የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ተፈጥሯዊ የውሃ ሙሌት ሂደትን ማስቆም ይቻላል?

ከሰሞኑ የወጡ የሳተላይት ምስሎች በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጥ ያለው የውሃ መጠን መጨመሩን ማመልከታቸውን ተከትሎ የግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውሃ ሙሌት ተጀምሯል የሚሉ መረጃዎች መውጣት ጀምረዋል።
የግድቡ ሙሌት በይፋ አለመጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የገለፁ ቢሆንም እየጣለ ባለው ከፍተኛ ዝናብ ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመሩን አስረድተዋል።
የሳተላይት ምስሎቹ ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ መጨመሩን የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልፀው፤ ባለፈው ዓመት ውሃው ያልፍ የነበረው በ520 ሜትር ከፍታ ላይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 560 ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ከ560 ሜትር ከፍታ በታች ያለው ውሃ ግድቡ ውስጥ የሚቀር እንደሆነም አስረድተዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በግድቡ ዲዛይንና ባለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት የውሃ ሙሌቱ በይፋ መንግሥት ጀምሬዋለሁ ባይልም ግድቡ ውሃ መያዙንም ሚኒስትሩ አሳውቀዋል።
ሚኒስትሩም ለፋይናንሻል ታይምስ በሰጡት ቃለ መጠይቅም "የዝናብ ወቅት እንደመሆኑ መጠን ግድቡ ውሃ ይዟል። ይሄ በሁሉም አካላት ዘንድ የሚታወቅ ነው፤ ግብጾችም ያውቁታል። ለሕዝባቸው መንገር አለባቸው" ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ ያዘ ሲባል ምን ማለት ነው? የውሃ ሙሌት በይፋ ተጀረ ሲባል እንዴት ይገለፃል? የሚለውን ለማብራራት ቢቢሲ በውሃ ምህንድስናና በግድብ ግንባታ ዘርፍ የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች አነጋግሯል።

የህዳሴው ግድብ ግንባታ ባህሪይ
የግንባታውን ሂደት ከመነሻው አንስቶ በቅርበት የሚያውቁና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ኢትዮጵያዊ የዘርፉ ባለሙያ ሲያስረዱ ግድቡ ውሃ ያዘ ወይም ሙሌት ተጀመረ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ለመረዳት የህዳሴው ግድብ አገነባብን መረዳት እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ግድቡ የተሰራው ሸለቆ ውስጥ በመሆኑ ኢትዮጵያ ግድቡን ለመሙላት የምትዘጋውም ሆነ የምትከፍተው ነገር እንደሌለ በቀዳሚነት በማስረዳት የተፈጥሮ አካበቢው ለዚሁ ተብሎ የተመረጠ መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም ሆኑ ሚኒስትሩ ዶ/ር ስለሺ በተደጋጋሚ ሲናገሩት እንደነበረው በዚህ ዓመት ግድቡ 25 ሜትር የነበረው ከፍታው ወደ 60 አድጓል። በዚህም የተነሳ ከዚህ ቀደም በግድቡ አናት ላይ ይፈስ የነበረውን የክረምት ውሃ ማጠራቀም ጀምሯል ሲሉ ተደምጠዋል።
እንደ እኚህ ባለሙያ ማብራሪያ ከሆነም በክረምት ዝናብ ምክንያት ወደ ውሃ ማጠራቀሚያው የገባው ውሃ የሚወጣበት እድልም የለውም።
ለዚህ የግድቡ ማዕከላዊ ክፍል ከላይ የክረምት ውሃ ማሳለፍ እንዲችል በበጋ ደግሞ በዚሁ ማዕከላዊ ክፍል ያለምንም ችግር ማሳለፍ እንዲችል ተደርገው የተሰሩ መዋቅሮች ( ስትራክቸሮች) እንዳለውም ይጠቅሳሉ።
ይህ በበጋ ውሃውን ለማሳለፍ የሚያስችለው ክፍል በህዳሴው ግድብ ላይ አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት መሆኑንም ከተመለከቷቸው የግድቡ ዲዛይንና ምስሎች እንደሚረዱ ባለሙያው ያብራራሉ።
በክረምት ወቅት ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ እና የሚወጣው ስለማይመጣጠን በክረምት እንዲጠራቀምም ተደርጎ ዲዛይን መደረጉንም በማመልከት ውሃው ግድቡ ላይ እንዳይፈስ ማዕከላዊው የግድቡ ክፍል ዝቅ ተደርጎ ነው የተሰራው።
ክረምት ሲመጣ ከስር ለማሳለፍ ተብለው በተሰሩት መዋቅሮች እየፈሰሰ ይሄድና ከማስተንፈሻው አቅም በላይ ሲሆን ደግሞ በዚህ በ25 ሜትር ከፍታ ላይ ይፈሳል። ኢትዮጵያ በዚህኛው የበጋ ወራት ይኸኛውን 25 ሜትር የነበረውን ከፍታ ወደ 60 ሜትር ከፍ እንዳደረገችው ያስረዳሉ።
[በምስሉ ላይ ያለውን ቀስት ወደ ግራና ወደ ቀኝ በማንቀሳቀስ በግድቡ አካባቢ በተለያዩ ቀናት የታውን የውሃ ልዩነት ይመልከቱ]
በቀላል አገላለጽ በበጋው ወቅት በማስተንፈሻው በኩል ያልፍ የነበረው ውሃ በክረምት ወቅት መጠኑ ከፍተኛ ስለሚሆን ማለፍ አይችልም። ስለዚህ ተወደደም ተጠላ ውሃ እየተጠራቀመ 60 ሜትር ከፍታ ላይ ሲደርስ በግድቡ ላይ ይፈሳል። እስከዚያ ድረስ ግን የትም መሄጃ ስለሌለው ውሃው ይጠራቀማል።
የግድቡን ግንባታ ካላቸው ሙያና ከተለያዩ ምንጮች በቅርበት የሚከታተሉት የውሃ ምህንድስና ባለሙያው እንደሚሉት አሁን ባለው ሁኔታ የሚከፈት ወይም የሚዘጋ ነገር አለመኖሩን ደግመው ያረጋግጣሉ።
በአተጠቃላይ የታላቁ የህዳሴ ግድብ አገነባብ ውሃው እንዲጠራቀምም እንደሚያስገድደው በመሆኑ አሁን እታየ ያለው የውሃ ክምችት ከፍተኛ ዝናብ እጣለ በመሆኑ በዚህ ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ።
ባለሙያው ሲያጠቃልሉ "ይህ ማንም የሚቆጣጠረው አይደለም፤ ስለዚህ በጋ ሲሆንና የውሃው መጠን ሲቀንስ የግድቡ ማዕከላዊ ክፍል በግንባታ ምክንያት ውሃ እንደ ቀድሞው በማስተንፈሻው በኩል ያልፋል ማለት ነው" ብለዋል።
ተፈጥሯዊ የውሃ ሙሌት
በግድቡ በስተጀርባ ባለው የውሃ ማጠራቀሚያ ሰፊ ስፍራ ላይ ከሰኔ ጀምሮ እስከ መስከረም ድረስ በሚቆየው የዝናብ ወቅት ላይ በተፈጥሯዊ ሁኔታ ውሃ መጠራቀም ይጀምራል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ አንስቶ በቅርብ ሲከታተሉ የቆዩት ዶክትር ኬቭን ዊለር እንደሚሉት አሁን ግድቡ ከደረሰበት የግንባታ ደረጃ አንጻር "የግድቡን ዝቅተኛ የውሃ መያዣ ክፍልን ውሃ እንዳይዝ የሚያደርግ አንዳችም ነገር የለም" ሲሉ የግንባታው ሂደት ውሃ ለማቀብ መድረሱን ይገልጻሉ።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ከዘጠኝ ዓመት በፊት አንስቶ ግዙፍ የግንባታ ሥራ እየተከናወኑ የአባይ ወንዝ ውሃ ያለችግር ሲከናወን የቆየ ሲሆን፤ በበጋ ወቅት ደግሞ የውሃው መስመር በሌላ በኩል እንዲያልፍ ተደርጎ ቀሪው ክፍል እንዲገነባ ተደርጓል።
በአሁኑ ጊዜ የግድቡ ማዕከላዊ ክፍል የታችኛው አካል ተገንብቶ በማለቁ ውሃው በግድቡ ግድግዳ ላይ ባሉ የውሃ ማስተላለፊያዎች በኩል እንዲፈስ እየተደረገ ነው።
ከፍተኛ ዝናብ የሚጥልበት በአሁኑ የክረምት ወቅት ላይ ከፍተኛ መጠን ያለው ውሃ ወደ ግድቡ ስለሚገባ ውሃው በግዙፎቹ የግድቡ የማስተላለፊያ ቦዮች በኩል መፍሰስ ከሚችለው አቅም በላይ ይሆናል።
ይህም ማለት በግድቡ በኩል አልፎ ከሚፈሰው ውሃ በተጨማሪ ከፍተኛ መጠን ያከለው ከግድቡ ጀርባ ባለው ውሃ እንዲያርፍበት በተዘጋጀው ሰፊ ቦታ ላይ በመጠራቀም ሐይቅ መፍጠር ይጀምራል ሰሉ ዶክተር ዊለር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ጨምረውም ኢትዮጵያ በውሃ ማጠራቀሚው ቦታ ላይ የሚያርፈውን የውሃ መጠን መጨመር ከፈለገች በግድቡ ላይ ያሉትን የውሃ ማፍሰሻ መተላለፊያዎችን መዝጋት ትችላልች። ነገር ግን ይህ አስፈላጊ ላይሆን ይችላል ሲሉ ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድብ ቀጣይ ደረጃ
የአባይ ወንዝ ዓመታዊ አማካይ የውሃ ፍሰት 49 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ዓመት የውሃ ሙሌት ታላቁ የህዳሴ ግድብ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በመያዝ የግድቡ ዝቅተኛው ውሃ መያዝ ደረጃ ድረስ ውሃ ለማቀብ ይችላል። ይህም ኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖችን እንድትሞከር ያስችላታል።
በቀጣዩ የበጋ ወቅት ከግድቡ ጀርባ የተጠራቀመው ውሃ ስለሚቀንስ የግድቡን ቁመት መጠን ለመጨመር የሚደረገው ግንባታ እንዲቀጥል ዕድል ስለሚሰጥ ሥራውን በማከናወን በሁለተኛው ዓመት ደግሞ 13 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ እንዲይዝ ይደረጋል ይላሉ ባለሙያው።
በዚህ ጊዜም በግድቡ አማካይነት የሚታቀበው የውሃ መጠን በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተገነቡትን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ተርባይኖች ጋር ይደርሳል። ይህ ደግሞ የውሃውን ፍሰት በበለጠ ለመቆጠጠር ያስችላል።
ኢትዮጵያ እንዳለችው የግድቡ ከፍተኛ አቅም የሆነውንና አስፈላጊውን የ74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ በግድቡ ውስጥ ለመያዝ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት ያስፈልጋል።
ግድቡ በሚጠበቀው መጠን በውሃ ተሞልቶ ሲያበቃ በተጠራቀመው ውሃ የሚፈጠረው ሐይቅ 250 ኪሎ ሜትሮችን የሚያካልል ቦታን በውሃ ይሸፍናል።
ግድቡ ተጠናቆ ሥራ ሲጀመር በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ግድብ ሲሆን በዓለም ካሉ 10 ግዙፍ ተመሳሳይ ግድቦች መካከልም ይመደባል።
ያልተቋጨው ውዝግብ
ለአስር ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት እተገነባ ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታው ከሦስት አራተኛው በላይ ጠተናቋል።
ቢሆንም ግን በግድቡ ዙሪያ በተነሱ ሕጋዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ለዓመታት ስታካሂዳቸው የነበሩት ድርድሮች እስካሁን መቋጫ አላኙም።
ኢትዮጵያ ከአገራቱ ጋር ከስምምነት ለመድረስ ፍላጎት እንዳላት በተደጋጋሚ የገለጸች ሲሆን፤ ቢሆንም ግን በድርድሮቹ የሚገኘው ውጤት ግድቡን ውሃ ከመያዝና ሥራውን ከማስጀመር እንደማያግዳት በተደጋጋሚ አሳውቃለች።
ሱዳንና ግብጽ በበኩላቸው ግድቡ ከሚያገኙት ዓመታዊ የውሃ መጠን ላይ መቀነስን ስለሚያስከትል ከስምምነት ከመደረሱ በፊት የውሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ሲወተወቱ ቆይተዋል።
ኢትዯጵያ የግድሙን ሙሌት ገና እንዳልጀመረች ያሳወቀች ሲሆን ከሰኔ ወር ጀምሮ በአገሪቱ እጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የግድቡ የውሃ ማተራቀሚያ ክፍል ላይ መጠኑ እጨመረ የሚሄድ የውሃ መጠን መታቱ ሱዳንና ግብጽን ሳያሳስባቸው አልቀረም።
ይህንን በተመለከተም ግብጽ ኢትዮጵያ መንግሥት በግድቡ የውሃ አያያዝ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጣት ጠይቃለች።
















