ሕንድ በስልክ ጥሪ ስለኮሮናቫይረስ መረጃ እየሰጠች ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕንድ የሚገኙ በርካታ የሞባይል ኔትወርክ አቅራቢዎች ደንበኞቻቸው ማንኛውንም ጥሪ ከማድረጋቸው በፊት ለ30 ሰከንድ የኮሮናቫይረስ መረጃ እንዲያገኙ እያደረጉ ነው።
ጂሎ፣ ቢኤስኤንኤል እና ቮዳፎን የተባሉት ኩባንያዎች መንግሥት ያቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ተግባራዊ ካደረጉት መካከል ይገኙበታል።
መልዕክቱ በእንግሊዘኛ የሚሰራጭ ሲሆን ማንኛውም ሰው ሲደውል ከጥሪው በፊት የሚያስል ሰውና የጤና መልዕክቱን ይሰማሉ።
ነገርግን አንዳንድ ደንበኞች በመልዕክቱ መበሳጨታቸውን ደጋግመው በመግለጻቸው የተነሳ በርካታ ድረ-ገጾች መልዕክቱን እንዴት ማስቆም እንደሚቻል የሚገልፅ መረጃ እያሰራጩ ይገኛሉ።
ስለቫይረሱና ስለምልክቶቹ መረጃ የያዘው ይህ መልዕክት ደዋዩ ብቻ የሚሰማው ሲሆን የመደበኛው ጥሪው አካል አይደለም ተብሏል።
የቢቢሲ ደልሂ ቢሮ ባልደረቦች ይህንን መልዕክት መስማት ከጀመሩ ሳምንት እንደሆናቸው ገልፀዋል።
አክለውም ሰዎች ስለበሽታው ምልክቶች እና ቫይረሱ ከተገኘባቸው ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው መረጃ ይሰጣል ሲሉ ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ ቀድሞም ስለቫይረሱ የበለጠ ፍርሃት በነበረባቸው ሰዎች ዘንድ "መረበሽ" መፍጠሩ እንዳልቀረ ገልፀዋል።
አገልግሎቱ የተጀመረ ዕለት በርካታ መገናኛ ብዙኀን ትኩረት ሳይሰጡ የቀሩ ቢሆንም በማግስቱ ግን አገልግሎቱን ለማቋረጥ የሚረዱ መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።
በሕንድ እስካሁን ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ከሌላ አገራት አንፃር ሲታይ አነስተኛ ነው።













