ብዝኀ ሕይወት ምንድን ነው? ለምንስ ግድ ይሰጠናል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምድራችን ላይ እስትንፋስ ያለው ሁሉ ሕልውናው የአንዱ ከሌላኛው ጋር የተሳሰረ ነው።
በዓለም ላይ የተለያዩ ፍጥረታት አንዳቸው ከሌላቸው ጋር በሰመረ ጥምረት ይኖራሉ። አንዳቸው ከሌላቸው ጋር ያላቸው መስተጋብር እንዲሁም ከሚኖሩበት አካባቢ ጋር ያላቸው ግንኙነትም የተጣጣመ ነው።
የሰው ልጅም በዚህ የሕይወት ዑደት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ ሕይወቱም በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ፍጥረታት መኖር ጋር የተሳሰረ ነው።
ብዝኀ ሕይወት ምንድን ነው?
ሕይወት ያለው ሁሉ፣ እኛን ጨምሮ፣ በሚኖርበት ፕላኔት ላይ በዙሪያው የተለያዩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል። ይህንን ነው ብዝኀ ሕይወት የምንለው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተክሎች የምንተነፍሰውን አየር ያመርቱልናል፤ ንቦች ደግሞ ሰብሎች እንዲራቡ በማድረግ ውስጥ አይተኬ ሚና አላቸው። ፈንገስ ደግሞ አፈር ለምነቱን ጠብቆ አንዲቆይ ያደርጋል።
ስለዚህ ካልተበረዘው የተፈጥሮ ዓለም፣ የምንጠጣውን ኩልል ያለ ንፁህ ውሃ፣ ባመመን ጊዜ የምንፈወስበትን መድኀኒት እንዲሁም መንፈሳችንን የሚያድስ እይታ እናገኛለን።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከምድር ገፅ ላይ የአንድ ተክል ወይም እንስሳ ዝርያ መጥፋት ቀላል ሊመስል ይችል ይሆናል። ነገር ግን አንዳችን ከሌላችን ጋር በማይበጠስ ገመድ ስለተሳሰርን የአንድ ዝርያ መጥፋት ትልቅ ጉዳት ነው።
ስለምን ግድ ይሰጠናል?
አንድ ቤትን አስቡ። እናም አንድ ሰው ቤቱ ከተገነባበት ጡብ አንዱን መዞ ቢያወጣው ቤቱ ውበቱ እየደበዘዘ ጥንካሬውም እየደከመ ይሄዳል። በርካታ ጡቦች ሲወጡ ደግሞ በአጠቃላይ ቤቱ ይፈርሳል።
በምድርም ከአጠቃላይ የሕይወት ማዕቀፉ ውስጥ አንድ ዝርያ ሲጎድል፤ ብዝኀ ሕይወቱ ደካማ እየሆነ ይሄዳል፤ ያ ደግሞ በምድር ላይ ሕብር ሠርተው እየኖሩ ያሉ ፍጥረታትንም ያያደክማል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሁኑ ወቅት ዓለማችንን ስንመለከት መፃዒ ተስፋችን ጭጋግ የለበሰ ነው። ተፈጥሮ ሚዛኗ ተዛብቷል።
ምን እየሆነ ነው? ለምን?
ተመራማሪዎች በምድራችን ላይ የተለያዩ ዝርያዎች በሚሊየን ዓመታት አይተን በማናውቀው ፍጥነት እየጠፉና እየተመናመኑ ነው ይላሉ። ይህንን እያደረገ ያለው ደግሞ የሰው ልጅ ነው።
የደን መጨፍጨፍ፣ ለእርሻ፣ ለቤት ግንባታና ኢንደስትሪን ለማስፋፋት ተብለው የሚካሄድ ምንጣሮና ቃጠሎ ምድራችንን አደጋ ላይ ጥለዋታል።
አየሩን፣ አፈሩን እና ውሀውን እየበከልን በእነዚህ ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ፍጥረታትን አደጋ ላይ ጥለናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕገ ወጥ የዱር እንስሳት ንግድና አደን፣ ከተገቢው በላይ አሳ ማስገር እንስሳት በከፍተኛ ቁጥር እንዲሞቱና እንዲጠፉ እያደረገ ነው።
የሰው ልጅ እፅዋትንና እንስሳትን ከዚህ ቀደም ወደማይገኙበት የዓለማችን ክፍል እያጓጓዘ፤ በስፍራው ቋሚ ነዋሪ የነበሩት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈባቸው ይገኛል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአየር ጠባይ ለውጥ ምድራችንን እያናወጣት ነው።
ይህ ሁሉ ጥፋት ተስፋችን የተመናመነ ሊያስመስለው ይችላል። ግን ተስፋ አለን። እያንዳንዱ ግለሰብም ሆነ አገራትን የሚመሩ ባለስልጣናት ማድረግ የሚችሉት ነገር አለ።
መንግሥታት ሕገ ወጥ አደንንና የዱር እንስሳት ንግድን ቢከላከሉና ዝርያቸው ለመጥፋት ለተቃረቡ እንስሳት ልዩ ጥበቃ ቢያደርጉ ተፈጥሮን መታደግ እንደሚቻል ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ምን እናድርግ?
ማድረግ የምንችለው ነገር አለ።
የምንጠቀመውን ኃይል መቀነስ፣ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ በመጠቀም፣ አየርንና ምድሪቱን ከብክለት መታደግ፣ ነዳጅ በመቀነስ ሌሎች የኃይል አማራጮችን መጠቀም።
ከባቢ አየሩን የማይጎዱ ምርቶችን መጠቀምም ልናደርጋቸው ከምንችላቸው ነገሮች መካከል ይገኝበታል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሚኖሩበት አካባቢ አበባ በመትከል ንቦች ለሰብሎች መራባት ያላቸውን አስተዋፅኦ ማስቀጠል ይችላሉ።
አሁን ያለንበት ወቅት የተፈጥሮ አደጋ ጊዜ ይሰኛል። ስለዚህ ተፈጥሮ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ነገር እኛንም ይጎዳናል።













