ካሜሮናዊው ተማሪ በኮሮናቫይረስ በመጠቃት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆነ

ካሜሮናዊ ተማሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሃያ አንድ ዓመቱ ካሜሮናዊው ተማሪ በኮሮናቫይረስ በመያዝ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሆኗል።

ትምህርቱን በቻይና ያንግትዜ ዩኒቨርስቲ ይከታተል የነበረው ተማሪ ዉሃን ከተማ ለጉብኝት በሄደበት ወቅት በበሽታው መያዙን ከዩኒቨርስቲው የወጣው መግለጫ ያስረዳል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ወደሚኖርበት ከተማ ጂንግዙ ከተመለሰም በኋላ በበሽታው መያዙ ታውቋል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ኪልያን ኒጋላ ከካሜሮኗ መዲና ያውንዴ እንደዘገበው ይህ ዜና መሰማቱ በካሜሮናውያን ዘንድ ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።

300 የሚሆኑ ካሜሮናውያን በዉሃን የሚገኙ ሲሆን ወደየትም መንቀሳቀስም ስለማይቻል የውሃ፣ ምግብና ሌሎችም ቁሳቁሶች እጥረትም በማጋጠሙ ችግር ላይ ናቸው ተብሏል።

ዩኒቨርስቲው ለተማሪው ቤተሰቦች እንዲሁም ለኤምባሲው ማሳወቁንና ህክምናም እየተከታተለ ነው ተብሏል።

በአሁኑ ሰዓት የሰውነት ሙቀቱ እየተስካከለ እንደሆነ፣ የምግብ ፍላጎቱም መመለሱን እንዲሁም በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም ዩኒቨርስቲው በመግለጫው አትቷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ተማሪዎች በቻይና የሚገኙ ሲሆን፤ ኮሮናቫይረስ በከፍተኛ ሁኔታ መዛመቱን ተከትሎ በርካታ መንግሥታት ከቻይና በተለይም ከዉሃን እንዲያወጧቸው ቢማፀኑም ምላሽ አላገኙም።

ባለፈው ሳምንት በዉሃን የሚገኙ ካሜሮናውያን ለፕሬዚዳንታቸው ፓውል ቢያ ቤጂንግ የሚገኘው ኤምባሲ ምንም እርዳታ እያደረገላቸው እንዳልሆነ እንዲሁም መሰረታዊ የሸቀጥ ፍጆታዎችም እጥረት አለ በማለት ደብዳቤ ፅፈው ነበር።