በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በታኅሣስ ወር ብቻ የደረሱ የእሳት አደጋዎች

በወላይታ ሶዶ ከተማ "መርካቶ ገበያ" የደረሰው ቃጠሎ

የፎቶው ባለመብት, Wolaita Zone chief Administrator's

በኢትዮጵያ በተለያዩ ከተሞች በዚህ ዓመት በታኅሣስ ወር ብቻ በርካታ የእሳት አደጋዎች ደርሰዋል። በዚህም የተነሳ በሚሊዮኖች ብሮች የሚገመት ንብረት ወድሟል።

እነዚህ አብዛኞቹ የእሳት አደጋዎች የደረሱት በተለይ በገበያ ሥፍራዎች ላይ ሲሆን በመኖሪያ አካባቢዎች ላይ ደረሱና ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎች የተፈናቀሉባቸውም አጋጣሚዎች አሉ።

ቢቢሲ ከተለያዩ የዜና ዘገባዎች ካሰባሰባቸው የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች ውስጥ ባለንበት የታኅሣስ ወር ያጋጠሙት በቁጥር በርከት ይላሉ። ምክንያቱን ግን ለመገመት አስቸጋሪ ነው።

ቢሆንም ይህ ተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ትኩረት እንዲያገኝ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ያገኙትን የእሳት አደጋዎችን በየቀናቸው በቅደም ተከተል እንደሚከተለው አጠናቅረናቸዋል።

ነገር ግን በወሩ ውስጥ የተከሰቱት የእሳት አደጋዎች እነዚህ ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። በተለያዩ ምክንያቶች ያልተነገሩ እንዲሁም በዚህ ጥንቅር ውስጥ ያልተካተቱ ሊኖሩ የሚችሉብት ዕድል አለ።

ኅሣስ 8/2013 ዓ.ም ሐረማያ

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ህንፃ 3 በሚባለውና የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ከሚኖሩበት ህንፃ የኤሌክትሪክ መቆጣጠሪያ ላይ የተነሳ የእሳት አደጋ ተከስቶ እንደነበር የዩኒቨርስቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስታውቆ ነበር።

በአደጋው በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ ቢሆንም በሰው ላይ ምንም ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

ኅሣስ 9/2013 ቡራዩ

በቡራዩ ከተማ በደረሰ የእሳት አደጋ ግምቱ 10 ሚሊየን ብር የሆነ ንብረት የወደመ ሲሆን፤ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እሳቱ ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ መቀስቀሱን ገልጾ ነበር።

አደጋው የደረሰው በቡራዩ ከተማ ገፈርሳ ኖኖ ቀበሌ ልዩ ስሙ ገብርኤል በሚባል አካባቢ ሲሆን በ16 ሱቆች፣ በ3 መኖሪያ ቤቶችና 3 ባርና ሬስቶራንቶች ላይ ውድመት ቢያጋጥምም በሰው ላይ ምንም ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።

ኅሣ11/2013ወላይታ ሶዶ

በወላይታ ሶዶ ከተማ "መርካቶ ገበያ" መንስኤ ባልታወቀ ሁኔታ የእሳት አደጋ የተከሰተው ሲሆን በወቅቱ እሳቱን ለማጥፋት የወላይታ ሶዶ ከተማ እሳት አደጋ መከላከያ ቡድን ጥረት ያደረገ ቢሆንም በነበረው ከባድ ነፋስ እሳቱ በከፍተኛ ፍጥነት መዛመቱ ተገልጿል።

አደጋው በበርካታ የንግድ ሱቆችና ተቋሟት ላይ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፤ ማለዳ የተነሳውን የእሳት አደጋ መቆጣጠር የተቻለውም ከ6:20 በኋላ እንደነበር በወቅቱ የከተማው አስተዳደር አሳውቋል።

በሶዶ ከተማ የገበያ ቦታ ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎ አደጋ ሲደርስ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የግብይት ማዕከሉን ዘመናዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ተገልጿል።

በወላይታ ሶዶ ከተማ "መርካቶ ገበያ" የደረሰው ቃጠሎ

የፎቶው ባለመብት, Wolaita Zone Chief Administrator's

ኅሣስ 13/2013 ባሕርዳር

በአማራ ክልል መዲና በባሕር ዳር ከተማ ቀበሌ 3 በተለምዶ ጉዶባሕር ተብሎ በሚጠራው ሰፈር በደረሰ የእሳት አደጋ በ22 የመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት ሲደርስ፤ በቃጠሎው ከ300 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተነግሯል።

ከቀኑ 7:00 ሰዓት ገደማ የተነሳውን ይህን የእሳት አደጋን ተከትሎ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ እንዳሰወቀው ቃጠሎው እንጀራ በሚጋገርበት ወቅት ከተቀጣጣይ ነገሮች የተነሳ መሆኑን በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ኅሣስ 14/2013ጅግጅጋ

የሶማሌ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ጅግጅጋ ከተማ ቀበሌ 02 በልዩ ስሙ ድብኡራሾ ሱቅ ተብሎ በሚታወቀው ቦታ መንስኤው አልታወቀም የተባለ የእሳት አደጋ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ተከስቶ ነበር።

ከአንድ ሱቅ እንደተነሳ በተገለጸው የእሳት አደጋ በሰው ህይወት ላይ ምንም አይነት ጉዳት ያላደረሰ ሲሆን በፍጥነት በተዛመተው እሳት ሰባት የንግድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ አድርሷል። በዚህም በድምሩ ወደ 1.2 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መውደሙ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

ታኅሣስ 14/2013መቅደላ ወረዳ

በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ አዲሱ መናኽሪያ ላይ ከምሽቱ 3፡30 ላይ በኤሌክትሪክ ምክንያት በተነሣ እሳት ሁለት የንግድ ቦታዎች በውስጣቸው ከነበረ ሙሉ ንብረት ጋር መውደማቸ ተገልጿል።

በቃጠሎውም የ23 ግለሰቦችና የተለያዩ ተቋማት ንብረት የሆኑ በጥቅሉ ከ1.2 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የወረዳው ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

በደቡብ ወሎ ዞን መቅደላ ወረዳ ማሻ ከተማ አዲሱ መናሃሪያ የደረሰ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Mekedela Woreda Communucation

ኅሣስ 18/2013 ሀላባ ዞን

በደቡብ ክልል በሀላባ ዞን ዌራ ወረዳ ላይኛ በደኔ ቀበሌ ላይ ውስጥ በተከሰተ የእሳት አደጋ 11 መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውን የወረዳው አስተዳደር አስታውቋል።

ለጊዜው ምክንያቱ ባልተወቀ ሁኔታ ከረፈዱ 5:00 ሰዓት አካባቢ የተነሳው ይህ የእሳት አደጋ ያደረሰው የንብረት ጉዳት ግምት አልተገለጸም።

ታኅሣስ 18 እና 19/2013ሀዲያ ዞ

በደቡብ ክልል በሀዲያ ዞን ሁለት ወረዳዎች ላይ ባልታወቀ ምክንያት በደረሰ የእሳት አደጋ 510 የቤተሰብ አባላት መፈናቀላቸውን የዞኑ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ገልጾ ነበር።

በወቅቱ እንደተነገረው በሀዲያ ዞን ምሻ ወረዳ በሦስት ቀበሌዎች ኤራ ጌሜዶ፣ ኩናፋ፣ ጉና ሜጋቾ እንዲሁም በሌሞ ወረዳ ኦሞ ሾራ አራት ቀበሌዎች በደረሰ እሳት አደጋ ሁለት ቆርቆሮና 45 የሳር ክዳን ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተገልጿል።

በአደጋው በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት ባይኖርም በርካታ ቁጥር ያላቸው በድምሩ ከ23 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።

በተጨማሪም በዞኑ ውስጥ በታኅሣስ ወር ብቻ በሆሳዕና ከተማ እና ወረዳዎች 15 ሱቆች 47 ቤቶች፣ በእሳት ተቃጥለው 33 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን ዞን ገልጿል።

ታኅሣስ 19/2013ምዕራብ ኦሞ ዞን

በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን ቤሮ ወረዳ ሾላ ቀበሌ ከቀኑ11፤00 ሰዓት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ586 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተገለጿል።

ከባድ ጉዳትን ባደረሰው በዚህ የእሳት አደጋ ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ 1ሺህ 840 መኖሪያ ቤቶችና 547 የንግድ ቤቶች እንዲሁም በወርቅ ሥራ የሚተዳደሩ 37 ማኅራት ንብረታቸ ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

በአደጋው 16 ሺህ 709 ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው በመፈናቀላቸው በሐይማኖት ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ቤት መጠለላቸው ተገልጿል።

ታኅሣስ 22/2013በደብረ ማርቆስ

በደብረማርቆስ ከተማ ቀበሌ 05 በተለምዶ ጉልት ገበያ ተብሎ በሚጠራ የገበያ ስፍራ የደረሰ የእሳት አደጋ ንብረት ሲያወድም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት አለመድረሱ ተገልጿል።

የእሳት አደጋው ሐሙስ ምሽት 3፡00 አካባቢ የተከሰተ ሲሆን ባደረሰው ጉዳት በገበያው የሚገኙ ሱቆችና ኮንቴይነሮች በአብዛኛው መውደማቸውን የተነገረ ሲሆን የእሳት አደጋው መንስኤ በመጣራት ላይ ይገኛል።