በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በርካታ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ ለመቆየት እየጠየቁ ነው

የፎቶው ባለመብት, Luke Dray
በኮሮናቫይረስ ስጋት ምክንያት በርካታ ቁጥር ያላቸው ቻይናዊያን ወደ አገራቸው ላለመመለስ በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ቪዛ እያራዘሙ መሆኑ ተገለጸ።
ቻይናዊያኑ ለተለያዩ ሥራዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ቆይተው በአሁኑ ወቅት የተሰጣቸው የመቆያ ቪዛ ሲያበቃ ነው ወረርሽኙን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ፈቃድ እየጠየቁ ያሉት ተብሏል።
በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ውስጥ የኢሚግሬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ አይክፋው ጎሳዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቂት የማይባሉ ቻይናዊያን በኢትዮጵያ ለመቆየት የሚያስችላቸውን የቪዛ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ እያገኙ ነው።
"ቻይናዊያኑ በአገራቸው ያጋጠመውን ወረርሽኝ በመስጋት ነው በኢትዮጵያ ለመቆየት ጥያቄ እያቀረቡ ያሉት" ብለዋል አቶ አይክፋው። ይህንን ከግንዛቤ በማስገባትም መንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ላሉ ቻይናዊያንም ሆነ የሌሎች አገራት ዜጎች የመቆያ ጊዜያቸው እንዲራዘም እያደረገ ነው ብለዋል።
ሕገ ወጥነትን ለመከላከል ቀደም ሲል ቻይናዊያን የመቆያ ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ እንዲራዘምላቸው በሚጠይቁ ጊዜ ለ10 ቀናት የሚቆይ ማራዘሚያ ይፈቀድላቸው እንደነበር የጠቀሱት አቶ አይክፋው፤ አሁን ግን በአገራቸው የተከሰተውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ለአንድ ወር የሚቆይ ቪዛ ይሰጣቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ባሻገርም በአንዳንድ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ በርካታ ጣሊያናዊያን ቱሪስቶች በኢትዮጵያ መቆየት የሚያስችላቸው ቪዛ ቢያበቃም በአገራቸው ያለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋትን በመፍራት ኢትዮጵያ ውስጥ ለመቆየት ጠይቀዋል ለሚለው ወሬ ማረጋጫ አልተገኘም።
ቢቢሲ ይህንኑ ለማጣርት አዲስ አበባ የሚገኘውን የጣሊያን ኤምባሲን የጠየቀ ሲሆን በተሰጠው ምላሽ መሰረት እንዲህ አይነት ጥያቄ አለመቅረቡንና የተባለው ነገር "ሐሰተኛ ወሬ" መሆኑን ተነግሮታል።
አቶ አይክፋው ጎሳዬም ይህንን መረጃ ሰምተው ለማጣራት መሞከራቸውንና እንደተባለው ከተጠቀሱት ጣሊያናዊያን ቱሪስቶች በኩል ቪዛ የማራዘም ምንም አይነት ጥያቄ ለመስሪያ ቤታቸው አለመቅረቡን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።













