ቻይና አሜሪካን ኮሮናቫይረስን አስመልክቶ ፍራቻ እየነዛች ነው ስትል ወነጀለች

ቻይና አሜሪካን ኮሮና ቫይረስ ፍራቻ በመንዛት ወነጀለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻይና መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መዛመትን አስመልክቶ አሜሪካ ፍራቻን እየነዛች ነው ስትል ከሰሰች።

አሜሪካ ኮሮናቫይረስ ብሔራዊ የጤና ቀውስ ነው በማለት ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት ማወጇን ተከትሎ ነው ቻይና አሜሪካን የምትወነጅለው።

በአሜሪካ አዋጅ መሰረት ቻይናን በባለፉት ሁለት ሳምንታት የጎበኙ ማንኛውም የውጭ አገር ዜጎች አሜሪካ መግባት አይፈቀድላቸውም።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንይንግ እንደገለፁት የአሜሪካ ድርጊት "ፍራቻን መፍጠርና ማስፋፋት እንጂ ምንም የሚፈይደው የለም" ብለዋል።

ሰኞ ዕለት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ሁዋ አሜሪካ እርዳታን ከመለገስ ይልቅ "ፍራቻን ትነዛለች" በማለት ወንጅለዋታል።

ቻይናዊ መንገደኞችንም ሆነ ከቻይና የሚመጡ በረራዎችን ለማገድ አሜሪካ የመጀመሪያዋ አገር ስትሆን የኤምባሲ ሰራተኞቿንም በተወሰነ መልኩ አስወጥታለች ብለዋል።

"በሽታውንም የመከላከልም ሆነ የመቆጣጠር አቅማቸው የዳበሩ እንደ አሜሪካ ያሉ አገሮች ናቸው ከአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ምክሮች በተፃራሪ መንገድ እንዲህ አይነት አላስፈላጊ እግዶች እየጣሉ ያሉት" ብለዋል።

የአሜሪካን እግድ ተከትሎም አውስትራሊያ እና ሌሎች በርካታ አገራት ከቻይና የሚመጡ በረራዎችን አግደዋል።

የአለም ጤና ድርጅት በረራዎችን ማገድ ከሚጠቅመው በላይ ሊጎዳ እንደሚችል ምክሮችን እየለገሰ ነው።

መረጃዎች እንዳይተላለፉ እንቅፋት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የህክምና ቁሳቀሱሶች በቀላሉ እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ፤ እንዲሁን አጠቃላይ የአገራትን ኢኮኖሚ ይጎዳል።

ከዚህ በተጨማሪም ተጓዦች በህገወጥ መንገድ ድንበሮችን እንዲያቋርጡ በር ስለሚከፍት የቫይረሱን በፍጥነት የመዛመቱን ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ሊያሻቅበው ይችላል ይላል ከአለም ጤና ድርጅት የተገኘው መረጃ።

እስካሁን ባለው መረጃ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 17 ሺ የደረሰ ሲሆን ለ361 ህይወት መቀጠፍም ምክንያት ሆኗል።

ከቻይና ውጭ 150 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም የተረጋገጠ ሲሆን በፊሊፒንስም አንድ ሞት ተከስቷል።

የአሜሪካ እርምጃ ምንን ያካትታል?

ከአስር ቀናት በፊት አሜሪካ የኮሮናቫይረስ መነሻ ከሆነችው ሁቤ ግዛት፣ ውሃን ከተማ የሚገኙ ከአንዳንድ የአደጋ ጊዜ ስራተኞች በስተቀር የአሜሪካ ዜጎች በሙሉ ለቀው እንዲወጡ አዛለች።

የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው ሲል ማወጁን ተከትሎ ማንኛውም የአሜሪካ ዜጋ ሆነ በሙሉ ቻይናን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፋለች።

ከዚህም በተጨማሪ በሁቤ ግዛት ቆይታ ያደረገ ማንኛውም አሜሪካዊ ለአስራ አራት ቀናት ያህል በለይቶ ማቆያ ክትትል እንደሚደረግም አስታውቃለች።