መዓዛ መላኩ፤ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ስለኮሮናቫይረስ መረጃ የምታቀብለዋ በጎ ፍቃደኛ

የፎቶው ባለመብት, Meaza Melaku
በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ ሕብረተሰቡን ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ብቅ ብቅ እያሉ ነው።
ከእነዚህም መካከል ሰለ ኮሮናቫይረሰ ጠቃሚ መረጃዎችን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በፌስቡክ አማካኝነት በምልክት ቋንቋ የምታሰራጨው መዓዛ መላኩ ትገኝበታለች።
ልዩ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች እንደዚህ ያሉ ወሳኝ እና ወቅታዊ መረጃዎችን የሚያገኙበት ዕድል በጣም ጠባብ እንደሆነ መዓዛ ትናገራለች።
ለዚህም "ኃላፊነቴን መወጣት ስላለብኝ ይህን ተግባር ለመፈጸም ተነሳሳሁኝ" ስትል መዓዛ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የሚፈልጉት ይዘት የለም
በ Facebook ተጨማሪ ይመልከቱቢቢሲ ከሌሎች ድረ-ገጾች ለሚመጡ መረጃዎች ሀላፊነት አይወስድም.የ Facebook ይዘት መጨረሻ
መዓዛ በፌስቡክ ገጿ ቫይረሱን በተመለከተ ከመንግሥት እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎችን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በምልክት ቋንቋ እያስተላለፈች ትገኛለች።
በአገሪቱ የሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ መስማት ለተሳናቸው ዜጎች አጥጋቢ መረጃ መስጠት እስኪጀምሩ ድረስ ፌስቡክን በመጠቀም መልዕክት የማድረስ ጥረቴን እቀጥላለሁ ብላለች።
መዓዛ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምልክት ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪዋን፤ ሁለተኛ ዲግሪዋን ደግሞ ከኦስሎ ዩኒቨርሲቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት አጠናቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትናንትናው ዕለት አምስት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውን ተከትሎ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችና ትልልቅ ስብሰባዎች ለቀጣዮቹ 15 ቀናት እንደሚዘጉ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ አስፈላጊነቱ በያሉበት ዩኒቨርሲቲ ክትትል የሚደረግላቸው መሆኑን ገልፀው እንደ አስፈላጊነቱ ታይቶ አነስተኛ ስብሰባዎችም በጤና ሚኒስቴር እውቅና ሊካሄዱ እንደሚችሉም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ወቅት እጅግ አስፈላጊ የሆኑ እንደ አልኮልና ሳሙና ያሉ በስፋት የሚሰራጩም ይሆናል ብለዋል።
እህንን ተከትሎም የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት አንበሳ እና ሸገር አውቶብሶች ለተሳፋሪዎቻቸው የእጅ ማጽጃ ሳኒታይዘር እንደሚያቀርቡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) አስታወቀዋል።
ተሳፋሪዎች ወደ አውቶብሶቹ ሲገቡ እጃቸውን በሳኒታይዘር እንዲያጸዱ ይሆናል ያሉት ምክትል ከንቲባው ፤ የአውቶብሶቹ አሽከርካሪዎችም የእጅ ጓንት ያደርጋሉ ብለዋል።












