ሁለት ኢትዮጵያዊያን ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ መሞታቸው ተረጋገጠ

የሬሳ ሳጥን

የፎቶው ባለመብት, AFP

አውሮፓ ውስጥ በኮሮናቫይረስ [ኮቪድ-19] ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል ቀዳሚዋ በሆነችው ጣሊያን ውስጥ ሁለት ኢትዮጵያዊያን በበሽታው ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አረጋገጠ።

ኢትዮጵያዊያኑ እዚያው ጣሊያን ውስጥ በበሽታው ተይዘው ህክምና ሲደረግላቸው ቆይተው ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ ያናገራቸው የውጪ ጉዳይ ምንጮች አረጋግጠዋል።

በወረርሽኙ የሞቱት ሁለቱም ሰዎች ዕድሜያቸው ከ40 ዓመት በላይ የነበረ ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊያን እንደሆኑ የታወቀ ሲሆን አንደኛው ለረጅም ዓመታት ጣሊያን ውስጥ የኖሩ መሆናቸውም ቢቢሲ ለመረዳት ችሏል።

አመሻሹ ላይ ያነጋገርናቸው በጣሊያን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሠራተኛ የሆኑት አቶ ብዙአየሁ ወንድይራድ የሁለቱን ኢትዮጵያዊያን ሞት ለቢቢሲ አረጋግጠው፤ ሟቾቹ ግን ሁለት ወንዶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

አንደኛው ፓርማ በተባለ ከተማ ሌላኛው ደግሞ ቤርጋሞ የሚባል ሚላን አጠገብ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ሕይወታቸው እንዳለፈ አስረድተዋል።

በመጀመሪያ በፓርማ ሕይወቱ ያለፈው ግለሰብ ባለቤትም በቫይረሱ ተይዛ በሆስፒታል ውስጥ ክትትል እየተደረገላት ሲሆን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ የገለፁልን አቶ ብዙአየሁ፤ የሁለቱ ግለሰቦች ባለቤቶችን በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዘነቡ ታደሰ ደውለው እንዳፅናኗቸውም አክለዋል።

በጣሊያን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ሁኔታም በተመለከተም በዋትስአፕ ግሩፕ እና የኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብን ከሚያስተባብሩ ግለሰቦች ጋር መረጃዎችን እንደሚለዋወጡ አቶ ብዙአየሁ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ በሽታ በእድሜ በገፉና ሌሎች የቆዩ የጤና ችግሮች ባሉባቸው ሰዎች ላይ እስከ ሞት የሚያደርስ ከባድ ጉዳትን ያስከትላል።

ጣሊያን ውስጥ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው እንዳለፈ የተነገረው ሁለቱ የኢትዮጵያዊያንም ሞት የተፋጠነው ቀደም ባለ የጤና ችግር ምክንያት ሊሆን ይችላል ተብሎ ተጠርጥሯል።

ከቻይና ቀጥሎ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ክፉኛ በተጠቃችው ጣሊያን ውስጥ እስካሁን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ31 500 በላይ የደረሰ ሲሆን 2503 ሰዎች ደግሞ መሞታቸውን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታስ።

ኮሮና

ከኮሮናቫይረስ ጋር የተያያዙ ሌሎች የአገር ውስጥ እና ከተቀረው ዓለም የተሰባሰቡ ወቅታዊ መረጃዎችን የሚከተለውን ሊንክ በመጫን ማግኘት ይችላሉ።