በኮሮናቫይረስ እስካሁን ስንት ሰዎች ሞቱ? ወደ የትኞቹ አገሮች ተዛመተ?.

የፎቶው ባለመብት, AFP
ይህ ዘገባ እስኪታተም ድረስ 80 ሰዎች ሞተዋል። 3 ሺህ ሰዎች ታመዋል፤ 300ዎቹ በጽኑ ሁኔታ ታመው አልጋ ይዘዋል።
ሆኖም ይህ ኮሮና ቫይረስ በትክክል ምንጩ ምን እንደሆነ የሚያውቅ የለም። በዉሃን ከተማ የዓሳ ገበያ ውስጥ እንደተነሳ ግን ይጠረጠራል።
ቻይና አዲስ ዓመቷን በስጋት ተሸብባ እያከበረች ነው። በዓሉ ለሦስት ቀናት የተራዘመ ሲሆን ይህም የሆነው ቫይረሱን ለመቆጣጠር እንዲያመች በሚል ነው።
የቫይረሱ መነሻ ናት የተባለችው ዉሃን ከተማ በሆበይ አውራጃ የምትገኝ ሲሆን በዓለም 42ኛ፣ በቻይና 7ኛዋ ትልቅ ከተማ ናት። አብዛኛዎቹ ከተሞች የጉዞ እገዳን ጥለውባታል።
የዉሃን አየር ማረፊያ በትንሹ 20 ሚሊዮን መንገደኞችን በዓመት ያስተናግዳል። ለዚህም ይመስላል በሽታው ቶሎ የተዛመተው።
በዚህች ከተማ ብቻ የሟቾቹ ቁጥር ከ56 ወደ 76 አድጓል።
ከቻይና ውጭ ደግሞ በትንሹ 41 ሰዎች ታመዋል። ከነዚህ መሐል አሜሪካ ታይላንድና አውስትራሊያ ይገኙበታል።
መልካሙ ዜና እስካሁን ከቻይና ውጭ በቫይረሱ የተያዙ እንጂ በቫይረሱ የሞቱ አለመኖራቸው ነው።
በሽታው የመተንፈሻ አካልን የሚያውክ ሲሆን እስካሁን ክትባትም ሆነ መድኃኒት አልተገኘለትም።
ብዙዎቹ ሟቾች በእድሜ የገፉና መጀመርያውኑም ከመተንፈሻ አካላቸው አንዳች እክል የነበረባቸው ናቸው እየተባለ ነው።

በዉሃን አውራጃ ምን እየሆነ ነው?
የቻይናዋ ዉሃን ከተማ ለንደንን ነው የምታክለው፤ 11 ሚሊዮን ሰዎች ይኖሩባታል። ጉዞ ክልከላ የተደረገባት ዉሃን፤ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ተሽከርካሪዎች ካልሆኑ በስተቀር አይገቡም፣ አይወጡም።
የሚገቡትም ሆነ የሚወጡት ሰዎች የትኩሳት መጠናቸው እየተለካ ነው።
ከግማሽ ሚሊዮን ያላነሱ የጤና ባለሞያዎች በግዛቷ ገብተው ተፍ ተፍ እያሉ ነው።
ሁለት ግዙፍ ጊዜያዊ ሆስፒታሎች በፍጥነት ተገንብተዋል። ፋብሪካዎቿ የአፍ መሸፈኛ ማስክ በማምረት 24 ሰዓት ተጠምደዋል።
የግዛቷ ከንቲባ ዡ ዢያዋንግ እንደተናገሩት በትንሹ 5 ሚሊዮን ዜጎች ከግዛቷ ወጥተዋል፤ ይህም የሆነው የጉዞ እቀባ ከመደረጉ አስቀድሞ ነው።
በቻይና ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?
ለክፋቱ ይሄ ቫይረስ በቻይናዎቹ አዲስ ዓመት ነው የተከሰተው፤ የቻይና አዲስ ዓመት ደግሞ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀስበት እጅግ ትልቅ አውዳመት ነው።
እስካሁን ቤይጂንግ፣ ሻንጋይ፣ ዢኣን እና ቲያንጂን አገር አቋራጭ አውቶቡስ እንዳይገባ እንዳይወጣ እግድ ጥለዋል።
ቤይጂንግ ታላቁን ግንብ በከፊል፣ ሌሎች ዝነኛ የቱሪስ መዳረሻዎቿን ደግሞ ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።
በጉዋንግዶንግ አውራጃ ደግሞ በርካታ ከተሞች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማጥለቅ ግዴታ ነው ሲሉ አውጀዋል። በሆንግ ኮንግና ሻንጋይ ግዙፉ የዲስኒ ፓርክ መዝናኛ ለጊዜው አገልግሎት አልሰጥም ብሏል።
የዚህ ቫይረስ ክፋቱ አንድ በሽተኛ ምንም አይነት ምልክት ሳያሳይ ለ14 ቀናት መቆየቱ ሲሆን የክፋቱ ክፋት ደግሞ በዚህ የበሽታው መራቢያ ወቅት ቫይረሱ ድምጽ አጥፍቶ ከሰው ወደ ሰው መተላለፍ መቻሉ ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ የት ደርሷል?
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም የሚመሩት የዓለም ጤና ድርጅት ለቫይረሱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን ከቻይና ውጭ 41 ሰዎች በቫይረሱ ስለመያዛቸው አረጋግጧል።
ከእነዚህ መካከል 8ቱ በታይላንድ፣ 5ቱ በአሜሪካ፥ 4ቱ በሲንጋፖር አውስራሊያ፣ ታይዋንና ማሌዢያ፣ ሦስቱ በፈረንሳይና ቬትናም፣ አንድ በኔፓል አንድ በካናዳ ይገኛሉ።
ታዲያ ሁሉም ታማሚዎች በቅርብ ጊዜ ዉሃን ከተማ ነበሩ።
ኮሮና ቫይረስ እንሰሳትን የሚያጠቃ በሽታ ነበር።
በፈረንጆች 2003 ሳርስ የሚባል ሌላ ወረረሽኝ ተከስቶ በርካቶችን እንደገደለ የሚታወስ ነው።












