ኮሮናቫይረስ፡ የተጠረጠሩ 4 ሰዎች በአዲስ አበባ ተገኙ

የጤና ጥበቃ ሚንስትር

የጤና ጥበቃ ሚንስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ በኮሮና ቫይረስ ሳይያዙ አይቀሩም ተብለው የተጠረጠሩ አራት ሰዎች በኢትዮጵያ መገኘታቸውን አሳውቋል።

አራቱም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ ሦስቱ ቫይረሱ በተከሰተበት ዉሃን ግዛት ተማሪ የነበሩ ናቸው ተብሏል።

4ቱ ሰዎች በለይቶ ማከሚያ ማዕከል ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው እንደሆነ ታውቋል። ከተለዩት ተጠርጣሪዎች ሁለቱ የሳል እና የሙቀት ምልክት አሳይተዋል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች ደግሞ ምንም አይነት የህመም ምልክት ባያሳዩም፤ ወረርሺኙ ከተከሰተበት ስፍራ የመጡ በመሆናቸው እና ምልክቱ ከታየባቸው ሰዎች ጋር ግነኙነት ስለነበራቸው ተለይተው ክትትል እየተደረገላቸው ነው ሲል ጤና ጥበቃ አስታውቋል።

የጤና ጥበቃ አመራሮች በሰጡት መግለጫ፤ ለተጠርጣሪ ህመምተኞቹ የላብራቶሪ ናሙና ተወስዶ ለምረመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ መላኩን እና እስካሁን ከተወሰደው ናሙና በኢትዮጵያ በተደረገላቸው ምረመራ ከ5 አይነት ኮሮና ቫይረሶች ነጻ መሆናቸው ተናግረዋል።

በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የመንገደኞች የሰውነት ሙቀት መለካት ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን 21ሺህ ሰዎች ሙቀት መለካቱም ተነግሯል።

እስካሁን በቻይን ከ100 በላይ ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።

Presentational grey line

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ ጠቃሚ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ የሚከተለውን መረጃ ከቀናት በፊት አስተላልፏል።

ኮሮና ቫይረስ ምንድነው?

የኮሮና ቫይረስ ከቀላል እስከ ከባድ የመተንፈሻ አካል ሕመም የሚያስከትል የቫይረስ ዝርያ ሲሆን ሞትን ሊያስከትል የሚችል ህመም ነው።

የቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች

በሽታው ያለበት ሰው ሲያስነጥስ ወይም ሲያስል፣ ባልበሰሉ ምግቦች፣ ከታማሚው ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ ይተላለፋሉ።

የበሽታው ምልክቶች

በበሽታው የተያዙ ሰዎች ትኩሳት፣ ሳል፣ የትንፋሽ መቆራረጥ እና የመተንፈስ ችግር ምልክቶች ይታይባቸዋል።

በሽታው የጠናባቸው ሰዎች ላይ ደግሞ እንደ የሳምባ ምች እና ከባድ የመተንፈሻ አካላት ህመም ይስተዋልባችዋል።

በበሽታው መያዛቸውን የጠረጠሩ ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው?

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ካለብዎ ወዲያውኑ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።

የበሽታው ስሜት ከመፈጠሩ አስራ አራት ቀናት በፊት በሽታውን ሪፖርት ወዳደረጉ አገራት ሄደው ከነበረም ይህንንም ለጤና ባለሙያ ያሳውቁ።

በሚያስሉበት እና በሚያስነጥሱበት ጊዜ በሽታው ወደ ጤነኛ ሰው እንዳይተላለፍ አፍና አፍንጫን በክንድ፣ በመሃረብ ወይም በሶፍት ይሸፍኑ።

አፍን አፍንጫን ለመሸፈን የተጠቀምንበትን ሶፍት በአግባቡ በቆሻሻ መጣያ ውስጥ ማስወገድ እና እጅን ሁልጊዜ በውሃ እና በሳሙና መታጠብ ያስፈልጋል።

በበሽታው መያዝዎን ሪፖርት ለማድረግ በነጻ የስልክ መስመር 8335 ወይም የመደበኛ ስልክ 0112765340 መጠቀም ይችላሉ

በሽታው ወዳለባቸው ሃገራት ሲጓዙ ሊወሰዱ የሚገቡ ጥንቃቄዎች

ትኩሳት እና የሳል ምልክት ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር ንክኪ አለማድረግ

በተለይ ደግሞ ከታመሙ ሰዎች ወይም ከአካባቢያቸው ጋር ንክኪ ከፈጠሩ እጅን በሳሙናና ውሃ መታጠብ

ያልበሰሉ የእንስሳት ተዋጽኦዎችን አለመመገብ

በሕይወት ካሉም ሆነ ከሞቱ የቤት እና የዱር እንስሳት ጋር ንክኪ አለማድረግ

ስለ በሽታው በቂ መረጃ እንዲኖረዎ የሚመለከታቸውን ይጠይቁ

የመከላከልና የዝግጁነት ራዎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቤጂንግ፣ ሆንግ ኮንግ፣ ሻንጋይ፣ ቸንዱ እና ጓንዡ እንደሚበር ይታወቃል። ይህ ቫይረስ ከተሰራጨባቸው ከተሞች መካከል ደግሞ ቤጂንግ እና ሆንግ ኮንግ ተጠቃሽ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ቦሌ ዓለም አቀፍ አየርማረፊያ በርካታ መንገደኞች አቋርጠውት የሚያልፉት በርካታ ናቸው።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በዓለም ጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሠረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት የመለካት ሥራ መጀመሩን አስታውቋል።