በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሲካሄድ የነበረው የህዳሴ ግድብ ድርድር ያለስምምነት ተቋጨ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
በአፍሪካ ህብረት አሸማጋይነት ሲካሄድ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ስለሺ በቀለ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ሶስቱ ሃገራት፣ 11 ታዛቢዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ለአስራ አንድ ቀናት ያህልም ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰው ትናንት ምሽት ሶስት ሰአት ላይ መጠናቀቁም ሰፍሯል።
እስካሁን በተካሄደው ድርድር መሻሻሎች ቢኖሩም በአጠቃላይ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለ የገለፀው የትዊተር ፅሁፉ በዛሬው ዕለትም አገራቱ የደረሱባቸውን ጉዳዮች ለመሪዎቹ እንዲሁም ሲያሸማግል ለነበረው አፍሪካ ህብረትም በሪፖርት መልክ ያቀርባሉ።
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርን ጨምሮ አባለት አገራቱና የሶስቱ አገራት መሪዎች ሪፖርቱን ከገመገሙ በኋላም ድርድሩ ሊቀጥል እንደሚችል በፅሁፉ ላይ የሰፈረ ሲሆን፤ እነዚህ አካላት በሚሰጡት መመሪያም መሰረት ይሆናል ሲል ጨምሮ ገልጿል።
ለአመታት የዘለቀው የሶስቱ አገራት ድርድር ያለምንም ውጤት ሲንከባለል መጥቶ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሙሌትን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እጀምራለሁ ማለቷን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ግብፅ መጠየቋ የሚታወስ ነው።
ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር መደረጉ ለኢትዮጵያ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የተባለ ሲሆን የግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቅ፣ የድርቅ የውሃ ስሌት፣ የግድቡ አስተዳደርና ቁጥጥር፣ የግድቡ ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተም የአገራቱ ቴክኒክና ህግ ባለሙያዎች እየተወያዩ ነበር ተብሏል።
በአስረኛው ቀንም የሶስቱ አገራት የውሃና መስኖ ሚኒስትር የቴክኒካልና ህጋዊ ኮሚቴ ውይይቶችን መገምገማቸውንም የግብፅ የውሃና መስኖ ሚኒስቴርን ጠቅሶ 'ኢጅፕት ቱደይ' ዘግቧል።
በተለይም በባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ስምምነት ያልተደረሳባቸው ጉዳዮች ለሌላ ጊዜ ይተላለፉ ማለታቸው ከግብፅ በኩል ተቀባይነት አለማግኘቱንም ዘገባው አስነብቧል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ከሰሞኑ ለአገሪቱ ሚዲያዎች በሰጠው መግለጫ ድርድሩ ፍሬ አልባ እንደነበር ገልጿል።
አረብ ኒውስ በበኩሉ ኢትዮጵያ ለአወዛጋቢዎቹ የህግ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች አማራጭ ሃሳቦችን ብታቀርብም በግብፅ ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ ዘግቧል። ኢትዮጵያ የአማራጭ ሃሳቧን በስምንተኛው የድርድር ቀን ማቅረቧን የገለፀው ዘገባው ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮችንና ስምምነቶቹ ተግባራዊ መሆናቸውንም ለማየት አንድ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደዛ እንዲመራ ማሰቧን ዘግቧል።
ግብፅ በበኩሏ ድርቅና የድርቅ ውሃ ስሌትን በተመለከተ አማራጭ ሃሳብ ማቅረቧን የውሃና መስኖ ሚኒስትሩን ጠቅሶ ዘግቧል። ቴክኒካል ጉዳዮችንም በተመለከተ አንዳንድ መሻሻሎች መኖራቸውንም የሱዳን የውሃና መስኖ ሚኒስቴርን ዋቢ በማድረግ ዘገባው አስነብቧል።














