ኮሮናቫይረስ፡ "ቻይና፣ ዉሃን በመሆኔ ደህንነቴ የተጠበቀ ነው"

ሄኖክ አምደማሪያም

የፎቶው ባለመብት, Henock Amedemariyam

የምስሉ መግለጫ, ሄኖክ አምደማሪያም በቻይና ዉሃን ግዛት የምህንድስና ተማሪ ነው

ሄኖክ አምደማሪያም ኪዳኔ በቻይና ዉሃን ግዛት የምህንድስና ትምህርቱን መከታተል ከጀመረ አምስት ዓመት እንደሞላው ይናገራል። ወደ ዉሃን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ የሄደው የመጀመሪያ ዲግሪውን ለመሥራት የነበረ ቢሆንም በዚያው ሁለተኛ ዲግሪውን ቀጥሎ መቆየቱን ለቢቢሲ ገልጿል።

ሄኖክ በዉሃን ብቻ ወደ 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች እንደሚገኙ ገልጾ፣ እርሱ በሚማርበት ዉሃን ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ አርባ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙ ይናገራል።

ሄኖክ የሚማርበት ተቋም በግዛቲቱ ከሚገኘው ዉሃን ዩኒቨርስቲ ቀጥሎ ሁለተኛው ነው።

የቫይረሱ ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞ ከኢትዮጵያውያኑ ጋር በተለያዩ በዓሎች አከባበር ላይ ይገናኙ እንደነበር የሚያስታውሰው ሄኖክ፤ ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ ግን በስልክ ደህንነትን ከመጠያየቅ ባለፈ አብሮ ጊዜ ለማሳለፍ ምቹ አለመሆኑን ይገልፃል።

የኮሮናቫይረስና ዉሃን

ውሃን በየቀኑ ትለያያለች ይላል ሄኖክ፤ በፍጥነት የምታድግ ከተማ ናት። እንደርሱ አገላለጽ ዛሬ የታየ ባዶ ስፍራ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ህንፃ አልያም አትክልት ተተክሎበት የሚገኝባት፣ ሕይወት እስከነሙሉ ጣዕሟ የምትገማሸርባት ከተማ ነበረች።

በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ተግባቢ፣ ማኅበራዊ ሕይወቱ የሞቀ፣ ሁሉም በመልክም በልክም በዝቶና ሰፍቶ የሚገኝባት ነበረች።

በሚማርበት ዩኒቨርስቲም ቢሆን ከቻይናውያን ውጪ ከአንድ ሺህ ስምንት መቶ በላይ ከተለያዩ አገራት የሄዱ ተማሪዎች የሚገኙበት፣ የመልከ ብዙ ተማሪዎች መሰባሰቢያ መሆኗን ይገልፃል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽን ከመከሰቱ ጥቂት ቀደም ብሎ፤ ውሃን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተውጣጡ ወታደራዊ መኮንኖች አውደ ርዕይን አዘጋጅታ፤ ለቻይናውያን አዲስ ዓመት ሽር ብትን እያለች ነበር።

እንደድሮው ቢሆን ኖሮ ሰባት ቀን ፌሽታና ደስታ በመሆኑ ሁሉም በዚህ መንፈስ ውስጥ ይሆን ነበረ ይላል ሄኖክ።

ሄኖክም ወደ ታይላንድ ሄዶ ለማሳለፍ ሻንጣውን አዘገጃጅቶ፣ የአውሮፕላን ቲኬት ቆርጦ እየተጠባበቀ እንደነበር ያስታውሳል።

አንድ ቀን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለመሸማመት ወደ ገበያ አዳራሽ ሲሄድ፤ ከኢትዮጵያውያን ጓደኞቹ በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችም የመተንፈሻ አካላቸውን ሸፍነው ተመለከተ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ኮሮናቫይረስ፡ በዉሃን ተማሪ የሆነው ሄኖክ ህይወት በከተማይቱ ምን እንደሚመስል አስቃኝቶናል

እርሱም ግራ ስለተጋባ "ከሰው ላለመለየት ብዬ የመተንፈሻ አካል መሸፈኛ ገዝቼ መጠቀም ጀመርኩ" ይላል።

በኋላ ላይም ቤቱ ሳለ የታይላንድ ጉዞህ ተሰርዟል የሚል ኢሜልና ገንዘቡ መመለሱን የሚገልጽ መልዕክት ደረሰው።

በዉሃን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ጎዳናዎቿ የሰው ጠኔ ያዛጋቸዋል። የገበያ አዳራሾቹ ሠው አልባ ሆነዋል። ወረርሽኙ እንደተከሰተ በሳምንት አንዴ ወይንም ሁለቴ ወጥቶ የሚያስፈልጉ ነገሮችን መሸማመት የሚቻል የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ እንቅስቃሴ ተከልክሏል ይላል።

ስለ ኮሮናቫይረስ የተለያዩ ሀሰተኛ መረጃዎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ይለቀቃሉ የሚለው ሄኖክ፤ የሚማርበት ዩኒቨርስቲ ስለበሽታውም ሆነ ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ በማኅበራዊ ሚዲያ የቡድን መወያያቸው (ዊቻት) በኩል መረጃ እንደሚሰጣቸው ይገልፃል።

ቤተሰቡም ቢሆን በየዕለቱ ከኢትዮጵያ እየደወለ ይጠይቃል። ዘወትር በየዜና አውታሩ የሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ሲገለጽ ሲሰሙ ስጋት እንደሚገባቸው ይናገራል።

በየዕለቱ የእርሱ በሕይወት መኖርና በጤና መቆየት የእነርሱ ጭንቀት ነው።

በቻይና የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ደህንነታቸውን ለማወቅ መልዕክት እንደሚልክላቸው የሚናገረው ሄኖክ፤ መመለስ የሚፈልጉ ካሉ በሚል ቅጽ ልኮ ማስሞላቱን ይናገራል።

"የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎቹን ከዉሃን ለማውጣት የሚፈልግ ከሆነ የማልሄድበት ምክንያት የለም" ቢልም እዚያው ቻይና ውስጥ መቆየት ደግሞ ፍላጎቱ መሆኑን ይናገራል።

"ቻይና በመሆኔ ደህንነቴ የተጠበቀ (ሴፍ) ነው ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም በሽታው እዚህ ስለተነሳ ከሌላው አገር የተሻለ ትንሽም ቢሆን እውቀቱም ሆነ ቴክኖሎጂው አላቸው ብዬ አስባለሁ"

አገር ቤት ቢሄድ ቫይረሱ ያለበት እንደሆነ ለማወቅ ከአስራ አራት ቀን እስከ ሃያ ቀን ለይቶ ማቆያ ውስጥ ማስቀመጥ፣ ናሙናውን ወደ ደቡብ አፍሪካ ወስዶ ማስመርመር እንደሚያስፈልግም ይገልጻል።

ሄኖክ እንደሚለው ባይታመምም የጥንቃቄ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። "እዚህ ያለው ነገር ቢታክተኝም ማንንም መውቀስ አልፈልግም" በማለትም ስሜቱን ይገልጻል።

ቻይና ዉሃን ግን ቢያንስ ምርመራውና ሕክምናው አለ በማለት "ያልፋል ብዬም አምናለሁ፤ ይህ ሁሉ ያልፋል" ሲል ለቢቢሲ ተስፋውን ተናግሯል።

እኛ እዚህ አስፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ እናደርጋለን ብሎም "ፈጣሪ ከእኛ ጋር ነው" ሲል ያክላል።

ሄኖክ በዉሃን የተማሪነት ሕይወቱ ከትምህርት ባሻገር የተለያዩ ስፖርቶች ላይ ይሳተፋል

የፎቶው ባለመብት, Henock Amedemariyam

የምስሉ መግለጫ, ሄኖክ በዉሃን የተማሪነት ሕይወቱ ከትምህርት ባሻገር የተለያዩ ስፖርቶች ላይ ይሳተፋል

ኑሮ በሰው ድርቅ በተመታች ከተማ

ሄኖክ በዉሃን የተማሪነት ሕይወቱ ከትምህርት ባሻገር የተለያዩ ስፖርቶች ላይ ይሳተፍ እንደነበር ይገልፃል። አሁን ግን በአንድ ክፍል ውስጥ ከዩኒቨርስቲ ጓደኛው ጋር ቀኑን ሙሉ በር ዘግቶ ማሳለፉ ድብርትና እንቅልፍ እንደለቀቀበት ይገልፃል።

"ከዚህ በፊት ስፖርት እሠራ ነበር። እዋኝ ነበር። ቅርጫት ኳስ ከጓደኞቼ ጋር እጫወት ነበር። አሁን ይህ ሁሉ ናፍቆኛል። ከጓደኞቼ ጋር ሻይ ቡና ማለት፣ ትምህርት ሁሉ ናፍቆኛል። እዚህ ባለው ነገር ደስተኛ ነበርኩ፤ አሁን ግን ሁሉም ነገር ጨለማ ውጦታል።"

አሁን በማደሪያ ክፍላቸው ውስጥ ቀኑን ሙሉ ምግብ በማብሰል፣ መጻሕፍት በማንበብ እና ፊልም በማየት እንደሚያሳልፉ ይናገራል።

"አገር ቤት በጣም ናፍቆኛል" የሚለው ሄኖክ፤ ሙሉ ቀን አልጋ ላይ መዋሉ ይጨንቃል ሲልም የሚሰማውን ለቢቢሲ አጋርቷል።