ኬንያ ተማሪዎቿን ከቻይና ዉሃን ከተማ ልታስወጣ ነው

የኢንዶኔዥያ ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, HANDOUT

ኬንያ የኮሮናቫይረስ መነሻ በሆነችው ዉሃን ከተማ ያሉ 85 ተማሪዎቿን ልታስወጣ ነው።

ሲመለሱም በለይቶ ማቆያ እንዲገቡም ተወስኗል።

የአገሪቱ የጤና አስተዳደር ፀሐፊ ለፓርላማው የጤና ኮሚቴ እንዳስታወቁት የማስወጣቱ ሥራ የሚከናወነው ቻይና በዉሃን ከተማ ላይ የጣለችው የመውጣትና የመግባት እግዳን ስታነሳ ነው።

የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ቢሮም ከተማሪዎቹ ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ የፓርላማ አባሏ ዶር ሜርሲ ምዋንጋንጊ ተናግረዋል።

ለተማሪዎቹ በጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የለይቶ ማቆያ ሁለት ክፍሎች የተዘጋጀላቸው ሲሆን፤ በተመሳሳይም በኬንያታ ሆስፒታል የህክምና ክትትል የሚደረግባቸው ለይቶ ማቆያ ክፍሎች እንደተዘጋጁም ገልፀዋል።

በተጨማሪም በናይሮቢ እንዲሁ ተጨማሪ ለይቶ ማቆያዎች ተዘጋጅተዋል።

ወደ ዉሃን ከተማ መግባትና ከከተማዋ የመውጣት እግድ መቼ እንደሚነሳ ግልፅ ባይሆንም ብዙ አገራት ዜጎቻቸውን አውጥተዋል።

ከአፍሪካም ዜጎቿን በማውጣት ግብፅን የቀደማት የለም።

የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አፍሪካ የተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ በሽታ ቢያጋጥማት ያላት ዝግጅት ላይ ስጋት እንዳለው መግለጹ ይታወሳል።

በአፍሪካ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ድንገተኛ መከላከል ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሚካኤል ያዎ "አፍሪካ የደከመ የጤና መዋቅር ነው ያላት" ብለዋል።

በአህጉሪቷ በአጠቃላይ ቫይረሱን መመርመር የሚችል ላብራቶሪ ያለው ስድስት ብቻ ሲሆን፤ እነዚህም ናይጄሪያ፣ ማዳጋስካር፣ ሴራሊዮን፣ ጋናና ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ናቸው ብለዋል።

እስካሁን ባለውም የደቡብ አፍሪካ ላብራቶሪ 71 ተጠርጣሪዎችን የመረመረ ሲሆን ሁሉም ነፃ ናቸው ተብሎም ተመልሷል።

የዓለም አቀፉ ኤጅንሲ በበኩሉ ለሃያ አራት አገራት ቫይረሱን መመርመር የሚያስችል እርዳታን እንደሚለግስ አስታውቋል።

ቫይረሱ 426 ሰዎችን በቻይና የገደለ ሲሆን፤ አንድ ግለሰብም ከቻይና ውጪ ሞቷል።

በአፍሪካ ውስጥ ኮሮና ቫይረስ ባይገኝም፤ በቻይና ተማሪ የሆነ አንድ ካሜሮናዊ ቫይረሱ ተገኝቶበታል።