የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ፍለጋና የዋጋ መናር በአዲስ አበባ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አዲስ አበባ ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ገንዘብ ሲሸጥ እንደነበረና በመደብሮች ውስጥ ማግኘት እንዳልቻሉ ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ።
አርብ ዕለት አዲስ አበባ ላይ የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት የመጀመሪያው የተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ ታማሚ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተገኘ በኋላ ስጋት የገባቸው ሰዎች የፊት ጭንብልና ፈሳሽ የእጅ ማጽጃ ውህዶችን በመግዛት ላይ ናቸው።
የቢቢሲ ያናገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዳሉት በሽታው አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ሊከላከለው ይችላል የተባሉ ነገሮችን እየገዙ መሆናቸውን ነገር ግን የጭንብሎቹና ፈሳሽ የንጽህና መጠበቂያዎች [ሳኒታይዘር] እንደልብ እንደማይገኙ ከተገኙም ዋጋቸው በሚያስደነግጥ ሁኔታ መናሩን ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ የመድሃኒት መደብሮችም የፊት ጭንብልና ሳኒታይዘር እንደሌላቸው በሚለጥፉት ማስታወቂያም ሆነ በተጠየቁ ጊዜ የሚሰጡት ምላሽ እንደሆነ ቅዳሜ ዕለት በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ ፋርማሲዎችን የተመለከተው የቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይም በርካቶች የፊት ጭንብል ስለመጥፋቱና ስለመወደዱ ገጠማቸውን በጽሁፍና በምስል እያሰፈሩ ነው። ጭንብሉ ያለባቸው ፋርማሲዎች ረዘም ያሉ ሰልፎች የታዩ ሲሆን ውስን ቁጥር ያላቸውን መሸፈኛዎችን በመደበኛው ዋጋ ሲሸጡ እንደነበር ተገልጿል።
ቢቢሲ በስልክ ያናገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት የመድሃኒት መደብሮች የፊት መሸፈኛ ጭምብል እንደጨረሱና ሲሸጡ የነበረውም ቀደም ሲል በነበረው ዋጋ እንደሆነ ገልጸዋል።
የከተማዋ ባለስልጣናትም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ተፈላጊ በሆኑ ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ በሚሸጡ የንገድ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተው፤ ኅብረተሰቡም ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የፊት ጭንብል ፍለጋ
በርካታ ሰዎች በሽታውን ሊከላከል ይችላል በማለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን ለመግዛት ወደ መድሃኒት መደብሮች ቢሄዱም ለማግኘት እንደተቸገሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ሰው ሁሉ እየገዛ በመሆኑ ለልጆቼም ሆነ ለእራሴ የሚሆን ማስክ ለመግዛት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በየደረስኩበት ቦታ ያሉ ፋርማሲዎችን ብጠይቅም ላገኝ አልቻልኩም" ያሉት የሁለት ልጆች እናትና አዲስ አበባ ውስጥ አብነት የሚባለው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ መብራት አስቻለ ናቸው።
ወይዘሮ መብራት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጎረቤቶቻቸው ጭንብሉን እስከ 200 ብር በሚደርስ ዋጋ ከሰዎች ላይ መግዛታቸውን እንደሰሙ ነገር ግን ይህን ያህል ገንዘብ በማውጣት ለቤተሰባቸው መግዛት ከባድ ስለሆነባቸው እንደተዉት ገልጸዋል።
የጭንብሉን አስፈላጊነት በተመለከተ የሰሙት በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች መሆኑን እንጂ ከባለሙያዎች የተነገራቸው ነገር እንደሌለ የሚጠቅሱት ወ/ሮ መብራት "በሸታው አሳሳቢ በመሆኑ የምችለውን ላድርግ በማለት ነው ከአንዱ ፋርማሲ ወደ ሌላው በመሄድ ስጠይቅ የነበረው" ይላሉ።
ተለያዩ ሰዎች በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ የሚሰጡት አስተያየቶችም ከዚሁ ጋር የሚመሳሰሉ ናቸው የፊት መሸፈኛ ጭንብል ከ150 እስከ 500 ብር በሚደርስ ዋጋ እየተሸጡ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ናቸው።
ከፊት መሸፈኛ ጭምብሎች በተጨማሪ የእጅ ማጽጃ ፋሳሾችም ዋጋቸው የጨመረ ሲሆን ተህዋሲያንን ያጠፋሉ ተብለው የሚነገርላቸው ሳሙናዎችም ተፈላጊነታቸው ጨምሯል። ዋጋቸውም በዚያው ልክ መጨመሩን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የከተማው መስተዳደርም "የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ተጠቂ ተገኝቷል" የሚለው መረጃ ከወጣ በኋላ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አሳወቋል።
እጥረት እየተከሰተ ነው
ከኮሮናቫይረስ መከሰት ጋር በተያያዘ አፍን አፍንጫን የሚሸፍኑ ጭምብሎች በስፋት በዓለም ዙሪያ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው። በዚህም ሳቢያ በበርካታ አገራት ውስጥ የጭንብሎቹ እጥረት እየተከሰተ በመሆኑ አምራቾች የጭንብል ምርታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ በዓለም የጤና ድርጅት ተጠይቀዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚገምተው በየወሩ 89 ሚሊዮን የሚደርስ የፊት ጭምብሎች ያስፈልጋሉ። በኮሮናቫይረስ ስጋትና በተሳሳተ አመለካከት ሳቢያ እነዚህ ጭንብሎች ያላግባብ ጥቅም ላይ ስለሚውሉ የሚየስፈልገው ቁጥር ከዚህም በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
ድርጅቱ እንዳለውም የፊት ጭንብሎች በስፋት ጥቅም ላይ በመዋላቸውና ሰዎች በብዛት እየገዙ በማስቀመጣቸው የተነሳ የህክምና ባለሙያዎች በየዕለቱ በሚጠቀሙት አቅርቦት ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን አመልክቶ፤ ይህም በዚህ የወረርሽን ጊዜ ህሙማንን በመርዳት ሥራ ላይ የተጠመዱ የህክምና ባለሙያዎች ለኮሮናቫይረስና ለሌሎች በሽታዎች ተጋላጭ ሊያደርጋቸው ይችላል ሲል ስጋቱን ገልጿል።
የፊት መሸፈኛ ጭንብል በእርግጥ ያስፈልገናል?
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው የኮሮናቫይረስን ለመካላከል በሚል ሁሉም ሰው የአፍና የአፍናጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አያስፈልገውም።
ጭንብሉን ማድረግ ያለባቸው የሚያስነጥሱና የሚያስሉ ከሆነ እንዲሁም በበሽታው የተጠረጠረ ወይም የተያዘን ሰው የሚቀርቡና የሚንከባከቡ ሰዎች ብቻ ነው።
ለእነዚህ ሰዎች ጭንብሉን ማድረግ ብቻ በቂ አይደለም፤ በውጤታማ ሁኔታ በሽታውን ለመከላከልም በመደበኛነት እጃቸውን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ወይም አልኮል ነክ በሆኑ ፈሳሾች እጃቸውን ማጽዳት ይጠበቅባቸዋል።
በተጨማሪም ጭንብሉን መጠቀም ያለባቸው ሰዎች እንዴት መጠቀምና በተገቢው ሁኔታ እንዴት መወገድ እንዳለበትም ማወቅ ይገባቸዋል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ይመክራል።
ስለዚህም በአዲስ አበባና በሌሎች ስፍራዎች የተጠቀሱት አይነት የበሽታው ስጋቶች ሳይኖሩ ጭምብልን ከሚገባው በላይ ከፍተኛ ገንዘብ እያወጡ መግዛት በሽታውን ለመከላከል የሚኖረው ጠቀሜታ ዝቅተኛ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒሰቴር መክሯል።
እነዚህ ለአጭር ጊዜ ጥቅም ላይ ውለው የሚጣሉት የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች ጥብቅ ብለው አፍንጫና አፍን የሚሸፍኑ ካለመሆናቸው ባሻገር ረጅም ጊዜን አያገለግሉም።
የማስነጠስና የማሳል ምልክት የሚታይባቸውን ወይም በኮሮናቫይረስ ከሚጠረጠሩ ሰዎች ጋር የግድ መቅረብ ያለባቸው ሰዎች የሚጠቀሙባቸው የፊት መሸፈኛ ጭንብሎች በቀላሉ በላብ ስለሚባላሹ ወዲያው ወዲያው መቀየር አለባቸው።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚመክሩት የተጠቀሱት ምልክቶች እስካልታዩ ድረስ ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ማድረግ አያስፈልጋቸውም።
ከዚያ ይልቅ ግን የበሽታው ስጋት ለማስወገድ ከሚያስሉ፣ ከሚያስነጥሱ ወይም ትኩሳት ካለባቸው ሰዎች ጋር የሚኖርን ንክኪ ማስወገድ፣ እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ ካልሆንም ተህዋሲያንን በሚያስወዱ ማጽጃዎች እጅን ማጽዳት ከሁሉ በበለጠ ጠቃሚ ነው።
በተጨማሪም እጅን ሳይታጠቡ ዓይንን፣ አፍንጫንና አፍን አለመንካት እንዲሁም መጨባበጥን ማስወገድ የቫይረሱን መስፋፋት ለመግታት መወሰድ ካለባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል ይጠቀሳሉ።













