በቻይና የተከሰተው አዲስ ቫይረስ ምን ያህል አስጊ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቀደም ሲል በሳይንስ የማይታወቅ እና የሳንባ በሽታን የሚያስከትል ግራ የሚያጋባ ቫይረስ በቻይናዋ ከተማ ውሀን መከሰቱ ተሰምቷል።
ከ50 የሚበልጡ ሰዎችም በቫይረሱ ተይዘዋል። ከእነዚህ መካከል ሰባቱ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።
ይሄው አዲሱ ቫይረስ ታማሚዎችን ለሳንባ ምች የሚያጋልጥ ሲሆን፤ በዓለም የሚገኙ የጤና ባለሥልጣናትን ስጋት ውስጥ ከትቷል። ይሁን እንጅ ዛሬ ተከስቶ ነገ የሚጠፋ ቫይረስ ይሁን፤ አሊያም በጣም አደገኛ የሆነ ቫይረስ ምልክት ይሆን? የሚለው እያወዛገበ ነው።
በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ናሙና ተወስዶ በቤተ ሙከራ ምርመራ እየተደረገበት ነው።
በቻይና የሚገኙ ባለሥልጣናት እና የዓለም ጤና ድርጅት የተከሰተው ቫይረስ 'ኮሮናቫይረስ' የተባለና በአፍንጫ እና በላይኛው ጉሮሮ ክፍል የሚከሰት የተለመደ ኢንፌክሽን እንደሆነ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
የዚህ ቫይረስ ዓይነቶች አንዳንዶቹ በጣም አስጊዎች ሲሆኑ ሌሎቹ የተለመዱና በቀላሉ የሚድኑ ናቸው።
ኮሮናቫይረስ በርካታ ዓይነቶች ያሉት ሲሆን ስድስቱ ብቻ በሰው ላይ በሚያስከትሉት ጉዳት ይታወቃሉ። በእርግጥ አዲስ የተከሰተው ቫይረስ ቁጥሩን ሰባት አድርሶታል።
በኮሮናቫይረስ የሚመጣውና 'ሪስፓራቶሪ ሲንድረም' (የመተንፈሻ አካላትን የሚጎዳው ቫይረስ) በቻይና መከሰት ከጀመረበት የአውሮፓዊያኑ 2002 ጀምሮ 774 ሰዎችን ሲገድል 8,098 ሰዎች ተይዘዋል።
"ከዚህ በፊት የተከሰተው ቫይረስ ያስከተለው የሚዘነጋ አይደለም፤ ለዚያ ነው አሁን በርካታ ስጋቶች እየተፈጠሩ ያሉት፤ ነገርግን እንዲህ ዓይነት በሽታዎችን ለመከላከል ተዘጋጅተናል" ሲሉ ዌልካም ትረስት ከተሰኘ የምርምር ተቋም ዶክተር ጆሴ ጎልዲንግ ተናግረዋል።
ቫይረሱ ምን ያህል አስጊ ነው?
ኮሮናቫይረስ የጉንፋን ዓይነት ምልክቶች ያሉት ሲሆን እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። ይህም አዲስ ቫይረስ በእነዚህ መካከል ላለ የጤና ችግር ሊዳርግ ይችላል ተብሏል። ቀላልም ያልሆነ ለሞትም የማይዳርግ።
"አዲሱን ኮሮናቫይረስ ምልክቶቹ ምን ያህል አስጊ እንደሆኑ ማወቅ እንፈልጋለን። ምልክቶቹ ከጉንፋን የበረቱ ናቸው፤ ስለዚህ ያ ነው ትኩረት የሚስበው፤ ይሁን እንጅ እንደ መተንፈሻ አካል ችግር ከባድ ላይሆን ይችላል" ሲሉ በኢድንበርግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርክ ውል ሃውስ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይረሱ ከየት መጣ?
በየጊዜው አዳዲስ ቫይረሶች ይከሰታሉ። ከአንደኛው ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ ይለወጣሉ፤ ነገር ግን በሰዎች ላይ ሲከሰቱ ልብ ተብለው አያውቁም።
"ከዚህ በፊት የተከሰተውን ካሰብን እና የተከሰተው አዲስ ኮሮናቫይረስ የመጣው ከእንስሳት ውሃ መጠጫ ነው" ሲሉ በኖቲንግሃም ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ጆናታን ቦል አስረድተዋል።
የመተንፈሻ አካል ላይ የሚከሰተው የጤና እክል በአብዛኛው በኤዥያ ከሚገኙ ትንንሽ ድመቶች ወደ ሰዎች ይተላለፋል።
የግመል ጉንፋን በመባል የሚታወቀው የመካከለኛው ምስራቅ በሽታ ከተቀሰቀሰበት የአውሮፓዊያኑ 2012 ጀምሮ ከተመዘገቡ 2 ሺህ 494 ምልክቱ ከታየባቸው ታማሚዎች 858ቱ ሞተዋል።
የትኞቹ እንስሳት ያስተላልፋሉ?
በውሃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንደ አሳ ነባሪ ያሉ አጥቢ እንስሳት ኮሮናቫይረስ ሊሸከሙ ይችላሉ። ሌሎች እንደ ዶሮ፣ ጥንቸል ፣ እባብ፣ የሌሊት ወፍ የቫይረሱ ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።
በዚህም ምክንያት ቫይረሱ በደቡባዊ ቻይና ውሀ፤ የባህር ምግቦች መሸጫ ገበያዎች ጋርም ተያይዟል፤ ነገር ግን ቫይረሱ የሚገኝበት ምንጭ ከተለየ በቀላሉ መከላከል ይቻላል ተብሏል።
ምንም እንኳን ከመተንፈሻ አካላት ጋር የተገናኙ ህመሞች ከሰው ወደ ሰው ቢተላለፉም አሁን ላይ ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም።
የሥርጭት መጠኑም ያን ያህል የተፋጠነ አይደለም። ምልክቱ የታየባቸው 59 ሰዎች ሃያ ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምልክቱ የታየባቸው ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ የተመዘገበ ታማሚ አለመኖሩም ለዚህ ማሳያ ነው።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተለይቶ በተዘጋጀ ቦታ ህክምና እየወሰዱ ሲሆን፤ ከተያዙ ሰዎች ጋር ግንኙነት የነበራቸው 150 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ክትትል እየተደረገላቸው ነው።
ተጓዦችን የሚመረምር የሙቀት መለኪያም ተዘጋጅቷል። የባህር ምግቦች ገበያዎች ለፅዳት ሲባል ተዘግተዋል።
ዶክተር ጎልዲንግ "በአሁኑ ሰዓት ተጨማሪ መረጃ እስከምናገኝ ድረስ ምን ያህል መጨነቅ እንዳለብን ማወቅ አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።
"የቫይረሱ ምንጭ ማረጋጋጫ እስክናገኝ ድረስ ግን ጉዳዩን ቀላል ነው ማለት አይቻልም" ሲሉም አክለዋል።














