ሕዳሴ ግድብ፡ የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ባለሥልጣናት የሕዳሴ ግድቡን በሚመለከት የጎበኟቸው የአፍሪካ አገራት

ሕዳሴ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በሕዳሴ ግድቡ ዙሪያ ኪንሻሳ ያደረጉት የሶስትዮሽ ድርድር ያለውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸውን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ልከዋል።

ሦስቱ አገራት ለዓመታት በሕዳሴ ግድብ ውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ጋር በተያያዘ ሲያደርጉት የነበረው ድርድር ይህ ነው የሚባል ውጤት አላመጣም።

በህዳሴ ግድቡ ጉዳይ ለ3 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የኪንሻሳው የሶስትዮሽ ውይይት ያለስምምነት ሲጠናቀቅ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ በኪንሻሳው ውይይት ላይ "ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስቸግር ግትር አቋም አራምዳለች" ብላ ስትከስ፣ ግብፅ ደግሞ "ኢትዮጵያ ሁሉንም የድርድር ሂደት አማራጮች ውድቅ ማድረጓን" አስታውቃለች።

ኢትዮጵያ በበኩሏ ውይይቱ ያለስምምነት ለመጠናቀቁ ሱዳን እና ግብጽን ወንጅላለች።

በባለፉት ሳምንታት የሶስቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት ዋነኛ ዓላማም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ውዝግብ ሲሆን ትኩረት ያደረጉት ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጀት የጸጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ሃገራትን ነው።

ኒጀር፣ ቱኒዚያ እና ኬኒያ የወቅቱ የተመድ ተለዋጭ የጸታው ምክር ቤት አባላት ናቸው።

ኢትዮጵያ መጪው ክረምት ሲገባ ሁለተኛ ዙር ሙሌቷን በእቅዷ መሰረት እንደምታከናውን አስታውቃለች። ነገር ግን ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዙር ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ስምምነት ላይ መደረስ አለበት ይላሉ።

ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ከማካሄዷ በፊት ግብጽ እና ሱዳን ለመረጃ ልውውጥ ባለሙያዎች እንዲመድቡ ጠይቃለች።

ኢትዮጵያ ወዴት አቀናች?

የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ ጋር በመሆን ወደ ኒጀር አቅንተዋል።

እነዚህ የኢትዮፕያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኒያሚ ቆይታቸው ለፕሬዝዳንት ሞሐመድ ባዞም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ገለጻ ማድረጋቸውን የውሃ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት ያስረዳል።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶ/ር ስለሺ በቀለ በትዊተር ሰሌዳቸው፤ ከኒጀር ፕሬዚዳንት እና ሚኒስትሮቻቸው ጋር በኒያሚ ውይይትና ጉብኝት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በጉብኝቱም በትግራይ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የህዳሴ ግድብ ድርድር እና የግንባታ ደረጃ፣ ቀጣዩ ምርጫና ከሱዳን ጋር ስላለው የድንበር ጉዳይ የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳታቸውን አስታውቀዋል።

"ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ ፍቱን መሆኑን ታምናለች" ብለዋል ሚንስትሩ።

በሌላ በኩል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ወደ ደቡብ አፍሪካ በማቅናት ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸውን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሱዳን ምን አከናወነች?

የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር መሪያም አልሳዲቅ አልመሐዲ (ዶ/ር) በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን አነጋግረዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ በቅድሚያ ያቀኑት ወደ ኬንያ ሲሆን ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ከኬንያ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ራይቼል ኦማሞ እና በናይሮቢ ከሚኖሩ የሱዳን ማህበረሰብ አባላት ጋር መወያየታቸውን ተገልጿል።

ከፕሬዝደንት ኡሁሩ ጋር በነበራቸው ውይይት ከግድቡ ጋር በተያያዘ ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ስምምነት መደረስ አለበት የሚል አቋም ሱዳን እንዳላት አንጸባርቂያለሁ ብለዋል የውጪ ጉዳይ ሚንስትሯ በትዊተር ገጻቸው ላይ።

የውጪ ጉዳይ ሚንሰትሯ ሩዋንዳ ተገኝተው ተመሳሳይ ውይይት ከፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ጋር አድርገዋል።

ፕሬዝደንት ኡሁሩ እና ፕሬዝዳንት ካጋሜ ከሱዳኗ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጋር በተገናኙበት ወቅት ከጠቅላይ ሚንስትር ሃምዶክ የተላከ መልዕክት ተቀብለዋል።

ግብጽ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወደዴት አቀኑ?

የግብጽ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ሳሚ ሽኩሪ የግድቡን ድርድር በተመለከተ የአገራቸውን አቋም ለማንጸባረቅ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጉዞ አድርገው ነበር።

ሳሚ ሽኩሪ ከሳምንታት በፊት ወደ ወደ ኬንያ፣ ኮሞሮስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሴኔጋል፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኦፍ ኮንጎ እና ቱኒዚያ ተጉዘዋል።

ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ድርድሩን በአፍሪካ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲቀጥል ፍላጎት አላት። በቀጣይ የክረምቱ ወራት ሁለተኛው የግድቡ ውሃ ሙሌት እንደምታካሂድ ይፋ ያደረገችው ኢትዮጵያ፤ በአፍሪካ ሕብረት የሚመራውን አደራዳሪ ቡድን ወደ ጎን ማድረግ፤ በሦስቱ አገራት መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል ትላለች።

ግብጽ እና ሱዳን በበኩላቸው ሶስቱ አገራት ከስምምነት ሳይደርሱ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት መካሄድ የለበትም ይላሉ። ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ እና የአውሮፓ ሕብረት በአደራዳሪነት እንዲመሩ ፍላጎት አላቸው።

የህዳሴ ግድብ

በአምስት ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እስካሁን ሲጓተት ቆይቶ በግንባታ ላይ አስር ዓመትን አስቆጥሯል።

ተገንብቶ ሲያበቃ በግዝፈቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሚሆን የተነገረው ግድቡ በአሁኑ ጊዜ ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግንባታ ሥራው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን በሚቀጥለው ዓመት በከፊል የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል ተብሎ ይጠበቃል።

ከአምስት ሺህ በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የተነገረለት ይህ ግድብ ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ ለኢንዱስትሪዎችና ለጎረቤት አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ያቀርባል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።