ኮሮናቫይረስ፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት

የፎቶው ባለመብት, GRAND ETHIOPIAN RENAISSANCE DAM
ከሰሞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በሚከናወንበት ጉባ ወረዳ አንድ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱን የጤና ሚንስቴር እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባወጡት ዕለታዊ መግለጫ ላይ ማስታወቃቸው ተሰምቷል።
የግድቡ ግንባታ በሚካሄድበት ወረዳ ውስጥ በበሽታ የተያዘ ሰው መገኘት በግንባታው ላይ ምን አይነት ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል? ሠራተኞቹስ በምን አይነት ስሜት ውስጥ ይገኛሉ የሚሉ ጥያቄዎችን አጭሮ ነበር።
ከ7000 በላይ ሰራተኞች ያሉት የአፍሪካ ግዙፉ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ሊያስከትልበት የሚችለውን ጫና ለመቋቋም ምን እየተደረገ ነው ስንል የፕሮጀክቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆሮን አነጋግረናል።
"ፕሮጀክቱ ምንም እንኳ ከጉባ ወረዳ ቢገኝም፤ በቫይረሱ መያዙ በምርመራ የተረጋገጠው ግለሰብ የሚኖርበት ቦታ እና ፕሮጀክቱ ያለበት ስፍራ ይራራቃሉ" ይላሉ።
የጉባ ወረዳ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች ሰፊው መሆኑን ያስታወሱት ኢንጅነር ክፍሌ፤ "በቫይረሱ የተያዘው ሰው የተገኘበት ፓዊ በሚባል በቫይረሱ ተጠርጥረው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ካሉ ሰዎች መካከል ነው። በዛ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ደግሞ ከሱዳን የሚመጡ ሰዎች ተለይተው የሚቆዩበት ቦታ ነው። ከፕሮጀክታችን ጋር አይገናኘም" ብለዋል።
ከኮሮናቫይረስ ስርጭት በኋላ በግንባታ ሂደቱ ላይ ምን ተቀየረ?
የኮሮናቫይረስን ወረርሽኝ ተከትሎ አሰሪዎች ሰራተኞቻቸው ርቀታቸውን ጠብቀው በጥንቃቄ እንዲሰሩ አልያም ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ ትዕዛዝ ሲያስተላልፉ ታይተዋል።
በርቀት ሆኖ ሥራን ማከናወን ከማይቻልባቸው መካከል አንዱ የግንባታ ሥራ ነው የሚሉት ኢንጅነር ክፍሌ፤ "ጥንቃቄን በማጠናከር ከመስራት ውጪ ሠራተኞችን መቀነስ ወይም ከርቀት ሆነው እንዲሰሩ ማድረግ አልቻልንም" ይላሉ።
"ሠራተኞች በሥራ ቦታ ላይ ርቀታቸውን እና ንጽህናቸውን ይጠበቃሉ። የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭንብል እያደረጉ ነው" ብለዋል።
"እንደ ከዚህ ቀደሙ የፕሮጀክት ግንባታ ጉብኝት እንዲቆም ተደርጓል። እንዳጋጣሚ ወደ ፕሮጀክቱ የሚገባ ካለ ለ14 ቀን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ ተደርጎ እና ከክትትል በኋላ ነው ከሠራተኞች ጋር የሚቀላቀለው" ይላሉ የፕሮጅክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ።
ኢንጀነር ክፍሌ እንደሚሉት ሌላው ስጋት ሊፈጥሩ የሚችሉት የግንባታ ግብዓቶችን ጭነው የሚመጡ መኪኖች ናቸው። እንደ ኢንጂነሩ ገለጻ ከሆነ ተሽከርካሪዎቾ ወደ ግንባታው ከመቃረባቸው በፊት በጸረ-ተዋሲያን እንዲጸዱ ይደረጋሉ። ሠራተኞቹም ቢሆኑ ከአሽርከርካሪዎቹ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳይኖራቸው ይደረጋል።
ለቻይኖች አዲስ ዓመት በዓል የፕሮጀክቱ ሠራተኞች የነበሩ ቻይናውያን ወደ አገራቸው ተጉዘው እንደነበረ ያስታወሱት ኢንጅነር ክፍሌ፤ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በአዲስ አበባ ለ14 ቀናት በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ መቆየታቸውን እና ወደ ፕሮጀክቱ ሥፍራ በልዩ አውሮፕላን እንደተመለሱ፤ በግድቡ ግንባታም ክትትል ከተደረገላቸው በኋላ ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን ተናግረዋል።
ከቻይናውያን በተጨማሪ በህዳሴ ግድብ ላይ ተሳትፎ የሚያደርጉ የጣሊያን፣ ጃፓን እና ጀርመን ዜጎች እንዳሉ ይታወቃል።
ኢንጅነር ክፍሌ የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች ሆነው ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ የውጪ አገር ዜጎች እንደሌሉ ተናግረዋል።
ኮሮናቫይረስ በፕሮጀክቱ ውስጥ ቢከሰት ዝግጅቱ ምን ይመሥላል?
መንግሥት ለዚህ ፕሮጅከት ከፍተኛ ትኩርት ሰጥቷል ያሉት ኢንጅነር ክፍሌ፤ "በጥበቃ ረገድም ተጨማሪ የጸጥታ ኃይል ተመድቦ የደህንነት ስራውን በቅርበት እያከናወኑ ይገኛሉ። የጤና ሚንስቴር እና አሶሳ የሚገኘው ማዕከል ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል" ብለዋል።
በሽታው እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ሠራዎች መሠራታቸውን ቀጥለዋል ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ "ድንገት ኮሮናቫይረስ ቢከሰት እንኳ እዚህ ያዘጋጀነውን የህክምና ማዕከል እና በአሶሳ ያለው ለመጠቀም ከስምምነት ላይ ደርሰናል" ብለዋል።

















