ከቻይና ውጪ የመጀመሪያው ግለሰብ በኮሮና ቫይረስ ሞተ

የፊሊፒንስ የጤና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ኮሮና ቫይረስ የዓለም ስጋት መሆኑ ቀጥሎ ፊሊፒንስ ውስጥ አንድ ግለሰብ በቫይረሱ ህይወቱ ማለፏ ተረጋግጧል። ከቻይና ውጪ በቫይረሱ ሰው ሲሞት ይህ የመጀመሪያው ነው።

የ 44 ዓመቱ ቻይናዊ ግለሰብ በሁቤ ግዛት በምትገኘው ዉሃን ከተባለችው ከተማ የመጣ ሲሆን ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውም በዚችው ከተማ ነበር። የዓለምአቀፉ ጤና ድርጅት እንዳስታወቀው ግለሰቡ ፊሊፒንስ ከመድረሱ በፊት በቫይረሱ ተይዞ ነበር።

እስካሁን በኮሮና ቫይረስ ከ 300 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ያለፈ ሲሆን አብዛኛዎቹ ደግሞ ከሁቤ ግዛት ናቸው። በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ 14 ሺ በላይ እንደደረሰም ታውቋል።

አሜሪካ፣ አውስትራሊያ እና ሌሎች በርካታ ሀገራት ከቻይና የሚመጡ በረራዎችን አግደዋል።

ከቻይና ተጉዞ ፊሊፒንስ ውስጥ ህይወቱ ያለፈችው ግለሰብ ከእሱ በተጨማሪ አብራው የነበረችው የ 38 ዓመቷ ቻይናዊ ባለቤቱ በቫይረሱ እንደተያዘች ማረጋገጣቸውን የሀገሪቱ የጤና ኃላፊዎች አስታውቀዋል።

በፊሊፒንስ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ የሆኑት ራቢንድራ አቤያሲንግ ዜጎች እንዲረጋጉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። '' ከቻይና ውጪ በቫይረሱ ሰው ሲሞት ይህ የመጀመሪያው ነው። መርሳት የሌለብን ግን ግለሰቡ በሽታውን ከቻይና ይዞት መምጣቱን ነው'' ብለዋል።

ሁኔታው በቻይና ምን ይመስላል?

የቻይና ባለስልጣናት እንደገለጹት ትናንት (ቅዳሜ) ብቻ በሁቤ ግዛት 45 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። ይህም ቁጥር የሟቾችንም ቁጥር ወደ 304 ከፍ አድርጎታል።

በተጨማሪ 2590 አዲስ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። በአጠቃላይም ቻይና ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 14 ሺ 380 ደርሷል።

ምንም እንኳን የቻይና ባለስልጣናት ይህን ይበሉ እንጂ ቁጥሩ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል በርካቶች ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። በእነሱ ግምት መሰረትም ቫይረሱ መጀመሪያ በተገኘባት ዉሃን ከተማ ብቻ ከ75 ሺ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሳይያዙ አልቀረም።

ከዉሃን ከተማ በስተምስራቅ የምትገኘውና ስድስት ሚሊየን ሰዎች የሚኖሩባት ሁዋንግጋንግ ከተማ ከንቲባ በበኩላቸው በከተማዋ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በመጪዎቹ ቀናት ሊጨምር እንደሚችል ገልጸዋል።

አክለውም ከዉሃን የሚገቡ መንገደኞች ላይ እገዳ ከመጣሉ በፊት እንኳን እስክ 700 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከዉሃን ወደ ሁዋንግጋንግ ገብተዋል ብለዋል።

ኮሮና ቫይረስ ምንድነው?

የቻይና ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት በአገራቸው የተከሰተው በሽታ መንስኤው ኮሮና በሚባል ቫይረስ ምክንያት ነው።

ቀደም ሲል ሰዎችን የሚያጠቁ ከዚህ ቫይረስ ጋር ዝምድና ያላቸውና የሚመሳሰሉ የታወቁ ስድስት አይነት የቫይረሱ ቤተሰቦች አሉ፤ አሁን የተገኘው አዲሱ ሰባተኛ እንደሆነ ተነግሯል።

በሽታው ሲጀምር በትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ተከትሎት ይከሰታል፤ከዚያም ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን በማስከተል አንዳንድ ህሙማንን የሆስፒታል ውስጥ ህክምና እንዲያስፈልጋቸው ሊያደርግ ይችላል።

በአራት ሰዎች ላይ ከሚከሰተው ይህ በሽታ አንዱ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ። በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ማስነጠስና የአፍንጫ ፈሳሽ ላይታይበት ይችላል።

የኮሮና ቫይረስ ቀለል ካለ የጉንፋን ምልክቶች አንስቶ እየከፋ ሲሄድ እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።

ከሰሞኑም የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው ሲል አውጇል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክትር ቴድሮስ አድሃኖም ይፋ እንዳደረጉት ለዚህ ውሳኔ ዋነኛው ምክንያት "በቻይና የተከሰተው ነገር ሳይሆን በሌሎች አገሮች እየሆነ ያለው ነው" ብለዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታ ወረርሽኝ ተከስቶ ከዚህ አይነት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይህ ስድስተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም ኤችዋን ኤን ዋን የተባለው ኢንፍሉዌንዛ፣ ኢቦላ፣ ፖሊዮ፣ ዚካና በድጋሚ የተከሰተው ኢቦላ ምክንያት ነበሩ።

በሽታው የተያዙ ሰዎችን ለሞት እስኪያደርሳቸው የተወሰነ ጊዜን ስለሚወስድ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል የተወሰኑት እስካሁንም ሊሞቱ ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል።

በተጨማሪም ምን ያህል እስካሁን ያልተመዘገቡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።