ዛፎችና የአእምሮ ጤና ምን ያገናኛቸዋል?

ጫካ

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ዛፎች ሕይወትዎን ማዳን ይችላሉ፣ ደስተኛ ያደርጋሉ እንዲሁም ጠንካራ ጭንቅላት እንዲኖርዎ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይጫወታሉ ይላሉ በቅርቡ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች የሠሩት ጥናት።

የጀርመኑ ፈላስፋና ገጣሚ ሀርማን ሂስ እንደሚለው፤ ዛፎች የነፍስ መጠለያዎች ናቸው። ዛፎች በብዛት ያሉበት አካባቢ ድብርት ቦታ ሊኖረው አይችልም ይላል።

የዓለማችን ትልልቅ የሚባሉ ጸሀፍትም ቢሆኑ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ስለዛፎችና ጥቅማቸው ብዙ ነገር መጻፍ እያዘወተሩ ይመስላል።

ዛፎች ጎርፍን ለመከላከል፣ ድርቅን ለመከላከልና የአፈር መሸርሸርን ለመካከል ጠቃሚ እንደሆኑ ለብዙ ዓመታት በብዙ ባለሙያዎች የተጻፈ ቢሆንም ዛፎች ከሰው ልጆች አስተሳሰብና የጭንቅላት አሠራር ጋር ስላላቸው ቁርኝት ብዙም አልተባለም።

ብዙዎቻችን እንደምናስበው ንጹህ አየር እንድንተነፍስ ብቻ ሳይሆን ዛፎች በርካታ ጠቀሜታዎች አሏቸው። ዛፎችንና አረንጓዴ ተክሎችን ዝም ብሎ መመልከት በራሱ ማዕከላዊ የአዕምሮ ክፍላችንን እንደሚያረጋጋው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ዛፎችን መመልከት በጭንቅላታችን ውስጥ የሚመረተውን ኮርቲሶል የሚባለውን ለጭንቀት የሚያጋልጥ ንጥረ ነገር መጠን ይቀንሳል፣ የልብ ምትን ዝግ ያደርጋል፣ የደም ግፊትንም ይቀንሳል። ሌላው ቀርቶ የዛፎችን ፎቶ መመልከት እንኳን በጭንቅላታችን ውስጥ ጥሩ ስሜት ይፈጥራል።

ዛፎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሆስፒታል ተኝተው የሚገኙ ታማሚዎች በመስኮታቸው በኩል ዛፎችን ማየት ከቻሉ የመዳን ፍጥነታቸው ይጨምራል። ዛፎች ያላቸው የማረጋጋት አቅም ጭንቀትንና ህመመን እስከመቀነስ ይደርሳል።

ተፈጥሯዊ በሆኑ ዛፎች መካካል ሥራቸውን የሚያከናውኑ ሠራተኞችም ቢሆን ውጤታማነታቸው ከሌሎች ከፍ ያለ እንደሚሆን ጥናቶች ይጠቁማሉ።

እድሜያቸው ከ 12 እስከ 18 የሚሆኑ 9 ሺ በጎ ፈቃደኞችን ባሳተፈ አንድ ጥናት መሰረት፤ ተፈጥሯዊ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩት የድብርትና የጭንቀት መጠናቸው በእጅጉ የቀነሰ ነው።

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል 11.5 በመቶ የሚሆኑት የድብርት ምልክት ታይቶባቸው ነበር። የእነዚህን ተሳታፊዎች መኖሪያ መንደር ያጠናው ቡድን ልጆቹ በተጨናነቁ ህንጻዎችና ምንም አይነት ዛፎች በሌሉባቸው አካባቢዎች እንደሚኖሩ ደርሶበታል።

እንግሊዝ ውስጥ የአካላዊ፣ አዕምሯዊና መንፈሳዊ መረጋጋትን ለመፍጠር በሚል የተቋቋመ አንድ 'ዉድላንድ ትረስት' የሚባል ድርጅት አለ።

ድርጅቱ እንደሚለው፤ የድሮ ሰዎች ጭንቀትና ፍርሀት ያለባቸውን ሰዎች ጫካ ውስጥ ጥቂት ቀናት እንዲያሳልፉ ያደርጓቸው ነበር።

በጫካው ውስጥ ምግባቸውን ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረትና ለኑሯቸው ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ለመምረት በሚያደርጓቸው ውሳኔዎች መካከል ችግራቸውንና ጭንቀታቸውን ይረሱታል።

ምናልባት ምግባቸውን ካገኙና መጠለያቸውን ከሠሩ በኋላ የድሮው ጭንቀታቸው ቢመለስ እንኳን ዛፎቹን ነፋስ ሲያንቀሳቅሳቸው ሲመለከቱና የወፎችን ዝማሬ ሲሰሙ የመታደስ እንዲሁም የደህንነት ስሜት እንደሚሰማቸው ያምኑ ነበር።

በአንዳንድ ባህሎች ደግሞ የድብርትና የጭንቀት ጠባዮች የሚታዩባቸው ሰዎች ዛፎችን ረዘም ላለ ሰዓት እንዲያቅፉ ይደረጉ ነበር። ምናልባት ዛፍ ያቀፈ አንድ ሰው ብንመለከት ግራ ሊገባን ይችላል። ምንም ጥቅም የለውም ልንልም እንችላለን። ጉዳዩ ግን ወዲህ ነው ይላሉ ባለሙያዎቹ።

አንድ በድብርት የሚሰቃይ ሰው ሰውነቱ አንድ ዛፍን ሄዶ ስላቀፈ ችግሩ ሁሉ ጥሎት ሊሄድ እንደማይችል ይታወቃል። ነገር ግን ዛፉን በሚያቅፍበት ጊዜ በጥሞና ውስጥ ሆኖ የነፋስ ሽውታን መስማት እና የዛፉ ቅርንጫፎች ነፋስ ሲያንቀሳቅሳቸው መመልከት ከፍተኛ የሆነ የህሊና እርካታ ይሰጠዋል።