የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መቼ ይቆማል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በየአገራቱ ለወትሮ የሰው ግርግር የሚያደምቃቸው ከተሞችና ቦታዎች የኮሮናቫይረስ መምጣትን ተከትሎ ሁሉም ነገር ፀጥ ረጭ ብሏል።
ትምህርት፣ ስራና ሌሎችም እንቅስቃሴዎች ሲቆሙ የጉዞ እገዳዎችም ተጥለዋል። ስብሰባም ሆነ ሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮች እንዳይደረጉ ታግደዋል።
መንገዶች፣ ካፍቴሪያዎች እንዲሁም የገበያ ስፍራዎች ፀጥ ብለዋል፤ ከተሞች ኦና ሆነዋል በጥቅሉ ዓለም ተዘግታለች ማለት ይቻላል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቆሞ ህይወት ወደነበረበት የሚመለሰው መቼ ነው? ብዙዎች በአእምሯቸው የሚያውጠነጥኑት ነገር ነው።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እንግሊዝ በሶስት ወራት ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት ትገታለች ብለዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ቢቻልም ግን የቫይረሱ ማብቂያ ገና እንደሆነ ተናግረዋል።
ወረርሽኙን ማስቆም ረዥም ጊዜ ምናልባትም ዓመታት ሊወስድ ይችላል ሲሉም ፍርሃታቸውን ገልፀዋል።
የማህበረሰቡን እንቅስቃሴዎች መግታትና እገዳዎችን መጣል ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን አይችለም። እገዳዎቹን ዘላቂ ለማድረግ መሞከር ደግሞ ከባድ፣ የረዥም ጊዜ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስን ይፈጥራል።
አገራት የሚያስፈልጋቸው የጣሉትን እገዳ ማንሳት የሚያስችላቸውን ስትራቴጂ መንደፍና የሰዎች ኑሮን ወደ ነበረበት እንዲመለስ ማድረግ እንደሆነ እየተገለፀ ነው።
ምክንያቱም ኮሮናቫይረስ በዚህ ጊዜ ይጠፋል የሚባል አይደለም።
ግን ደግሞ ምን ዓይነት ስትራቴጂ እገዳዎችን ማስነሳት ይችላል? የሚለው አሁንም የአገራት ራስ ምታት ነው።
እገዳውን ማስቀጠልም ማንሳትም የሚያስከትሉት ቀውስ ፈርጀ ብዙ ነው።
በኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ውልሃውስ "በምን ዓይነት ስትራቴጂ ከዚህ እንወጣለን? እንዴት? የሚለው ትልቁ ችግራችን ነው" ይላሉ።
አክለውም "እንግሊዝ ብቻም ሳትሆን ማንም አገር ከዚህ ቀውስ መውጫ ስትራቴጂ የለውም" ብለዋል።
ይህ በእጅጉ የገዘፈ ማህበራዊና ሳይንሳዊ ፈተና ነው ይላሉ።
ከኮሮናቫይረስ ቀውስ መውጫ ሶስት መንገዶች
ክትባት፣ በቂ የሚባሉ ሰዎች ቫይረሱን መቋቋም የመቻል ተፈጥሯዊ መከላከያ ማዳበርና በዘላቂነት የግለሰቦችና የማህበረሰብ ባህሪ መቀየር እንደ አማራጭ የተቀመጡ ነገሮች ናቸው።
ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባት ላይ ለመድረስ ቢያንስ ከአመት እስከ ዓመት ተኩል የሚሆን ጊዜ ይቀረዋል።
ክትባቱ ቢያንስ 60 በመቶ ለሚሆኑ ሰዎች ተሰጥቶ እነዚህ ሰዎች ቫይረሱን የመከላከል አቅም አዳብረው ለቫይረሱ ተጋልጠው እንኳ የማይታመሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።
የዚህ ክትባት ሙከራ በአሜሪካ ሰው ላይ ባለፈው ሳምንት ተሞክሯል።
ከጊዜ ጋር እየተደረገ ባለው ሩጫ ምክንያት ክትባቱ በመጀመሪያ እንስሳት ላይ መሞከር የሚባውን መደበኛ አሰራር ሳይጠብቅ በቀጥታ የሰው ልጅ ላይ እንዲሞከር ተደርጓል።

የኤደንብራው ፕሮፌሰር ውልሃውስ ክትባቱን መጠበቅን አገራት እንደ ስትራቴጂ ሊመለከቱት አይገባም ብለዋል።
ተፈጥሯዊ በሽታውን የመቋቋም አቅምን ማዳበርም ቢያንስ ሁለት ዓመት የሚወስድ ጊዜ ነው እየተባለ ነው።
የእንግሊዝ መንግሥት የአጭር ጊዜ ስትራቴጂ ያለው ነገር ቢኖር ሆስፒታሎች እንዳይጨናነቁ ማድረግ ሲሆን ይህ ደግሞ የኮሮናቫይረስ ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይጨምር ይረዳል ተብሏል።
በሌላ በኩል የእንግሊዙ ቁጥር አንድ ሳይንቲስት ሰር ፓትሪክ ቫላንስ ጊዜው በአሁኑ ወቅት ይህን አሁን ብናደርግ በዚህ ጊዜ ያንን እናሳካለን የሚባልበት ወቅት እንዳልሆነ ገልፀዋል።
የዚህ ዓይነቱ ክትባት ውጤትም ቢገኝም ያልተጠበቁ ሌሎች ኮሮናቫይረሶችን የማስከተል እድልም እንዳለው ሳይንቲስቶች እየገለፁ ነው። ለምሳሌ እንደ መደበኛ ጉንፋን ምልክት ያላቸውን ኮሮናቫይረሶች ሊያስከትል፣ በዚህም ሰዎች በተደጋጋሚ ሊያዙ ይችላሉ።
ይህ ደግሞ በሽታ የመከላከል አቅማቸው ደካማ ለሆኑ ሰዎች አደጋ ይሆናል።
የመጨረሻው አማራጭ የሰው ዘር በዘላቂነት ባህሪውን መቀየርና የቫይረሱን ስርጭት መግታት እንደሆነ ሳይንቲስቶቹ ይናገራሉ። ይሀ እስካሁን እየተሰጡ ያሉ ምክር ሃሳቦችን በሙሉ መተግበርን እና በተደጋጋሚ የቫይረሱን ምርመራ ይጨምራል። ሰዎችን ዘወትር በለይቶ ማቆያ ማስቀመጥንም እንዲሁ።
ኮቪድ-19 በውጤታማነት የሚያክሙ መድሃኒቶችን መስራትም ሌሎች ስትራቴጂዎችን ሊያግዝ የሚችል ይሆናል።
የእንግሊዝ መንግሥት ዋና የጤና አማካሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ክሪስ ዊቲ መፍትሄ የሚሉት ስትራቴጂ ምን እንደሆነ በቢቢሲ ተጠይቀው ሲመልሱ " በረዥም ጊዜ ክትባት ከዚህ ጉዳይ መውጫ ነው፤ ይህም በሚቻለው ፍጥነት ይሆናል" ሲሉ መልሰዋል።















