የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በይፋ እንዳልተጀመረ ተገለፀ

የሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌትን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውሃ ሙሌት መጀመሩን የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ማስታወቁን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የዘገቡ ቢሆንም በይፋ አለመጀመሩን ሚኒስትሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩን ዶ/ር ስለሺ በቀለን ዋቢ አድርገው የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እንደዘገቡት የውሃ ሙሌቱ የግድቡን ተፈጥሯዊ የግንባታ ሂደት በጠበቀ መልኩ እየተከናወነ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሰሞኑ በሕዳሴው ግድብ አካባቢ የተገኙት የሳተላይት ምስሎች በግድቡ ውስጥ ያለው የውሃ መጠን እየጨመረ መሆኑን ያመላከቱ ሲሆን፣ ይህም ምስል ትክክለኛ መሆኑንና የግድቡ ሙሌት መጀመሩን የሚያሳይ መሆኑ ሚኒስትሩ መግለፃቸው ተዘግቧል።

የግድቡ ሙሌት መጀመሩን አስመልክቶ ሚኒስትሩ ለቢቢሲ በሰጡት ምላሽ ዘገባው "በስህተት የወጣ ነው፤ የራስ ትርጉም ተጨምሮበታል። ግድቡ ግንባታው አሁን የደረሰበት ደርሷል፤ ግድቡ ውሃ ይይዛል እንጂ በይፋ የተጀመረ ነገር የለም" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ሚኒስትሩ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገሩት እነዚህ የሳተላይት ምስሎች የሚያሳዩት ከፍተኛ ዝናብ መኖሩንና ከግድቡ ከሚወጣው ይልቅ ግድቡ ውስጥ የሚገባው መጨመሩን ነው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ዶ/ር ስለሺ ለቢቢሲ እንደገለጹት ባለፈው ዓመት ውሃው ያልፍ የነበረው በ520 ከፍታ ላይ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት 560 ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ከ560 ከፍታ በታች ያለው ውሃ ግድቡ ውስጥ የሚቀር እንደሆነና ሙሌቱም ከግንባታው ሂደት ጋር የማይነጣጠል ነው ማለታቸውንም የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ስምምነት ባይደረስም ግድቡን መሙላት እንደምትጀምር ማስታወቋ ይታወሳል፤ ከዚህ አንጻር ይህ ስምምነት ሳይደረስ የውሃ ሙሌቱ ትጀምር እንደሆነ ከቢቢሲ ለተጠየቁት ሚኒስትሩ "አሁን የምሰጠው ነገር የለም፤ ጊዜው ሲደርስ ይታያል" ሲሉ መልሰዋል።

ዶ/ር ስለሺ አክለውም በሦስቱ አገራት መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር በቀጣይነት እንደሚካሄድ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን በትናንትናው ዕለት በትዊተር ገፃቸው ያስታወቁት ሚኒስትሩ "ድርድሩ የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ትውልድ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልክ የሚደረግ ነው" ማለታቸውንም ዘገባው አስፍሯል።

ሦስቱ አገራት 11 ታዛቢዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ለአስራ አንድ ቀናት ያህል ውይይት ያደረጉ ሲሆን እስካሁን በተካሄደው ድርድር መሻሻሎች እንዳሉ ተጠቅሶ በአጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በትናንትናው ዕለትም አገራቱ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመሪዎቹ እንዲሁም ሲያሸማግል ለነበረው አፍሪካ ህብረትም በሪፖርት መልክ እንደሚያቀርቡም ሚኒስትሩ በትዊተር ባሰራጩት መልዕክት አስፍረዋል።

የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን ጨምሮ አባለት አገራቱና የሦስቱ አገራት መሪዎች ሪፖርቱን ከገመገሙ በኋላም ድርድሩ ሊቀጥል እንደሚችል በፅሁፉ ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ እነዚህ አካላት በሚሰጡት መመሪያም መሰረት ይሆናል ሲል ጨምሮ ገልጿል።

ለዓመታት የዘለቀው የሦስቱ አገራት ድርድር ያለምንም ውጤት ሲንከባለል መጥቶ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ሙሌትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እጀምራለሁ ማለቷን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ግብፅ መጠየቋ የሚታወስ ነው።

ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መደረጉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተባለ ሲሆን የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ፣ የድርቅ የውሃ ስሌት፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የግድቡ ደኅንነት ጉዳዮችን በተመለከተም የአገራቱ ቴክኒክና ሕግ ባለሙያዎች እየተወያዩ ነበር ተብሏል።