በኮሮናቫይረስ ተጠርጥሮ ከአምቡላንስ ያመለጠው ወጣት ያደረገው ምንድን ነው?

የአማራ ክልል ካርታ

አንድ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሰ ግለሰብ የኮሮናቫይረስ ምልክት ታይቶበት ተጠርጥሮ ወደ ለይቶ ማቆያ በአምቡላንስ በሚወሰድበት ጊዜ አምልጦ ወደ ትውልድ መንደሩ በመመለስ ላይ ሳለ በደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል።

ዛሬ ከሰዓት (ሰኞ) የኢትዮጵያ ሕብረሰተብ ጤና ኢንስቲትዩት ግለሰቡ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ በላቦራቶሪ ምርመራ ተረጋግጧል ብሏል።

ቢቢሲ ስለግለሰቡ ከአካባቢው ነዋሪዎች ባደረገው ማጣራት ነዋሪነቱ እዚያው ለጋምቦ ወረዳ ተወልዶ ያደገ ወጣት ሲሆን በሕገ ወጥ መንገድ ከአንድ ወር በፊት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለሥራ ተጉዞ የነበረ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።

ነገር ግን በስደት ለአንድ ወር ከቆየ በኋላ በሳዑዲ አረቢያ ፖሊስ ተይዞ ወደ ኢትዮጵያ መላኩን የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌትነት አበባው ተናግረዋል።

በመሆኑም ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ በተደረገለት ምርመራ የኮሮናቫይረስ ምልክትቶች ስለታዩበት በአምቡላንስ ወደ ለይቶ ማቆያ ቦታ ሲወሰድ አምቡላንሱን ሰብሮ በማምለጥ እዚያው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የእህቱ ቤት አምርቶ እንደነበረ ኃላፊው ይናገራሉ።

ይህ መቼ እንደሆነ ቀኑን ለማወቅ እንዳልቻሉ አቶ ጌትነት ገልጸው፤ ትናንት (ቅዳሜ) ከፌደራል ጤና ጥበቃ ተደውሎ የአካባቢው ተወላጅ የሆነው ግለሰብ በኮሮናቫይረስ ተጠርጥሮ እንደነበርና ለይቶ ማቆያ ከመግባቱ በፊት እንደጠፋ እንደተነገራቸውና ክትትል እንዲያደርጉ መረጃ እንደደረሳቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም የአካባቢው ባለስልጣናት ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ወደ አካባቢው የሚመጡ መኪኖች ላይ ፍተሻ በማድረግ ግለሰቡን ለማግኘት ክትትል ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አቶ ጌትነት እንዳሉት የግለሰቡን ወንድም አብሯቸው እንዲሆን በማድረግ በመኪና ከሚጓዙ መንገደኞች መካከል ተፈላጊውን ለመለየት ጥረት ማድረጋቸውን አመልክተው ትናንት [ዕሁድ] ጠዋት 5 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችን ከፈተሹ በኋላ ስድስተኛው ላይ ተጠርጣሪው መገኘቱን ገልጸዋል።

ከተፈላጊው ግለሰብ ጋርም ከአዲስ አበባ ጀምሮ ወደ ትውልድ መንደሩ ለማድረስ የተጓዘው የእህቱ ባልም አብሮት መገኘቱን ተነግሯል።

ክስተቱን የበለጠ ውስብስብ ለማድረግም ከአዲስ አበባ ቀጥታ ወደ ሚፈልገው ቦታ የሚያደርሰው ትራንስፖርት ከመያዝ ይልቅ በተለያዩ ከተሞች ላይ እየወረደ መጓጓዣውን ሲቀይር እንደነበር ተገልጿል።

በዚህም መሰረት ከክትትሉ ለማምለጥ በሚልም ኮምቦልቻ፣ ደሴና ጉጉፍቱ የሚባሉ ከተሞች ላይ ወርዶ መኪና መቀየሩንና መጨረሻ ላይም ጉጉፍቱ ላይ በሳይንት መኪና ሲጓዝ ለጋምቦ ላይ መያዙን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

ግለሰቡና አብሮት የነበረው የእህቱ ባለቤት በትራንስፖርት አብረዋቸው ከተጓዙት ሰዎች ባሻገር ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙ በማድረግ በለይቶ ማቆያ ውስጥ በመሆን ምርመራና ክትትል ወደሚያገኙበት ወደ አዲስ አበባ ክትትሉ ሲያደርጉ በነበሩት የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ታጅበው እንዲሄዱ ተደርጓል።

ግለሰቡ ተሳፍሮበት በነበረው ውስጥ የነበሩት ወደ 60 የሚደርሱ ሰዎች ምርመራ ተደርጎ ውጤት እስኪታወቅ ድረስ ድንኳን ተዘጋጅቶ ለብቻቸው እንዲቆዩ እንደሚደረግም አቶ ጌትነት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ ባሻገር ግን በተለያዩ ከተሞች ውስጥ ከተሳፈረባቸው መኪኖች ላይ አብረውት የተጓዙትን መንገደኞች ለማወቅ አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ የግለሰቡ የምርመራ ውጤት ቀጣይ መወሰድ ያለበትን እርምጃ የሚወስን መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት አመልክተዋል።