አውስትራሊያ፡ ወደ ጫካነት የተቀየረው ስታዲየም

የፎቶው ባለመብት, Unimo
በአውስትራሊያ የሚገኝ አንድ የእግር ኳስ ስታዲየም ለማዕከላዊ አውሮፓ ብርቅዬ የሆኑ ዛፎችን ብቻ ለማቆየት ወደ ጫካነት ተቀይሯል።
ስታዲየሙን ለዛፎች ምቹ አድርጎ ዲዛይን ያደረገው ክላውስ ሊትማን የተባለ ግለሰብ ሲሆን የአየር ንብረት ለውጥና የደን ምንጣሮን ለመከላከል በማሰብ ነው ሃሳቡን ያፈለቅነው ብለዋል አስተባባሪዎቹ።
300 ዛፎችን ማስተናገድ የሚችለው ስታዲየም በአካባቢው ያሉ መሰረታዊ ነገሮችን በሰባት ሳምንታት ውስጥ ተጠናቀውለት የዱር እንስሳትና አእዋፋ መሳብ እንደሚጀምር ይጠበቃል።
ስታዲየሙን ወደ ጫካነት የመቀየር ሃሳብ የመጣው ማክስ ፔይንትነር የተባለ ሰአሊ ወደፊት ሰው ልጅ የተፈጥሮ ሃብቶችን ልክ እንደ እንስሳት በተከለሉ ቦታዎች ብቻ ነው የሚያያቸው የሚለውን ሃሳቡን ያንጸባረቀበት ስእል ላይ መሰረት በማድረግ ነው።
በጥንቃቄ ተተክለው ያደጉትን ዛፎች ለህዝብ ይፋ ለማድረግ ብዙ ጊዜ የፈጀ ሲሆን ባሳለፍነው ሃሙስ ለጋዜጠኞች ብቻ ክፍት ሆኖ ነበር። በመቀጠል እሁድ ዕለት ደግሞ ለሁሉም ጎብኚ ክፍት ሆኗል። ለመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታትም ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Max Peintner
ዲዛይነሩ ሊትማን የማክስ ፔይትነርን ስዕል እ.አ.አ. በ1970 ተመልክቶት በጣም እንዳስገረመው ይናገራል። ስዕሉን መግዛት ቢፈልግም ቀድሞ ተሽጦ ስለነበር ሊሳካለት አልቻለም።
''ስዕሉን ገዝቼ የግሌ ማግረድ ካልቻልኩኝ ሌላው ቢቀር ወደ እውነታ ለምን አልቀይረውም የሚል ሃሳብ መጣልኝ።'' ብሏል ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ።
ክላግንፈርት በተባለችው ከተማ የሚገኘው 'ዎርተርሲ' የእግር ኳስ ስታዲየም እስከ 30 ሺ የሚደርሱ ተመልካቾችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን የአውሮፓ ቀዝቃዛ ወቅት ሲጀምር ዛፎቹ መልካቸውን ቀይረው አስገራሚ ውበት እንደሚላበሱ እየጠበቅን ነው ብለዋል አስተባባሪዎቹ።
ስታዲየሙን ለዛፎቹ ምቹ አድርጎ የማሰናዳቱን ስራ ከክላውስ ሊትማን ጋር በመሆን ያከናወነው ደግሞ የመንገድና ህንጻዎች ቅየሳ ባለሙያው ኤንዞ ኤኒያ ሲሆን ከዚህ በፊት ከዛፎችና ከባቢያዊ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ብዙ ልምድ ያካበተ ነው ተብሏል።
የዎርተርሲ ስታዲየም ባለቤትና በአውስትራሊያ ሁለተኛ ሊግ ሚጫወተው ክላግንፈርት የተባለው ቡድን ለጊዜው በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ አነስተኛ ስታዲየም ፈልጎ ልምምዱን እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
ለህዝብ ይፋ የሆነው የዛፎች ኤግዚቢሽን እስከ መጪው ጥቅምት 27 ድረስ ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን፤ ቀነ ገደቡ ሲያልፍ ግን ዛፎቹ ተነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ይዘዋወራሉ።













