የአሜሪካ እስር ቤቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት እስረኛ መልቀቅ ጀመሩ

ሪከርስ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ እስር ቤቶች ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ታራሚዎች እንዳሉ መሰማቱን ተከትሎ እስር ቤቶች እስረኛ መልቀቅ መጀመራቸው ተገለፀ።

የሎስ አንጀለስ እና ክሌቭላንድ እስር ቤቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ታራሚዎች መልቀቃቸውን ተክትሎ ረቡዕ የኒው ዮርክ እስር ቤት ለወረርሽኙ ተጋላጭ ያላቸውን እስረኞች መልቀቅ መጀመሩ ተሰምቷል።

የእስርኛ አያያዝ ወትዋቾች ታራሚዎች በቫይረሱ ለመያዝም ለማስተላለፍም የተጋለጡ መሆናቸውን እየገለፁ ነው።

እስካሁን በአሜሪካ 9400 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን 152 ሞቶችም ተመዝግበዋል።

የኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ቢል ዲ ብላዚዮ ረቡዕ እለት እስር ቤቶች በጥቃቅን ወንጀሎች የታሰሩ ታራሚዎችን እንዲሁም ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸውና ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑትን የመለየት ሥራ እንደሚሰሩ አስታውቋል።

ከንቲባው ይህን የተናገሩት ረቡዕ እለት ሪከርስ በተሰኘው የደሴት እስር ቤት ጠባቂዎችና እስረኞች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው መሰማቱን ተከትሎ ነው።

የ68 ዓመቱ የቀድሞ የሆሊውድ ፕሮውዲውሰር ሃርቪይ ዋይንስታይንም እዚሁ እስር ቤት የሚገኝ ሲሆን እሱም ወደ ሌላ እስር ቤት እንደሚዘዋወር ተገልጿል።

ሎስ አንጀለስ እስር ቤት ባለፈው ሳምንት ብቻ የአጠቃላይ እስረኞችን ቁጥር በ600 ቀንሷል።

ሎስ አንጀለስ ግዛት በዓለም አቀፍ ደረጃ ብዙ እስረኛ ያላት ሲሆን 22 ሺህ የሚሆኑ እስረኞች እንዳሉ ይታመናል።

በግዛቲቱ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት እስሮችም መቀነሳቸው ታውቋል።

ኮሮና