የአማዞን እሳት ሕይወታቸውን ያሳጣቸው ጥንዶች

ኢዲ ሮድሪገስ እና ባለቤቷ ሮሚልዶ

የፎቶው ባለመብት, Family handout

የምስሉ መግለጫ, ኢዲ ሮድሪገስ እና ባለቤቷ ሮሚልዶ

የኢዲ ሮድሪገስ እና የባለቤቷ ሮሚልዶ ቤት እንዳልነበር ሆኗል። እነሱም እስከወዲያኛው አሸልበዋል።

የዛሬን አያድርገውና ጥንዶቹ ቤታቸውን በአማዞን በሚገኝ መንደር የሠሩት በኩራት ነበር።

ማቻዲንሆ ዴኦስቴ የምትባለው መንደር በደቡብ ምዕራብ ብራዚል ትገኛለች። በአካባቢው በተደጋጋሚ የሚነሳው እሳት ጥንዶቹን ያሰጋቸው ነበር።

በተለይም ዝናብ በሌለበት ወቅት በአቅራቢያቸው እሳት ሲነሳ 'አንድ ቀን እኛ ጓሮ ይደርስ ይሆን' ብለው ይፈሩ ነበር።

ነሐሴ 13 ቀን ጥንዶቹ የፈሩት ደረሰ፤ ቤታቸው በእሳት ጋየ፤ እነሱም ሕይወታቸውን አጡ።

የጥንዶቹ ቤት

የፎቶው ባለመብት, Family album

የምስሉ መግለጫ, የጥንዶቹ ቤት

ጥንዶቹ የሞቱት ቤታቸውን ለማዳን ሲጣጣሩ ነበር። ከኢድ ልጆች አንዷ ጄግስሌን ካርቫልሁ ለቢቢሲ እንዲህ ብላለች፦

"እዚ አካባቢ እሳት በመጠቀም መሬት ይመነጠራል፤ ያን ቀን ግን ንፋሱ ከቁጥጥር ውጪ ስለነበር እሳቱን ማጥፋት አልተቻለም፤ ሮጠው የሚያመልጡበት ጊዜ እንኳን አላገኙም።"

የአማዞን ደን በእሳት መጋየት ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። እሳቱ እየጨመረ መምጣቱን የሳተላይት ምስሎች ያሳያሉ። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአካባቢው የሚነሳው እሳት 76 በመቶ ጨምሯል።

ጥንዶቹ ይኖሩበት በነበረው አካባቢ ብቻ 6,500 የአማዞን ቦታዎች እሳት ተነስቷል።

የአማዞን ደን በእሳት መንደድ የዓለም መነጋገሪያ ከመሆኑም በላይ፤ የተለያዩ አገራት መሪዎች የብራዚል ፕሬዘዳንት ጃይር ቦልሶናሮ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱ እየጠየቁ ነው።

የቡድን 7 አገራት ለብራዚል የ 22 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለመስጠት መስማማታቸውን የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ቢናገሩም የብራዚሉ ፕሬዘዳንት አልተቀበሉም። የብራዚል አመራሮችም የውጪ ኃይሎች በብራዚል ፖለቲካ እጃቸውን ለማስገባት ጥረት እያደረጉ ነው ብለዋል።

ኢዲ ሮድሪገስ እና ባለቤቷ ሮሚልዶ ቤት የሠሩበትን መሬት የገዙት ለ10 ዓመት ብር አጠራቅመው ነበር። ጎረቤቶቻቸው ለፖሊሶች እንደተናገሩት፤ ቤታቸው በእሳት ሲያያዝ ጨክነው ጥለውት መሄድ አልቻሉም ነበር። እንደሌሎቹ የመንደሩ ነዋሪዎች እሳቱን ለማጥፋት ጥረት እያደረጉም ነበር።

በመንደሩ ይገኙ የነበሩ ዛፎች ተመንጥረው ስላለቁ እሳቱ ለመሰራጨት ጊዜ አልወሰደበትም።

ከኢድ ልጆች አንዷ የሆነችው ጄግስሌን እንደተናገረችው፤ ጥንዶቹ በቅርቡ የገዙትን የጣሪያ ንጣፍ ለማዳን ብዙ ደክመዋል።

"እቃቸውን እያወጡ እሳት ወዳልደረሰበት አካባቢ እየወሰዱ እንደነበር ጎረቤቶቻቸው ነግረውኛል።"

እሳቱ ከሁለት አቅጣጫ መጥቶ ቤቱን አውድሞታል

የፎቶው ባለመብት, João Messias Monteiro

የምስሉ መግለጫ, እሳቱ ከሁለት አቅጣጫ መጥቶ ቤቱን አውድሞታል

እሳቱ ከሁለት የተለያየ አቅጣጫ እየተቀጣጠለ ስለነበር ጥንዶቹ ራሳቸውን ማዳን አልቻሉም።

አንድ የአይን እማኝ ለፖሊስ እንደተናገሩት፤ እሳቱ ከቁጥጥር ውጪ ቢሆንም የአካባቢው ነዋሪዎች የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞችን አልጠሩም። "ሠራተኞቹን ያልጠሩት በደን ጭፍጨፋ ተጠያቂ እናደረጋለን ብለው ስለፈሩ ነው" ሲሉም አስረድተዋል።

የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች በአካባቢው የደረሱት ጥንዶቹ ሞተው በማግሥቱ (ነሐሴ 14) ነበር። ጥንዶቹ ሕይወታቸው ያለፈው በካርቦን ሞኖክሳይድ ታፍነው ነው ተብሏል።

ጥንዶቹ ዶሮና አሳማ ያረቡ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Family album

የምስሉ መግለጫ, ጥንዶቹ ዶሮና እሳማ ያረቡ ነበር

የጥንዶቹ ጎረቤቶች ከእሳቱ ተርፈዋል።

ጉዳዩን እያጣሩ ያሉት መርማሪ ስሌሶ ኮንድገስክ "እሳቱን ያስነሱት ሰዎች በግድያ ተጠያቂ ይደረጋሉ" ብለዋል።

ከኢድ ልጆች አንዷ የሆነችው ጄግስሌንም "ፍትህ እንሻለን" ብላለች።