2012፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከጅማሬ እስከ ውሃ ሙሌት


የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters
በ2012 ዓ.ም ከፍተኛ ትኩረትን ከሳቡ ክስተቶች መካከል አንዱ የሆነው የታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት በአጭር ጊዜ ውስጥ መከናወኑ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ደስታንና ተስፋን ፈጥሯል።
አስር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በግንባታ ላይ የቆየው ውሃ መያዝ መጀመሩ ሱዳንና ግብጽን ቅር አሰኝቷል። የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የውሃ ሙሌቱ ደረጃ በደረጃ ተካሂዶ ኃይል ማመንጨት ሲጀምር በአፍሪካ ግዙፉ ይሆናል።
ግብጽ አሁንም ቢሆን የአባይን ውሃ በጋራ መጠቀም በሚለው ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ መስማማት ያቃታት ሲሆን ሁሉን አቀፍ ስምምነት መደረግ አለበት በማለት ስትከራከር ቆይታለች።
በ2003 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ግብጽ ተቃውሞዋንና ስጋቷን በተለያዩ መንገዶች ስትገልጽ እስከ ዛሬ ደርሳለች።
በዚህ ጊዜው ግብጽና ኢትዮጵያ ሱዳንን ጨምሮ ላለፉት አስር ዓመታት ያህል በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወሳኝ ክስተቶች የጊዜ ሰሌዳ
2003 መጋቢት፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በአባይ ወንዝ ላይ በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላሮች በማውጣት ሊገነባው ያሰበውንና በአፍሪካ ትልቁ እንደሚሆን የተነገረለትን የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድብ ይፋ አደረገ። ሚያዝያ ላይ የግድቡ ግንባታ ተጀመረ።
ግንቦት ወር ላይ ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ የቴክኒክ ኮሚቴ አዋቅረው ጥናት ማካሄድ ጀመሩ። መስከረም ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ግድቡ የግብጽን የውሃ ድርሻ የሚጎዳ አይደለም አለ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በግብጽ ጉብኝት ለማድረግ ካይሮ በገቡበት ወቅት ደግሞ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ ሁለቱንም አገራት ሊጠቅም እንደሚችል ተናገሩ።
2004 ግንቦት፡ ከሦስቱ አገራት የተወጣጣ የኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች አራት የውጭ አካላትን ያካተተው ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የግድቡን ተጽእኖ ማጥናት ጀመረ። በጥቅምት 2005 ላይ ቡድኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ግድቡ የሚገነባበትን ቦታ ሄዶ ጎበኘ። ከዚህ በኋላም ስፍራውን አራት ጊዜ ሄደው ጎብኝተዋል።
2005 ግንቦት፡ ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ አቅጣጫን ቀየረች። ሰኔ ላይ ደግሞ የባለሙያዎቹ ቡድን የመጨረሻ ሪፖርቱን አቀረበ። ኢትዮጵያና ግብጽም በሪፖርቱ አተረጓጎም ላይ መስማማት አልቻሉም።
የግብጹ ፕሬዝዳንት ሞሀመድ ሙርሲ በግድቡ ዙሪያ ጠንከር ያሉ ሀሳቦችን ማራመድ ጀመሩ። በተለያዩ አጋጣሚዎችም በቴሌቪዥን በሚያደርጓቸው ንግግሮችና ውይይቶች ላይ ኃይል መጠቀም የሚለውን ሀሳብ በተደጋጋሚ ያነሱ ነበር።
ግብጽ በተደጋጋሚ ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንደምትወስደው ብትናገርም ብዙም ሳይቀይ አገራቱ የባለሙያዎቹ ቡድን ያቀረበውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ፖለቲካዊና ቴክኒካዊ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።
በ2006 መስከረም ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት አጠቃላይ ስብሰባ በኒውዮርክ ሲካሄድ ሁለቱ አገራት ባደረጉት የጎንዮሽ ስብሰባ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።
በኅዳር እና በታህሳስ ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ካርቱም ላይ ተሰባስበው የባለሙያዎቹ ያቀረቡት ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ ውይይት አካሄዱ። ነገር ግን ስብሰባው ያለምንም ስምምነት ተጠናቀቀ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
2006 ጥር፡ የኢትዮጵያ፣ የግብጽና ሱዳን የውሃ ሚኒስትሮች ለሦስተኛ ጊዜ በካርቱም ተሰበሰቡ። በስብሰባውም በቀሪ ጉዳዮች ላይ መስማማት ስላልቻሉ ከዚህ በኋላ ስብሰባ ላለማድረግ ተስማሙ።
የካቲት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያና የግብጽ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ በአዲስ አበባ ቢሰበሰቡም ምንም አይነት ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችሉ ቀርተዋል። መጋቢት ወር ላይ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የግብጽን አቋም ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅና በጎኑ ለማሰለፍ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።
ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ ግብጽ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የጀመረቸውን ዘመቻ እንድታቆምና ወደ ሦስትዮሹ ድርድር እንድትመለስ ጥያቄዋን አቀረበች።
ሰኔ ወር ላይ የግብጹ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር በኢኳቶሪያል ጊኒ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ ላይ በተጓዳኝ ውይይት በማድረግ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በድጋሚ ሥራውን እንዲጀምር ተስማሙ።
በነሐሴ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውሃ ሚኒስትሮች በካርቱም ድርድራቸውን በድጋሚ ጀመሩ። በዚያውም በባለሙያዎቹ ቡድን ምክረ ሀሳብ መሰረት አገራቱ በገልተኛ ዓለም አቀፍ ድርጅት የሚመራና ከሦስቱ አገራት የተወጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።
2007 መስከረም ፡ የግብጽና የሱዳን ውሃ ሚኒስትሮች የግድቡን የግንባታ ሂደት ከጎበኙ በኋላ የሦስትዮሽ ኮሚቴው አባላት በአዲስ አበባ ውይይት አደረጉ። ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያካሂድ ገለልተኛ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅትን ለመምረጥ በካይሮ ስብሰባ አደረጉ።
2007 ጥር፡ ግብጽ የግድቡን 74 ቢሊየን ኪዪቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅምና የግድቡን ከፍታ አልቀበለውም አለች። መጋቢት ላይ ደግሞ ሦስተኛው ዙር የሦስትዮሽ ኮሚቴ ስብሰባ በሱዳኗ መዲና ካርቱም ተካሄደ።
በዚያውም ሦስቱ አገራት በመርህ ደረጃ በሚያስማሟቸው ጉዳዮች ላይ ተፈራረሙ። በተመሳሳይ ወርም የግብጹ ፕሬዝደንት በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ንግግር አደረጉ።
2007 ሚያዝያ፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በአዲስ አበባ በመገናኘት የግድቡን አጠቃላይ ጥናት የሚያከናውኑ ሁለት የአውሮፓ አማካሪዎችን መረጡ። ሐምሌ ወር ላይ ደግሞ የኮሚቴው አባላት በካይሮ ባደረጉት ስብሰባ የሁለቱ አማካሪዎች የመጀመሪያ ዙር ምክረ ሀሳብን ገመገሙ።
2008 ኅዳር፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ ተሰበሰበ። በዚህ ስብሰባ ላይም ሁለቱ የአውሮፓ አማካሪ ቢሮዎች መካከል አለመግባባት መፈጠሩ ተገለጸ። ታህሳስ ወር ደግሞ ኮሚቴው ካርቱም ላይ ተሰብስቦ የካርቱሙን ስምምነት ተፈራረመ። በስምምነቱ መሰረትም የግድቡን አጠቃላይ የጥናት ሥራ በአንድ ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅና ከማማመከሩ እራሱን ባገለለው ድርጅት ፈንታ አዲስ አማካሪ ለመምረጥ ተግባቡ።
2008 ጥር፡ የግብጽ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ውስጥ በመገናኘት የካርቱሙን ስምምነት ለማክበርና ከመግባባት ላይ ለመድረስ ተስማሙ።
የካቲት ወር ላይ ደግሞ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካርቱም በመሰብሰብ ግድቡ በግብጽና በሱዳን ላይ ስለሚኖረው ተጽእኖ በፈረንሳይ አማካሪ ድርጅት በተሰራው ጥናት ላይ በመወያየት ግምገማ አካሄደ።

የፎቶው ባለመብት, FBC
2009 መስከረም፡ ሦስቱም አገራት በዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን የቀረበውን ምክረ ሀሳብ ለማስፈጸም 'ቢአርኤልአይ' ከተባለው የፈረንሳይ ድርጅት ጋር ስምምነት ተፈራረሙ።
2009 የካቲት፡ ሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች የመጀመሪያ ዙር ሪፖርታቸውን በግድቡ ዙሪያ አቀረቡ። ሪፖርቱን ግብጽ ስትቀበለው ኢትዮጵያና ሱዳን ግን ውድቅ አደረጉት።
ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የግብጽ ፕሬዝዳንትና ኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። በዚያውም የግብጹ ፕሬዝዳንት ካርቱም ላይ የተፈረመውን ስምምነት ተግባራዊ በማድረግ የግድቡ ሙሌት ላይ ከስምምነት መድረስ እንደሚገባ ገለጹ።
2010 ጥቅምት፡ የሦስትዮሽ ኮሚቴው ካይሮ ውስጥ በመሰብሰብ በሁለቱ የፈረንሳይ አማካሪ ድርጅቶች በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ዙሪያ ምክክር አደረገ።
ሕዳር ወር ላይ ደግሞ በድጋሚ ኮሚቴው በካይሮ ቢሰበሰብም ምንም ስምምነት ላይ መድረስ ሳይቻል ቀረ። በዚያው ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብጽ ችግር እየፈጠረች ነው በማለት ከሰሰ።
2010 ጥር፡ የግብጹ ፕሬዝደንት ድርድሩ ተስፋ ሰጪ ነገር እየታየበት አለመሆኑ እንዳሳባቸው በመግለጽ የዓለም ባንክን በጉዳዩ ለማስገባት ሀሳባቸውን አቀረቡ። ነገር ግን ኢትዮጵያ የግብጽን ሀሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አደረገችው።
በዚያው ወር ላይ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ዓመታዊ የሦስትዮሽ ስብሰባ ለማካሄድና በአንድ ወር ውስጥ ከግድቡ ጋር በተያያዘ የመሰረት ልማት ፈንድ በማቋቋም የሦስቱንም አገራት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ኮሚቴ ለማቋቋም ተስማሙ።
ሚያዝያ ወር ላይ ደግሞ የሦስቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የውሃ ሚኒስትሮችና የደኅንንት ኃላፊዎች በካርቱም ተሰበሰቡ። ነገር ግን ስብሰባው ፍሬያማ ስምምነት ላይ መድረስ ሳይችል ተበተነ።
ግንቦት ወር ላይ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የውጭ ጉዳይ፣ የደህንንትና የውሃ ሚኒስትሮች በድጋሚ ስብሰባቸውን በአዲስ አበባ ላይ አደረጉ። ግብጽም ስብሰባው ስኬታማ እንደነበረ ገለጸች።
ሰኔ ወር ላይ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብጽን ሲጎበኙ በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው ግድብ የግብጽን የውሃ ድርሻ እንደማይጎዳ ተናገሩ።
2011 መስከረም ፡ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብጽ ስምምነቱን አልፈርምም አለች።
2011 ጥር፡ በሱዳን እየተካሄደ በነበረው ከፍተኛ ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ምክንያት የግድቡ ድርድር መቋረጡን ግብጽ አስታወቀች።
ሐምሌ ወር ላይ የግብጹ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካይሮ ውስጥ ተገናኙ። በዚያውም የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።
2012 መስከረም ፡ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድርድሩ መጓተት እንዳላስደሰተው አስታወቀ። ኢትዮጵያ ደግሞ ግብጽ ከግድቡ አሞላል ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ በድጋሚ ውድቅ አደረገችው። ግብጽ በበኩሏ ኢትዮጵያ ግድቡን ወደ ሥራ እንዳታስገባ አስጠነቀቀች።
ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ ዋይት ሐውስ ለመጀመሪያ ጊዜ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ መግለጫ አወጣ። ግብጽም በግድቡ ድርድር ላይ አሜሪካ እጇን እንድታስገባ ጥያቄዋን አቀረበች። ኢትዮጵያ ደግሞ የግብጽን ጥሪ ተቃወመች።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ማንኛውም አይነት ኃይል ኢትዮጵያን ግድቡን ከመገንባት እንደማያስቆማት ተናገሩ። ግብጽ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በመተቸት በአሜሪካ ዋሽንግተን ለመነጋገር የቀረበውን ሀሳብ እንደምትቀበለው ተናገረች።
ሁለቱ አገራት በሶቺ በተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመገናኘት የሦስትዮሽ ድርድሩን ለማስቀጠል ተስማሙ።
ኅዳር ላይ ደግሞ በአሜሪካ አደራዳሪነት አዲስ ውይይት ተጀመረ። የሦስቱ አገራት የውሃ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም በበዋሽንግተን ድርድራቸውን ካደረጉ በኋላ በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሁለተኛ ድርድራቸውን በአዲስ አበባ አካሄዱ።
ታህሳስ ወር ላይ የሦስትዮሽ ኮሚቴው በካይሮ፣ ዋሽንግተን እና ካርቱም በአሜሪካና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሦስት ስብሰባዎችን አካሄደ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ስብሰባው ውጤታማ እንደነበረና ግብጽም ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ ያቀረበችውን ሀሳብ እንደተወችው አስታወቀ። ነገር ግን ግብጽ አልተውኩትም በማለት አስተባበለች።

2012 ጥር፡ የአገራቱ የውጭ ጉዳይና የውሃ ሚኒስትሮች ዋሽንግተን ሁለት ጊዜ ሲገናኙ የውሃ ሚኒስትሮች ብቻ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ ተገናኝተዋል።
ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚሰራው ቡድን ደግሞ ካርቱም ውስጥ ተገናኘ። በዚህ ወቅት ከተደረሱ ስምምነቶች ዙሪያ ግብጽና ኢትዮጵያ እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መግለጫዎችን አወጡ።
ሕጋዊና ቴክኒካዊ ቡድኑ እንዲሁም የውሃና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በአሜሪካ ዋሽንግተን በተደጋጋሚ ተወያዩ። ነገር ግን የመጨረሻዎቹን ሁለት ስብሰባዎች ኢትዮጵያ አልተካፈለችም። ግብጽ ደግሞ ከግድቡ ሙሌት ጋር በተያያዘ በአሜሪካ አሸማጋይነት የቀረበውን ሀሳብ ተቀብላ ስምምነቱን ፈረመች።
መጋቢት ወር ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃላፊዎች በግድቡ ላይ የሚፈጸም ማንኛውም አይነት ጥቃትን ለመመከት ዝግጁ መሆናቸው አስታወቁ። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም አሜሪካ በድርድሩ ላይ ወደ አንድ ቡድን ያጋደለ አቋም እንዳረመደች በመግለጽ ቅሬታውን አቀረበ።
ግብጽ በበኩሏ ወደ አረብ አገራት በመሄድ አቋሟን እንዲረዱና እንዲደግፏት ዘመቻ አደረገች። ኢትዮጵያም በአረብ ሊግ የቀረበውን ሀሳብ አልቀበለውም አለች።
ግንቦት ላይ ደግሞ የግድቡን ሙሌት የተመለከተውን በኢትዮጵያ የቀረበውን ሀሳብ ግብጽ አልቀበለውም እንደማትቀበለው አሳወቀች። ኢትዮጵያ ደግሞ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅና የውሃ ሙሌት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን የግብጽን ይሁንታ እንደማትፈል በመግለጽ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈች።
ግብጽ ደግሞ ቀደም ብላ ሁለቱ አገራት ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ ግድቡን የመሙላት ሥራውን እንዳትጀምር ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብታ ነበር። የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ ሁለቱ አገራት አለመግባባታቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱት ሀሳቡን አቅርቧል።
ሰኔ ወር ላይ ሱዳን ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በጻፈችው ደብዳቤ ሁለቱ አገራት ውይይት ሳይካሄድ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳያስተላልፉ ስትል ጠየቀች።
በጉዳዩ ላይ የማሸማገል ሥራ ለመስራት ሩሲያ ሀሳብ አቅርባ ነበር። የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን አምስት ተከታታይ ድርድሮችን አካሄዱ። ግብጽ ድርድሩ ተስፋ ሰጪ አይደለም ስትል ኢትዮጵያ በበኩሏ ድርድሩ ውጤታማ የማይሆነው በግብጽ ምክንያት ነው ስትል ከሳለች።
ሰኔ 26 ላይ ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሰብሳቢ ሲሪል ራማፎሳ ከሦስቱ አገራት መሪዎች ጋር በቨዲዮ ኮንፈረንስ ተገናኘተው ተወያዩ።
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታትም ስምምነት ላይ ለመድረስ የተስማሙ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ግን የግድቡ የመጀመሪያ ዙር ሙሌት በተከታይነት በነበሩት ሳምንታት እንደምትጀምር በመግለጽ የግድቡን ሥራ ለማከናወን አገራትን መለመን እንደበቃት አስታወቀች።
ሐምሌ ላይ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ወታደራዊ አማራጭ እንደማከተሉ ገለጸ። በአፍሪካ ሕብረት አስተባባሪነት ሦስቱንም አገራት በማሳተፍ የተካሄደውም ድርድር ያለምንም ስምምነት ተጠናቀቀ።
ተከትሎም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት መጀመሩን ይፋ ማድረግ ጀመሩ። የአረብ አገራት ሚዲያዎችም ዜናውን ተቀባበሉት። ግብጽ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጣት የኢትዮጵያን መንግሥት ጠየቀች። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ መረጃውን ቀድሞ ይፋ ያደረገው የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዜናውን ከገጹ ላይ አነሳ።
ሱዳን በበኩሏ የሙሌት ስራው ተጀመረ ከተባለ በኋላ የ90 ኪዩቢክ ሜትር ቅናሽ ማየቷን አስታወቀች።

















