ኮሮናቫይረስ፡ "ጭንቀት ላይ ነን" ኢትዮጵያዊቷ ከቻይና ውሃን

የፎቶው ባለመብት, SOLIANA AREGAWI
በቻይናዋ የዉሃን ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ዘርፍ ትምህርቷን አጠናቃ፣ ለአንድ ሴሚስተር ማንዳሪን ቋንቋ ለመማር በሚል ቆይታዋን ያስረዘመችው ሶልያና አረጋዊ፤ ወደ አገሯ የመመለሻ ቀኗን የቆረጠችው በዚሁ ወር ነበር።
ለአራት ዓመታት ያህል በታሪካዊዋ በጎርጎሳውያኑ 1893 የኪንግ ስርወ መንግሥትን ይመራ በነበረው ዛንግ ዚዶንግ የተመሰረተችው፣ ጥንታዊቷ የቻይና ዚኪያንግ ተቋም የአሁኗ ዉሃን ዩኒቨርስቲ ውስጥ የማይረሳ ጊዜም ነበራት።
የመጨረሻ ሳምንታቶቿን አንዳንድ የቀሯትን ነገሮች በማጠናቀቅ ላይ እያለች ነው አዲስ አይነት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃው፣ ከአራት መቶ ሰዎች በላይ ህይወትን በነጠቀው ኮሮናቫይረስ ምክንያት ካለችበት ከተማ መውጣት እንደማትችል ያወቀችው።
ከሳምንታት በፊት ትኩሳት (ፊቨር) እንደተከሰተና ጥንቃቄ አድርጉ፣ ጭምብል አጥልቁ የሚባሉ መልዕክቶች መተላለፍ ጀምረው የነበረ ቢሆንም እንደዚህ የከፋ ደረጃ ደርሶ ከአገር መውጣትና መግባት ይከለከላል ብላ ሶልያና አላሰበችም።
አስራ አንድ ሚሊዮን ህዝብ የሚኖርባት፣ ስምንተኛዋ ትልቋ የቻይና ከተማና የንግድ መናኸሪያዋ ዉሃን ፀጥ ረጭ ብላለች።
በያንግትዜና ሃን ወንዞች የተከፋፈለችው፣ የብዙ ሐይቆችና ፓርኮች የጥንታዊት ቻይና ስልጣኔ መገለጫ የሆነችው ዉሃን በኮሮናቫይረስ ምክንያት የተወረረች ከተማ መስላለች።
በቱሪስቶች የሚሞሉት ሙዚየሞች፣ በቡድሂስት አማኞች ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጠው ጉያን ቴምፕል (ምኩራብ)፣ በነዋሪዎቿ ዘንድ ልብን የሚሰርቀው የዉሃን ያንግትዜ ድልድይ፣ እነ ሰመር ሃውስ ፒዛ ባር፣ ዳሚያኖ የጣልያን ሬስቶራንት፣ አሎሃ፣ አቶሚየም ጭር ብለዋል።
ከዉሃን ዩኒቨርስቲ በሃያ ደቂቃ የምትገኘውና በማንታቀላፋው በሶልያና 'ዳውን ታውን' ሰፈርም እንቅስቃሴ ከጠፋ ሰነባበተ፤ ሶልያናም እየለመደችው ይመስላል።
"ድሮ ማታ ላይ ተኝቼ ራሱ መኪና ማለፍ አያቆምም፤ ውይ መተኛት ከባድ ነበር። ሁልጊዜም ሲያልፉ እንደቀሰቀሱኝ ነው። አሁን መኪናም የለም። ያስፈራል፤ የሞተች ከተማ መስላለች። እንዴ ዉሃን እንደዚህ ነበረች ወይ እንላለን?" ትላለች።
የሶልያና ሰፈር ብቻ አይደለም። ከተለያዩ አገራት በመጡ ቢያንስ ሦስት ሺህ ተማሪዎች የምትጨናነቀው ዉሃን ዩኒቨርስቲ እንቅስቃሴ አይታይባትም፤ ተማሪዎች ዶርማቸውን ከርችመዋል።

የፎቶው ባለመብት, SOLIANA AREGAWI
ኑሮ፤ መንቀሳቀስ በማይቻልባት ዉሃን
ቤት ውስጥ ቁጭ ማለት የማትወደው ሶልያና ያሁኑን አያድርገውና ዉሃንን ከጫፍ ጫፍ አዳርሳታለች። ብዙ ጓደኞችንም አፍርታባታለች። የተለያዩ ዝግጅቶችም ሲኖሩም ሶልያና አትቀርም።
በአሁኑ ሰዓት ግን ድንገተኛ ካልሆነ መኪናም ሆነ ሞተር መንዳት በከተማዋ ውስጥ ክልክል ነው። ከተማው ውስጥ የተመደቡት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አካላት ጥቂት ናቸው።
ከቤት መውጣትና መንቀሳቀስ ከተማዋ ውስጥ ባይመከርም ክልክል አይደለም፤ "ግን ወጥቼስ የት እሄዳለሁ ትላለች ሶልያና?"
ሁሉ ነገር ዝግ ነው በሰዓት ወስነው ከሚከፍቱት እነ ዋልማርትን ከመሳሰሉ ትልልቅ መደብሮች በስተቀር፤ ሆነም ቀረም ጭምብል ሳያጠልቁ እንቅስቃሴ ብሎ ነገር የለም።
ሶልያናም ሙሉ በሙሉ የሚያስፈልጓትን ግብይቶችን የምትፈፅመው የተለያዩ ድረገፆችን በመጠቀም ነው።
ሁሉ ነገር ፀጥ ረጭ ባለባት ዉሃን መንቀሳቀስ ከተከለከለ ሁለት ሳምንት ሊደፍኑ ነው፤ ቀኑስ ለሶልያና እንዴት ያልፋል፣ ይመሻል፣ ይነጋልስ?
ከእንቅልፏ የምትነሳው አርፍዳ ነው፤ በሱም የተወሰነውን ቀን ትገፋዋለች። 'ዳያሪዋ' ላይ ትፅፋለች፣ ማንበብ የምትፈልጋቸውን መፃህፍትና ጊዜ በማጣት የተወቻቸውን እያነበበች እንደሆነም በሳቅ በተሞላ ንግግሯ ገልፃለች።
ፊልም ማየት፣ ጓደኟቿ ጋር ማውራት፣ ቤተሰብ ጋር በመደወል መመለሻዋን በመናፈቅ ቀናቱን እያሳለፈች ነው።
"ወይ ቁጭ ብለሽ ታነቢያለሽ፤ ስልክ ታወሪያለሽ፤ መውጣት ብትፈልጊም ስለማትችይ ያው ቢሰለችም ምን ማድረግ ይቻላል" ትላለች።
ሶልያና ምንም እንኳን ከቤተሰቦቿ ጋር በቀን ሁለት ጊዜ የምታወራበት ጊዜ ቢኖርም ያለችበትን ሁኔታ አያምኑም።
"ቀን በቀን ነው የሚደውሉት፤ እናም ምን አዲስ ነገር አለ ትባያለሽ? ያው ምንም የለም፤ አትጨነቁ ደህና ነኝ፤ ሁሉ ነገር አለኝ እላቸዋለሁ" የምትለው ሶልያና ከውጭ ሆኖ ለሚያየው ሁኔታው ቢያስፈራም "እኔ እዚህ ስላለሁ ሁሌም አልደነግጥም። ይለመዳል" ትላለች ቀለል አድርጋ።
በመጀመሪያ ስለቫይረሱ ለቤተሰቦቿ አልነገረቻቸውም ነበር፤ ምክንያቱም በአንድ ሳምንት ውስጥ ተዘግቶ ሁሉ ነገር ይሻሻላል በሚል ግምት፤ ዜና ላይ ሲሰሙ ደወሉላት ብታስረዳቸውም ጭንቀቱ አልለቀቃቸውም።
ለእናቷ በተለይ ልጃቸውን ማረጋጋትም ሆነ እሷ ጋር መደወል በቂ አልነበረም፤ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሄዳቸውን በፈገግታ ሶልያና ትገልፃለች።
" እዚህ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎች መምህሮቻችንም ሆነ ዩኒቨርስቲው ስለሚሰጡን፤ አትሂጂ እያልኳት ነው የሄደችው" እናቷም አሻፈረኝ ብለው ጥያቄዎቻቸውን ጠይቀው፤ ስልክም ተቀብለው መጥተዋል ።
"ያው እንደ ወላጅ ያስጨንቃል፤ ምክንያቱም ምንም ማድረግ የማትችይበት ሁኔታ ሲሆን ትንሽ ያሳስባል" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Zhang Peng
የተማሪዎች ስጋትና መልሱን ጥያቄ
በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ መሆን በተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል። ምንም እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ኢትዮጵያውያን ባይኖሩም፤ ወደ አገራችን መልሱን በሚሉ በሺዎች በሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች ተሞልታለች።
ድምፃቸውን በዩኒቨርስቲው ግቢ እየተንቀሳቀሱ አይደለም እያሰሙ ያሉት፤ ሰውን በመፍራት፣ ቫይረሱን በመፍራት ኢንተርኔትን መርጠዋል። ከሰው ጋር ንክኪ የሚያስፈራበት ዘመን፤ የኢትዮጵያውን ተማሪዎችም በዚሁ ግራ መጋባት ውስጥ ናቸው።
በዉሃን ዩኒቨርስቲ ከሦስት መቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፤ በሁቤይ ግዛት ውስጥ በሚገኙ ከተሞችም ያሉ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ400 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች አሉ።
በዉሃንም ሆነ በአካባቢው የሚገኙ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የተገደበ ስለሆነ ብቸኛው የመገናኛ መንገዳቸውም በኢንተርኔት መልዕክት በመላላክ ነው።
ሶልያና ከተማሪዎች ማደሪያ ውጭ ተከራይታ በራሷ ስለምትኖር ሁኔታዎችን ቀለል ቢያደርግላትም በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚያድሩ ተማሪዎች ምግብ፣ ውሃም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች ቢቀርብላቸውም አንዳንዶች ቸልተኝነት እንዳለባቸው ከኢትዮጵያውያኑ ሰምታለች።
ተማሪዎቹ የቡድን (ግሩፕ) ቻት ስላላቸው ያሉበትን ሁኔታ፣ ስጋታቸውን እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮችን ይቀያየራሉ።
"አንዳንድ ተማሪዎች ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። ትምህርት ቤቱ ቸልተኝነት በማሳየቱ ወይም የሚገባቸውንና የሚያስፈልጋቸውን ባለመስጠቱ ይሆናል" ትላለች።
የምግብ እጥረት፣ የህክምና ቁሳቁሶች ለምሳሌ የጭምብል እጥረት በተደጋጋሚ የሚነሱ ጉዳዮች ነበሩ።
በሆዋጆንግ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ሳይንስ ኤንድ ቴክኖሎጂ በሲቪል ኢንጅነሪንግ ዲፓርትመንት የዶክትሬት ተማሪ የሆነችውና በቻይና ዉሃን ውስጥ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ዘሃራ አብዱልሃጅ በበኩሏ እነዚህ እጥረቶች የአንድ ሰሞን ችግር እንደነበሩ ነው።
አንድ ሰሞን የጭምብል እጥረት አጋጠመ በተባለበት ወቅት ህብረቱ ሪፖርት አድርጎ ፋርማሲ ሄደው መግዛት እንዲችሉ መመቻቸቱንና፤ የምግብ አቅርቦት ችግር አለ ከተባለም እንዲሁ ህብረቱ በሚያሳውቅበት ወቅት የቻይና መንግሥት ምላሽ ፈጣን መሆኑን ነው።
ምንም እንኳን በሁቤይ ግዛት ሁሉም ሰው እንቅስቃሴውን እንዲያቋርጥና፣ በቤቱ እንዲገደብ ቢወሰንም የቻይና መንግሥትም ማንኛውንም እርዳታ ለመለገስ መዋቅር ተዘርግቷል።
ቫይረሱን ለመግታት ከፍተኛ ዘመቻ ላይ እንደሆኑ ሶልያናም ሆነ ዘሃራ ምስክርነታቸውን የሚሰጡ ሲሆን በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ የውጭ አገር ተማሪዎችን የሚንከባከቡበትን ሁኔታም አድናቆቷን ዘሃራ ችራለች።
የቻይና መንግሥት በእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ ነፃ ምግብ ከማቅረብ በተጨማሪ የተማሪዎቹን ጉዳይ ለመቆጣጠር ፕሮፌሰሮች ተመድበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ያሉበትን የጤና ሁኔታ እንዲሁም ያለባቸውን ችግር ሌሎችንም ጉዳዮችን ለመከታተል ዓለም አቀፍ ቢሮዎች አሉ።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ደግሞ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት የሚወያዩበት እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን የሚያንሸራሽሩበት የቻት [የውይይት] ቡድን አላቸው።
አንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ችግር በሚፈጠርበት ወቅት ህብረቱ ለቆንስላው ሪፖርት ያደርጋሉ፣ ያ ፅህፈት ቤት ደግሞ ለዉሃን ባለስልጣናት ያሳውቃል፤ እነሱም የተዘረጋውን የራሳቸውን መዋቅር በመጠቀም ዩኒቨርስቲው ጋር ግንኙነት ይፈጥራሉ።
የሚያስፈልጓቸውን የምግብ አቅርቦት የጤና ቁሳቁሶችን በሟማላት ላይ የነበሩ ቢሆንም ነገር ግን በየዕለቱ ከሚሰሙ ዜናዎች ሁኔታዎች እየከፉ በመሄዳቸው ተማሪውን እንዲረበሽ አድርጎታል።
ተማሪዎቹ እስከመቼ በዚህ ሁኔታ እንቀጥላለን? ወደ አገራችን ብንሄድ? የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ መነሳቱን ተከትሎ ህብረቱ ተማሪዎቹን እንዲያስወጣ ጥያቄያቸውን ለኤምባሲ አስገብተዋል።
"የተማሪው እንቅስቃሴው ስለተገደበ በራሱ የሚያስጨንቅ ነገር አለው። ግፊትም ስለበዛብን ኤምባሲው እንዲያስወጣን ጥያቄውን አቅርበናል" ትላለች ዘሃራ።
በተለይም አሜሪካና ፈረንሳይን የመሳሰሉ አገራት ዜጎቻቸውን ማውጣታቸውን ተከትሎ ሌሎች የእስያ አገራት ተማሪዎቻቸውን ወስደዋል። ያ ሁኔታ በራሱ ግፊት እንደፈጠረ ዘሃራ ታምናለች።
ሶልያናም ሆነ ዘህራ በቫይረሱ የተያዙ ግለሰቦች ቁጥር መጨመር እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ያሉበት ጭንቀት ተማሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩን ነው የሚጠቅሱት።
"ተማሪው ከቤተሰቡ ጋር ሲያወራ፤ ቤተሰብ ይጨነቃል የሚሰማው ነገር በጣም ከባድ ነው፤ ስለዚህ እስከመቼ ነው እንደዚህ የምንቆየው 'ኳረንታይን' መደረግ ካለብን እንደረግ ከቤተሰቦቻችን መቀላቀል ይሻለናል" በማለት በተደጋጋሚ እንደሚናገሩ ዘሃራ ትናገራለች።
ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ መልስ ይሰጠን እያሉ እየጠየቁ ሲሆን ማህበሩም "ታገሱን ዝግጀት ይፈልጋል። ኤምባሲውም የራሱ የሆነ ሂደት አለው፤ የውጭ ጉዳይም እንዲሁ፤ ይህንን ሂደት እየተጠባበቅን ነው ያለነው" የሚል ምላሽም በመስጠት ላይ ናቸው።
ሆነም ቀረም "ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦች በጣም አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን እያሰቡ እንዲጨነቁ አልፈልግም፤ ከራሳቸው ዜጋ ባልተናነሰ መልኩ ክትትል እየተደረገልን ነው" በማለት ቤተሰቦች መረጋጋት አለባቸው ትላለች።
ሁሉም ሰው በጭንቀት ላይ እንደሆነ የምትናገረው ሶልያና "ምክንያቱም መልስ እየጠበቅን ነው፤ ለምንም ነገር መዘጋጀት አለብን፤ እሱ ላይ ትንሽ ግራ ስለተጋባን፤ አብዛኞቻችን መወዛገብ ሁኔታ ላይ ነን" ትላለች።
በተለይም ህብረቱ ደብዳቤ ካቀረበ በኋላ ኤምባሲው ምላሽ አለመስጠቱ ለሶልያናም ሆነ ለተማሪዎቹ አሳሳቢ በመሆኑ ሶልያና ጉዳዩን ወደ ትዊተር በመውሰድ ለሚመለከታቸው አካላት "እባካችሁ መልስ ስጡን" በማለትም ጠይቃለች፤ ተማፀናለች።
በትዊተርም ምላሽ ስጡን ብላ ትዊት ካደረገች በኋላም ብዙዎች በጎ ምላሽ ቢሰጧትም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ፀጥታ አስጨንቋታል። ከአራት መቶ በላይ ተማሪ ማስተናገድ ቀላል እንዳልሆነና ጫናውንም ብትረዳም "ዝም ከማለት ምንም አይነት ምላሽ ይሻላል" ትላለች።
በአብዛኛው እየቀረበ ያለው ጥያቄ ከዉሃን ታስወጡናላችሁ ወይ? ከሆነስ እንዴት ነው የሚሆነው የሚል ነው?
ተማሪዎቹን ከዉሃን ማስወጣት ከተቻለ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል? ምክንያቱም ሙቀት መለካት ብቻ ሳይሆን በሽታው ሳይገለጥ 14 ቀናት ሊቆይ ስለሚችል፤ የክትትሉ ሁኔታ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው።
ሌሎች አገራት በለይቶ ማቆያ ለአስራ አራት ቀን እንደሚያስቀምጡ ኢትዮጵያስ ያንን ትከተላለች ወይ የሚሉት ጥያቄዎችም የተማሪዎቹ መወያያ ሆኗል።
የምርመራ ሁኔታው ምን ይመስላል? ተመርምረው ቫይረሱ ከተገኘ ኢትዮጵያ በቂ ህክምና የማድረግ ዝግጅቱም ሆነ ብቃቱ አላት ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች በተማሪዎች ዘንድ እየተንሸራሸሩ ነው።
ይህ የተማሪዎቹ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አፍሪካ የተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ በሽታ ቢያጋጥማት ያላት ዝግጅት ላይ ስጋት እንዳለው ገልጿል።
"ተማሪዎችን ካወጣሽ እነዚህን ሁሉ ተሟልተው መሆን አለበት፤ ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ማውጣት ችግር ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ቫይረሱ ይኑርብሽ አይኑርብሽ ላታውቂ ትችያለሽ፤ እዚህ ተጋላጭ ነን" የምትለው ሶልያና ነገር ግን ተማሪዎቹን በለይቶ ማቆያ ውስጥ ለማቆየት ዝግጅት ካለ መውጣቱን ትመርጣለች።
"ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል የመቆየቱ ሁኔታ ተማሪዎቹን የበለጠ እያጋለጣቸው እንጂ የሚጨምረው ነገር የለም" በማለትም ተማሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, SOLIANA AREGAWI
ምላሽ ቢሰጣቸው ነገሮችን ያቀላል የምትለው ሶልያና "እናስወጣችኋለን ከተባለ ዝግጅት ታደርጊያለሽ፤ አይሆንም ከተባለም ምግብ እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን ወደ ማከማቸት ትሄጃለሽ" ትላለች።
ቀድሞም ለመዘጋጀት፣ ቲኬትም ለመግዛት፣ የቤት ኪራይ ልክፈል አልክፈል የሚሉ ጥያቄዎችም እንዲሁ መነጋገሪያ ጉዳዮቻቸው ከሆኑ ከራረሙ።
የኢትዮጵያ ኤምባሲ በቻይና ምክትል ሚሽን መሪ የሆኑት አቶ ገነት ተሾመ የተማሪዎቹ ጥያቄ በማህበሩ በኩል እንደቀረበና፤ አጠቃላይ ሁኔታውንም እየገመገሙት እንዳሉና የቻይና መንግሥትም ሁኔታውን ለመቆጣጠር አበክሮ እየሰራ ከመሆኑ አንፃር ተማሪዎቹ ከቤት እንዳይወጡ ምክር እየሰጧቸው ነው።
"በእኛም አገር በኩል ይሄ ዝግጅትም፣ ውሳኔም ይጠይቃል፤ ዝም ብለን ከዚህ ማውጣት አይቻልም ፤ መጀመሪያ መውጣታቸው መታመን አለበት፤ በቂ ኳረንታይን ያስፈልጋል የሚያስፈልጋቸውን መሰረታዊ ፍጆታዎች ምግብና መገልገያዎች ለተማሪዎቹ በነፃ እየቀረበ ነው" ብለዋል።
የተማሪዎቹን የመውጣት ፍላጎት ጉጉት ቢገባቸውም፤ ከተማው በኳረንታይን የሚቆየው እስከ ጥር ሰላሳ ከመሆኑ አንፃር መንቀሳቀስ ሲፈቀድ ነገሮች እንደሚስተካከሉ አቶ ገነት ተስፋ ያደርጋሉ።
ሁሉንም ነገር አጠናቃ በዚህ ወር ወደ አገሯ ለመጓዝ ቲኬቷን ቆርጣ የነበረችው ሶልያና እስካሁን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ባታውቅም፤ ጉንፋንም ሆነ ሙቀት ሰው ሲሰማቸው ያለው ድንጋጤ ከፍተኛ ነው።
ያለው የአየር ፀባይ ብርድ ከመሆኑም አንፃር ጉንፋን ሰው በሚታመምበት ወቅት እንዲሁም ምልክቶቹም ስለሚመሳሰሉ በድንጋጤ በተደጋጋሚ ድንገተኛ ቁጥሮችን ይደውላሉ ትላለች።
"የሆነ ቀን ሳስነጥስ ደንግጨ ነበር፤ የሌለ ጥርጣሬ ነው የሚፈጥረው።"
የጤና ተቋማት የኮሮናቫይረስን በማከም በከፍተኛ ሥራም ስለተጠመዱ እንዳው ማንኛውም ስሜት ሰው ስለተሰማው ተዘሎ አይኬድም፤ ድንገተኛ ተደውሎና ምልክቶቹን እርግጠኛ ካልሆኑ ዝም ብሎ መሄድም አይመከርም።
ቻይና ኮሮናቫይረስን ለማከም ከአቅሟ በላይ መሆኑ እየተነገረ ሲሆን በብቸኝነትም በሽታውን ማከም የሚችሉ ሆስፒታሎችን ገንብታለች።
በተለይ ሶልያና ትምህርቷን ከማጠናቀቋ አንፃር እንዲሁም ለመመለስ በዝግጅትም ላይ ስለነበረች መቼ ነው ሊሻሻል የሚችለው? የሚለውን እርግጠኛ አለመሆን፣ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመር እንዲሁም ሌሎች አገሮችም ላይ እየተከሰተ መሆኑ የሚያሳስቧት ጉዳዮች ናቸው።
"ትጨነቂያለሽ ራስሽን ደግሞ ያንን ያህል አታስጨንቂውም፤ ያው ያለሽበት ሁኔታ ስለሆነ ችለሽ ትቀጥያለሽ። ያው መቆጣጠራቸው አይቀርም፤ ግን ጊዜ ይፈጅባቸዋል ብዬ አስባለሁ።"












