሰደችውን እርምጃም በተመለከተ ሚኒስትሩ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት ደብዳቤ መፃፋቸው በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሱዳንና በግብጽ ጥያቄ መሠረት በዚህ ሳምንት እንደሚወያይ ይተበቃል።

ነገር ግን ምክር ቤቱ ሦስቱን አገራት በመጥራት ስጋታቸውን እንዲገልጹና ከስምምነት ሊያደርሳቸው ወደሚችለው ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ሊያደረግ የሚችለው ነገር እንደሌለ ባለፈው ሳምንት መግለጹ ይታወሳል።

በሱዳን የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር እሁድ እለት እንዳሉት ግብጽና ሱዳን የሦስቱ ዓመት የሕዳሴ ግድብ ሙሌት ዝርዝር መረጃ እንዳላቸው ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ዘገባው ጨምሮም አገራቱ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት ጉባኤ መውሰድ እንደማይገባቸውና ይህ ጉዳይ የሰላምና የጸጥታ ጉዳይ አይደለም በማለት አምባሳደሩ መናገራቸውን አስነብቧል።

ግብጽና ሱዳን ለረዥም ጊዜያት ያህል ያለ ሕጋዊ አሳሪ ስምምነት የግድቡ ሙሌት እንዳይጀመር ሲያስጠነቅቁ ነበር።

የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑት ግብጽና ሱዳን ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ የወጣበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የሚደርሳቸውን የውሃ ፍሰት ይቀንሰዋል በማለት ይከራከራሉ።

ግብጽ በተደጋጋሚም ለመጠጥ ውሃም ይሁን የምጣኔ ሀብት መሰረቴ ነው የምትለውን የናይል ወንዝ ፍሰት ያስተጓጉለዋል በማለትም የሕዳሴ ግድቡ አሰራር ላይ አሳሪ ስምምነት ሳይደረስ ውሃ ሙሌቱ እንዳይደረግ አጥብቃ ስትከራከር ቆይታለች።

ሱዳን በበኩሏ ግድቡ ከራሷ ካሏት ግድቦች ደኅንነትና ከጎርፍ መጥለቅለቅም ጋር በተገናኘ ስጋት አጭሮብኛል ትላለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ የሕዳሴ ግድብ የልማቷ መሰረት እንደሆነና 60 በመቶው ለሚሆነው ሕዝቧ የመብራት አገልግሎት ለመስጠትም አቅዳለች።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የምታደርገው ሁለተኛ ሙሌት የውሃ መጠን በምታገኘው የክረምት ዝናብ ላይ እንደሚወሰን መሆኑን የግብጽ የመስኖ ሚኒስትር ቃለ አቀባይ መሐማድ ጋኒም ለአገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ መናገራቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል።

"በአሁኑ ወቅት ላይ በናይል ምንም አይነት ለውጥ አናይም። ልዩነቱን ከአንድ ወይም ከአንድ ወር ተኩል በኋላ የምናየው ይሆናል" ብለዋል።

ከግድቡ አጠቃላይ አሰራር ጋር በተገናኘ አሳሪ ስምምነት ያስፈልጋል በሚል ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ግብጽና ሱዳን ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ዘመቻም በኢትዮጵያ ላይ ከፍተው ነበር። ለዓመታት ያህል ሲንከባለል የቆየው የሦስትዮሽ ድርድር ፍሬ ማፍራት አልቻለም።

አገራቱ የሚያደርጉትን ዲፕሎማሲያዊ ጫና ተቋቁማ የመጀመሪያ ሙሌቷን ያካሄደውችው ኢትዮጵያ ሁለተኛ ውን ዙር ሙሌቷንም በዘንድሮው ክረምት ጀምራለች።

ካርታ

ኢትዮጵያ በበኩሏ ለዓመታት በታችኛው ተፋሰስ አገራት ቁጥጥር ስርና የበላይነት በነበረው የአባይ ወንዝ ላይ ተፈጥሯዊ መብቷን እያስጠበቀች እንደሆነ በመናገር የግድቡን ፋይዳ ታስረዳለች።

ግብጽ ከምታነሳቸው ቅሬታዎች መካከል ኢትዮጵያ ግድቡን ሙሉ አቅም እየተጠቀመች ድርቅ ቢያጋጥም ችግሩ የሦስቱም አገራት ጉዳይ ነው የሚል አቋም ላይ መድረሷ ነው።

ረዘም ላለ ጊዜ ድርቅ የሚከሰት ከሆነ ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጥቅምን ለመጠበቅ ዋስትና ልትሰጠን ይገባል በማለትም ግብጽ ትከራከራለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በተደጋጋሚ ግብጽ የቅኝ ግዛት ውሎችን ሙጥኝ እንዳለችና ኢ-ፍትሃዊና አግላይ የሆነውን ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና እያደረገች ነው በማለትም ትወቀሳለች።

ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመጭ የተነገረለት ግዙፉ ግድብ ከሚሰጠው ጠቀሜታ ባሻገር የጎላ ጉዳት በታችኛው ተፋሰሱ አገራት ላይ አያስከትልም በማለት፤ ስምምነት ተደረስም አልተደረሰ በዚህ የክረምት ወር ሁለተኛውን ዙር ሙሌት እንደምታከናውን ኢትዮጵያ አሳውቃለች።

በተደጋጋሚ ያለስምምነት ሲቋረጥ የቆየው የሦስቱ አገራት ድርድር ውጤት ሳያስገኝ በመቅረቱ ሱዳንና ግብጽ ጉዳዩን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲመለከተው ከመጠየቃቸው ባሻገር ሌሎች ምዕራባውያን አገራት በአደራዳሪነት እንዲሳተፉ በተደጋጋሚ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ግን የግድቡ ድርድር ጉዳይ እየተካሄደ ባለበት በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር መጠናቀቅ እንዳለበት በመግለጽ ሌሎች አደራዳሪዎች እንዲገቡበት መጠየቅ "የሕብረቱን ጥረት ማንኳሰስ ነው" በማለት ውድቅ አድርጋዋለች።

የአፍሪካ ሕብረትና አሜሪካ በተለያዩ ወቅቶች ሦስቱን አገራት ለማሸማገል ለተራዘመ ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም በየትኛውም ድርድር ሁሉንም ከሚያስማማ ውጤት ላይ ለመድረስ አልቻሉም።

ግብጽና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምናገኘውን የውሃ መጠን ይቀንሰዋል በሚል ተደጋጋሚ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የቆዩ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡን ውሃ ለ65 ሚሊዮን ዜጎቿ የኤሌትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምጠቀምበት በመሆኑ ችግር አይፈጥርም በማለት ስጋታቸው ተገቢ እንዳልሆነ ስትገልጽ ቆይታለች።

ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታው እየተካሄደ ያለውና ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፤ ከአፍሪካ ትልቁ እንደሆነ የሚነገር ሲሆን ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችል አቅም ያለው ግዙፍ ግድብ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ባለፈው ዓመት ክረምት ላይ የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ዙር ደግሞ በዚህ ሳምንት ተጀምሯል፤ ግድቡ በሚጥለው ዓመት በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል።