ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በቻይና

Virus

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻይና ውስጥ የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ በርካታ ሰዎችን መግደሉንና በሺህዎች የሚቆጠሩት በበሽታው መያዛቸውን ተከትሎ በተለይ ቻይና ውስጥ ከፍተኛ ስጋት ነግሷል።

ወረርሽኙ ከአንዲት የቻይና ግዛት ተነስቶ በመላዋ ቻይና መስፋፋቱ ይፋ መሆኑን ተከትሎ በዚህም ሳቢያ የበሽታው መስፋፋት ስጋት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢ ያሉ ሰዎች ካሉባቸው ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው መሆንኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ባለፉት ዓመታት ከቻይና ጋር ጠንካራ ግንኙነት የገነባችው ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለንግድ፣ ለሥራና ለትምህርት ወደተለያዩ ግዛቶች ይሄዳሉ።

በተለይ ደግሞ ከቻይና ከፍተኛ ቁጥር ያለው የትምህርት ዕድል ከሚያገኙ አገራት መካከል አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ ተማሪዎች በተለያዩ የቻይና ግዛቶች በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ አሏት።

በቅርቡ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ የቻይና መንግሥት ከ800 በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ቻይና ውስጥ የአጭርና የረጅም ጊዜ ስልጣና እንዲያገኙ እድል ሰጥቷል።

ከቻይና የንግድ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው በጎርጎሳውያኑ 2018 ከ7 ሺህ 600 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ቻይና ውስጥ ስልጠና አግኝተዋል።

በአሁኑ ጊዜ ቻይና ውስጥ በትምህርት ምክንያት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ትክክለኛ ቁጥር ማግኘት ባይቻልም ከዚህ በፊት ከነበረው ቁጥር አንጻር ጥቂት የማይባሉ ተማሪዎች በቻይና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ይገኛሉ።

ታዲያ ዓለምን በከፍተኛ ደረጃ ያሳሰበው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት በዚህ ወቅት ቻይና ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሁኔታ ምን ይመስላል? ስንል ሁለት በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚማሩ ተማሪዎችን ጠይቀናል።

Presentational grey line

ባዩ አቦኃይ በቻይና ቶንጂ ዩኒቨርስቲ በአካባቢ ምህንድስና ሁለተኛ ዲግሪውን እያጠና ነው። ከበሽታው መከሰት ጋር በተያያዘ የእለት ከዕለት እንቅስቃሴው እንደተስተጓጎለ ይናገራል።

አሁን ወቅቱ የቻይና አዲስ ዓመት በመሆኑ በርካታ ተማሪዎች ወደየመጡባቸው አካባቢዎች በመሄዳቸው፤ በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚገኙት እሱን የመሰሉ ከሌሎች አገራት የመጡ ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

የዩኒቨርስቲው ባለስልጣናት ስለበሽታውና ማድረግ ስላለባቸው የመከላከያ ጥንቃቄዎች በየዕለቱ ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያገኙ የሚናገረው ባዩ እስካሁን የሚያሰጋ ነገር የለም ይላል።

በመላዋ ቻይና ስለተከሰተውና በርካታ ሰዎችን ስለገደለው በሽታ በስፋት መወራቱና በባለስልጣናት የሚደረገው ጥብቅ ቁጥጥር እስካሁን ምንም ስጋት እንዳልፈጠረበት የሚገልጸው ባዩ ዋነኛው ስጋት ነው የሚለው በጥቂት ቀናት ውስጥ እረፍት ላይ ያሉ ተማሪዎች የሚመለሱ ከሆነ ነው።

"ለበዓል ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሄዱ ተማሪዎች ተመልሰው ዩኒቨርስቲው ውስጥ ካሉት ጋር ያለምንም ጥንቃቄ እንዲቀላቀሉ የሚደረጉ ከሆነ ግን የበሽታውን ስጋት ይጨምረዋል" ይላል ባዩ።

አሁን እንደተነገራቸው ግን በሽታው በፍጥነት በመስፋፋቱና በተለያዩ የቻይና ግዛቶች ውስጥ ያለው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ቁጥጥር በመደረጉ ቀጣዩ ትምህርት የሚጀምርበት ጊዜ እንዲራዘም በመደረጉ ያለውን ስጋት በተወሰነ ደረጃ ቀንሶታል።

የዩኒቨርስቲው ኃላፊዎች ላሉት ተማሪዎች ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ተከታታይ ምክር ከመስጠት ባሻገር ከግቢው እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚያደርጉባቸው የሚገልጸው ባዩ፤ ምግብ ለመመገብ ወደ ካፍቴሪያ ከመሄድ ውጪ አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በመኝታ ክፍሎቻቸው ውስጥ ነው።

Presentational grey line

መንግሥት ምናለ በሾንጂ የኒቨርስቲ በአካባቢ ሳይንስ የዶክትሬት ትምህርቱን እየተከታተለ ነው።

በከተማዋ ያሉ የንግድ ተቋማት ተዘግተዋል እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ በመቀዛቀዛቸው ምክንያት "ያለው ሁኔታ ከባድና አስፈሪ ነው" ይላል መንግሥት።

በዩኒቨርስቲው ውስጥ የተወሰኑ የሌሎች አገራት ተማሪዎች መኖራቸውን የሚናገረው መንግሥት በሚወጡና በሚገቡ ቁጥር እንደሚመዘገቡና ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው እንዲሁም ከግቢው መውጣት እንደማይቻል ይህም ያሉበትን ሁኔታ "አስቸጋሪ አድርጎብናል" ይላል።

መንግሥት እንደሚለው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቻይናዊያን ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ውስጥ ስለሌሉ ምግብ በሽያጭ የሚቀርብበት ካፍቴሪያ ውስን ምግቦችን ስለሚያዘጋጅ ሊያልቅ እንደሚችል በዚህም እየተቸገሩ መሆኑን አመልክቷል።

ከግቢው መውጣት ባለመቻላቸው "በተለይ ምግብ ማግኘት ላይ ችግር እየገጠመን ነው" በማለት የእንቅስቃሴ ቁጥጥሩ በግቢው ውስጥም ጥብቅ በመሆኑ ለመንቀሳቀስ እንደተቸገሩና በቀጣይም አገልግሎቱ የበለጠ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለው።

ከበሽታው መከሰት ጋር ተያይዞ በዩኒቨርስቲው ውስጥ የሚገኙት መደብሮችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸው እንዲሁም ውጪ ያለው እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመቆሙ ተማሪዎቹ ባሉበት ቦታ ብቻ ተወስነው ይገኛሉ።

መንግሥት እንደሚለው የሚደረገው ቁጥጥር ጥብቅ ነው "ከመኝታ ክፍሎቻችን ወጥተን በዩኒቨርስቲው ውስጥ ወደሚገኘው ካፍቴሪያ ለመሄድ እንኳን የምንመለስበትን ጊዜ የሚጠቅስ ፎርም መሙላት ይጠበቅብናል" ይላል።

ስለጤንነታቸውና ስላሉበት ሁኔታ በኢንተርኔት አማካይነት በቀን ሦስት ጊዜ ሪፖርት እንሚያደርጉና፤ በግቢው ውስጥ ባሉ ህንጻዎች ውስጥ ከሚኖሩ ተማሪዎች ጋርም ለመገናኘት አስቸጋሪ መሆኑን መንግሥት ለቢቢሲ ተናግሯል።

በቻይና ውስጥ በተለይ የበሽታው ዋነኛ ማዕከል እንደሆነች በሚነገረው የሁቤይ ግዛት ዋና ከተማ ዉሃን ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ለማግኘት እንዲሁም በቻይና ካለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአገሪቱ ስላሉ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

የኮሮናቫይረስ በቻይና ውስጥ እየተስፋፋ በመሄዱ የተለያዩ አገራት ዜጎቻቸውን ከዉሃን ለማስወጣት ጥረት እያደረጉ ነው። አንዳንድ አየር መንገዶች ደግሞ በረራዎችን ሰርዘዋል።