ሕዳሴ ግድብ፡ ግብጽ በባለሙያዎች የቀረበውን ሰነድ አልቀበልም ማለቷ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, FBC
ተቋርጦ የቆየው በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚደረገው ስብሰባ እሁድ ዕለት ሲካሄድ ግብጽ በአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የተሰየሙ ባለሙያዎች ያቀረቡትን ረቂቅ ሰነድ እንደማትቀበለው ማስታወቋን የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት ሲያካሂዱት የቆየው የበይነ መረብ ውይይት ለአንድ ወር ያህል ተቋርጦ ቆይቶ ሲጀመር በባለሙያዎች የቀረበውን ረቂቅ ሰነድ ኢትዮጵያና ሱዳን በአዎንታዊ መልኩ እንደሚቀበሉት አሳውቀዋል ብሏል ሚኒስቴሩ ባወጣው መግለጫ።
በሦስቱ አገራት መካከል መልሶ የተጀመረውን ስብሰባ በደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ትብብር ሚኒስትር እና በአፍሪካ ሕብረት አስፈጻሚ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሰብሳቢነት ተካሂዷል።
እሁድ ዕለት በተካሄደው ውይይት ላይ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይና የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተሳተፉ ሲሆን፣ የሕዳሴው ግድብ ድርድር በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ማድረጋቸው እና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር የሰየሟቸው ባለሙያዎች ባቀረቡት ረቂቅ ሰነድ ላይ መወያየታቸው ተገልጿል።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ የቀረበውን ሰነድ እንደምትቀበለውና "በቀጣይ በሚካሄደው ድርድር ሰነዱን እንደግብዓት ለመጠቀም ፈቃደኛ መሆኗን" እንዳሳወቀች ጠቅሶ፤ ሱዳንም "ሰነዱን ለሂደቱ ጠቃሚ አድርጋ እንደምትመለከተው" በመግለጽ ድርድሩን መቀጠል ፍላጎት እንዳላት ስታሳውቅ "የግብጽ ወገን ሰነዱን ጨርሶ እንደማይቀበለው ገልጧል" ብሏል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ላይ እንዳሳወቀው የሕዳሴው ግድብ ሙሌትና ዓመታዊ አስተዳደርን የሚመለከተው ሰነድ ላይ የሚደረገው ድርድር በአመዛኙ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን አመልክቶ፤ "ወደፊት በአባይ ተፋሰስ ላይ ከሚገነቡ የውሃ ልማት ሥራዎች ጋር የሚኖረው ቁርኝት ዋነኛ የልዩነት ሃሳብ ነው" ሲል ገልጿል።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ውይይቱ ከመጀመሩ በፊት በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት ሦስቱ አገራት በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌትና በዓመታዊ የሥራ ሂደቱን በሚመለከቱ ደንቦችና መመሪያዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸው ነበር።
ሚኒስትሩ ጨምረውም በአሁኑ ውይይት ላይ የሚደረገው የውሃ ሙሌት ወይይት ግድቡን ሙሉ ለሙሉ በውሃ መሙላት የሚመለከት መሆኑን አብራርተዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍጆታ የሌለው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ በመሆኑ የሚደረሰው ስምምነት ይህንን ከግምት ያስገባና የተሟላ የውሃ ስምምነትና ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲኖር ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ የጠቀሰው የሚኒስቴሩ መግለጫ፤ ስምምነቱ "የኢትዮጵያን የመጠቀም መብት የሚያቅብ እንዲሆን አትፈቅድም" ብሏል።
የሦስትዮሽ ውይይቱ የአገራቱ ባለሙያዎች በሚያደርጉት ውይይት ስምምነት የተደረሰባቸውንና የልዩነት ሃሳቦችን በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እንደሚያቀርቡና ውይይቱ እንደሚቀጥል ተገልጿል።
በድርድሩ ላይ በታዛቢነት የሚሳተፈው የአውሮፓ ሕብረት የሦስቱ አገራት ውይይት መልሶ መጀመሩን በተመለከተ በቃል አቀባዩ በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ ውይይቱ "ግድቡን ስለመሙላትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ወደ ስምምነት ለመድረስ እድልን ይፈጥራል" ብሏል።
አምስት ቢሊዮን ዶላር በሚጠጋ ገንዘብ ላለፉት አስር ዓመታት በግንባታ ላይ የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ 78 በመቶ ግንባታው ተጠናቋል።
የግብጽ ቅሬታ
እሁድ ዕለት መልሶ ከተጀመረው ድርድር ቀደም ብሎ የግብጽ መንግሥት ካይሮ የሚገኙ የኢትዮጵያን ዲፕሎማትን ጠርቶ ባለፈው ማክሰኞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት አስተያየት ላይ ማብራሪያ መጠየቁ ይታወሳል።
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን ቻርጅ ዲ አፌርን ረቡዕ ዕለት በመጥራት ቃል አቀባዩ ተናግረውታል ባለው ጉዳይ ላይ ማብራሪያ መጠየቁን ቢገልጽም፤ ዝርዝር ነገር አልጠቀሰም ነበር።
አህራም የተባለው የግብጽ ጋዜጣ ስለጉዳዩ እንዳለው ዲፕሎማቱ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠሩት በቃል አቀባዩ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት በግብጽ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል በሚል እንደሆነ አመልክቶ፤ የተባለው አስተያየት ምን እንደሆነ ሳይገለጽ ማለፉን ዘግቧል።
ይህ ከአገሪቱ በኩል የተሰማው ቅሬታ ምናልባትም ግንባታው ወደ መጠናቀቁ የቀረበውና ግብጽ ከፍተኛ ተቃውሞና ስጋት እያሰማችበት ካለው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ቃል አቀባዩ በሰጡት አስተያየት ላይ ሊሆን እንደሚችል ተገምቶ ነበር።
እስካሁን መቋጫ ያላገኘውና በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለወራት ሲካሄድ የቆው ግድቡን የተመለከተው ድርድር ተቋርጦ ቆይቶ በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ለዓመታት በግንባታ ላይ የሚገኘውና በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ከስምምነት መደረስ አለበት በሚል ሁለቱ አገራት ግፊት ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ባለፈው የክረምት ወር መጀመሪያ ደረጃ የውሃ ሙሌትን ማከናወኗ ይታወሳል።
አብዛኛው የግንባታ ሥራው እየተጠናቀቀ የሚገኘው ግድቡ በከፊል ኃይል የማመንጨት ሥራውን ከወራት በኋላ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
ግብጽ ከአባይ ወንዝ ላይ በማገኘው የውሃ መጠን ላይ መቀነስን ያስከትላል በሚል ጥያቄ በምታስነሳበት ግድብ ዙሪያ በአዲስ አበባ፣ ካርቱም፣ ካይሮና ዋሽንግተን ውስጥ ተከታታይ ድርድሮች ቢካሄዱም አስካሁን መቋጫ የሚሆን ስምምነት ላይ አልተደረሰም።
በተለይ በአሜሪካ አሸማጋይነት ዋሽንግተን ላይ ሲካሄድ የነበረው ድርድር አንዳች ድምዳሜ ላይ ይደርሳል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በመጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚያስጠብቅ አይደለም በማለት ራሷን ከስምምነቱ ውጪ ማድረጓ ይታወሳል።

















