ኮሮናቫይረስ፡ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከዚህ ቀደም በሳይንስ እንደማይታወቅ የተነገረለት ቫይረስ ቻይና ውስጥ አደገኛ የሳምባ በሽታን ቀስቅሶ ወደ ሌሎች አገራትም እየተዛመተ ነው።
በመጀመሪያ ላይ ከአንድ ወር በፊት በቻይናዋ የዉሃን ከተማ መገኘቱ የተዘገበው ቫይረስ እስካሁንም ከአንድ መቶ በላይ ሰዎችን በሽታው ገድሏል።
እስካሁንም በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጠ ከ4500 በላይ ሰዎች ሲኖሩ ባለሙያዎች ይህ ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ ይገምታሉ።
ይህ ወረርሽኝ በቁጥጥር ስር ሊውል ይችላል ወይስ አስቸጋሪና አደገኛ ሆኖ ይቆያል?
ቫይረሱ ምንድ ነው?
የቻይና ባለስልጣናት እንዳረጋገጡት በአገራቸው የተከሰተው በሽታ መንስኤው ኮሮና በሚባል ቫይረስ ምክንያት ነው።
ቀደም ሲል ሰዎችን የሚያጠቁ ከዚህ ቫይረስ ጋር ዝምድና ያላቸውና የሚመሳሰሉ የታወቁ ስድስት አይነት የቫይረሱ ቤተሰቦች አሉ፤ አሁን የተገኘው አዲሱ ሰባተኛ እንደሆነ ተነግሯል።
የበሽታው ምልክቶች?
በሽታው ሲጀምር በትኩሳት ቀጥሎም ደረቅ ሳል ተከትሎት ይከሰታል፤ከዚያም ከሳምንት በኋላ የትንፋሽ ማጠርን በማስከተል አንዳንድ ህሙማንን የሆስፒታል ውስጥ ህክምና እንዲያስፈልጋቸው ሊያደርግ ይችላል።
በአራት ሰዎች ላይ ከሚከሰተው ይህ በሽታ አንዱ እጅግ የከፋ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በቫይረሱ የተጠቃ ሰው ማስነጠስና የአፍንጫ ፈሳሽ ላይታይበት ይችላል።
የኮሮና ቫይረስ ቀለል ካለ የጉንፋን ምልክቶች አንስቶ እየከፋ ሲሄድ እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።
የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታው ክስተት ቻይና ውስጥ አሳሳቢ እንደሆነ ቢገልጽም፤ እንደ ኤቦላና የወፍ ጉንፋን የበሽታው ሁኔታ ዓለም አቀፍ የሕዝብ የጤና ስጋት ነው ብሎ ለማወጅ አልወሰነም።
ምን ያህል አደገኛ ነው?
እስካሁን ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከ100 በላይ ሰዎች እንደሞቱ ታውቋል፤ ምንም እንኳን ቁጥሩ አስተማማኝ ባይሆንም በበሽታው ተይዘዋል ተብለው ከተረጋጋጡ ሰዎች ቁጥር አንጻር የሟቾቹ ቁጥር ዝቅተኛ ነው።
በሽታው የተያዙ ሰዎችን ለሞት እስኪያደርሳቸው የተወሰነ ጊዜን ስለሚወስድ በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጡ ሰዎች መካከል የተወሰኑት እስካሁንም ሊሞቱ ይችላሉ ተብሎ ተሰግቷል።
በተጨማሪም ምን ያህል እስካሁን ያልተመዘገቡ በበሽታው የተያዙ ሰዎች እንዳሉ ማወቅ አስቸጋሪ በመሆኑ ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቫይረሱ ከየት መጣ?
በተለያዩ ጊዜያት አዳዲስ ቫይረሶች ይገኛሉ።
እነሱም ሳይታወቁ ከአንድ ዝርያ ወደ ሌላ ዝርያ እየተሸጋገሩ ወደሰው ይደርሳሉ።
በአሁኑ ወቅት የተከሰተው አብዛኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በቻይናዋ ዉሃን በተባለችው ግዛት ውስጥ ከሚገኝ የደቡብ ቻይና ባሕር አካባቢ ካለ የአሳ መሸጫ ገበያ ነው።
ቫይረሱ ከየትኞቹ እንስሳት ተነሳ?
የትኞቹ እንስሳት የቫይረሱ አስተላላፊዎች እንደሆኑ ከታወቀ ችግሩን ለመቆጣጠር እጅግ ቀላል እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከባሕር ውስጥ የሚገኙ እንስሳት የኮሮና ቫይረስን እንደሚሸከሙ የታወቀ ሲሆን፤ በደቡባዊ ቻይና ውስጥ የሚገኘው የባሕር ምግቦች የጅምላ መሸጫ ገበያ ውስጥ ግን ዶሮዎች፣ ጥንቸሎች፣ እባቦችና ሌሎችም እንስሳት ስለሚገኙ እነሱም የበሽታው ምንጮች ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይነገራል።
ለምን ቻይና?
በሽታው ለምን ቻይና ውስጥ ተከሰተ ለሚለው ጥያቄ የዘርፉ ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዉልሃውስ ምክንያት ሲያስቀምጡ በሕዝብ ብዛትና ተጠጋግቶ በመኖር እንዲሁም ቫይረሱን በውስጣቸው ከሚይዙ እንስሳት ጋር በሚኖር የቅርብ ንክኪ ሳቢያ ነው ይላሉ።
አክለውም "በሽታው ቻይና ውስጥ ወይም ቻይና ባለችበት የዓለማችን ክፍል ውስጥ መከሰቱ ማንንም አላስደነቀም" ሲሉ ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
በምን ያህል ፍጥነት ይተላለፋል?
መጀመሪያ ላይ የቻይና ባለስልጣናት ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም ቢሉም አሁን ግን በዚህ መንገድ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል።
ሳይንቲስቶች እንደደረሱበትም በበሽታው የተያዘ እያንዳንዱ ሰው ቫይረሱን ከአንድ እስከ ሦስት በሚገመቱ ሰዎች ድረስ ሊያስተላልፍ ይችላል።
በተጨማሪም ቫይረሱ በእራሱ ጊዜ ተዳክሞ የሚጠፋ እንዳልሆነም ተነግሯል።
የቫይረሱን መስፋፋት ለማስቆም ቻይና ውስጥ የተወሰደው እርምጃ ችግሩ የተከሰተባቸውን ከተሞች መዝጋት ነው።
በሽታው መቼ ይተላለፋል?
የቻይና ሳይንቲስቶች እንደሚሉት በበሽታው የተያዙ ሰዎች የበሽታው ምልክቶችን ከማሳየታቸው በፊት አንስቶ ቫይረሱን ወደ ሌሎች ማስተላላፍ ይችላሉ።
በበሽታው በመያዝና ምልክቶቹ መታየት በሚጀምርበት ጊዜ ያለው የመራቢያ ጊዜ ከአንድ ቀን አስከ ሁለት ሳምንት የሚወስድ ነው።
ለንደን በሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ውስጥ የተላላፊ በሽታዎች ክፍል ውስጥ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዌንዲ ባርክሌይ እንደሚሉት በሳምባ ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች ምንም ምልክት ሳያሳዩ ከሰው ወደ ሰው የመተላላፍ ባህሪይ አላቸው።
ነገር ግን አሁን ባለው ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ከዚህ ቀደም እንደተከሰቱት ወረርሽኞች ዓለም አቀፋዊ የበሽታ ስጋት እንዳልሆነ እየተነገረ ነው።
በምን ያህል ፍጥነት ይዛመታል?
አዳዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በቀላሉ ሊለዩ የቻሉት ቻይና ሰዎቹን ለማወቅ የሚያስችላትን አቅሟን ማሻሻል በመቻሏ ነው ይባላል።
ነገር ግን የወረርሽኙ የመስፋፋት መጠንን የሚያመለክት መረጃን ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ሆኗል።
ነገር ግን ባለሙያዎች እንዳሉት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እስካሁን ከተነገረው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ቫይረሱ አደገኛ ሊሆን ይችላል?
የቻይና ብሔራዊ የጤና ኮሚሽን እንዳስጠነቀቀው የኮሮና ቫይረስ የመሰራጨት አቅም እየተጠናከረ ነው። ነገር ግን ከቫይረሱ ባህርይ መቀየር ጋር በተያያዘ ያለው ስጋት ግልጽ አይደለም።
ስለዚህም ይህንን ለማወቅ ሳይንቲስቶች በቅርበት ክትትል እያደረጉ ያሉት።
ኮሮና ቫይረስን ማስቆም ይቻላል?
አሁን ባለው ሁኔታ ቫይረሱ በራሱ መንገድ አይቆምም፤ ብቸኛው ሊያስቆመው የሚችለው የቻይና ባለስልጣናት የሚወስዱት እርምጃ ነው።
ሰዎች በቫይረሱ እንዳይያዙ የሚያደርግ የመከላከያ ክትባትም የለውም። ብቸኛው አማራጭ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር እንዳይገናኙ ማድረግ ነው።
ይህ ማለት ደግሞ፡
- የሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብ
- ሰዎች እጃቸውን በደንብ እንዲታጠቡ ማድረግና
- በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎችን ለብቻቸው መከላከያ ባጠለቁ የህክምና ባለሙያዎች እንዲታከሙ ማድረግ ማለት ነው።
ቫይረሱ እንዳለባቸው የሚያረጋግጡ ባለሙያዎች ራሱ ከበሽተኞቹ ጋር መነካካት አለመነካካታቸውን የሚያረጋግጥ ሌላ ሰፊ ሥራ ያስፈልጋል።
በቻይና ሳይንቲስቶች የቫይረሱ ታካሚዎችን ሊፈውስ ይችላል ብለው ተስፋ ያደረጉበትን መድሃኒት እየተጠቀሙ ነው።
ቢሆንም ግን ገና በሂደት ላይ ያለ ከመሆኑ አንጻር ሁለቱ ጸረ ቫይረስ መድሃኒቶች (ሎፒናቫይር እና ሪቶናቫይር) ለብቻቸው ወይም ከሌላ መድሃኒት ጋር ተቀምመው ፈውስ ያመጣሉ ብሎ ለመናገር አሁን ጊዜው አይደለም።
እነዚህ መድሃኒቶች የሳርስና ሜርስ ወረርሽኝ ተከስቶ በነበረበት ወቅትም ጥቅም ላይ ውለው ነበር።
የቻይና ባለስልጣናት የሰጡት ምላሽ?
ቻይና በሌላው ዓለም ያልታየ አንድ አዲስ ነገር አድርጋለች፤ ቫይረሱ የተገኘባትን የዉሃን ግዛትን በጊዜያዊነት ሙሉ በሙሉ ዘግታለች።
36 ሚሊዮን ህዝብን የእገዳው አካል በሆኑባቸው ሌሎች ከተሞች ላይ የጉዞ ማዕቀብ ጥላለች።
በብዛት መሰባሰብና የቱሪዝም መዳረሻዎች ለጊዜው ክልከላ ተጥሎባቸዋል። የተወሰነው የታላቁ የቻይና ግንብ ክፍልም እንዳይጎበኝ ተዘግቷል።
የቫይረሱ ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚገመተው የእንስሳት ግብይትም እንዳይካሄድ እገዳ ተጥሎበታል።
ቫይረሱ ማዕከል ያደረጋት የዉሃን ግዛት ሁለት ሆስፒታሎችን እየገነባች ሲሆን በድምሩ 2 ሺህ 3 መቶ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አልጋዎች ይኖሯቸዋል።
ዓለም ለቫይረሱ የሰጠው ምላሽ?
በርካታ የእስያ አገራት ከቻይና ዉሃን ግዛት የሚመጡ ሰዎችን ምርመራ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። የዓለም የጤና ድርጅትም ከዚህም የከፋ የቫይረሱ ስርጭት ሊኖር እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ሲንጋፖርና ሆንግ ኮንግ ከዉሃን ግዛት የሚመጡ የአውሮፕላን ተጓዦች ላይ ጥብቅ ምርመራ እያደረጉ ነው፤ የእንግሊዝና የአሜሪካ ባለስልጣናትም በጉዳዩ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።
ይሁንና እንደዚህ ዓይነት ምርመራዎች ውጤታማ ናቸው ወይ? የሚለው ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው።
ምክንያቱም በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምንም ምልክት ሳይታይበት ለሁለት ሳምንታት ሊቆይ ስለሚችል፤ የመጀመሪያውን ምርመራ ካለፈ ከቀናት በኋላ በመዳረሻ አገሩ ውስጥ ህመሙ ሊጀምረው ይችላል።
የሙያተኞቹ ጭንቀት?
"አሁን ላይ በርካታ መረጃ እስካለን ድረስ እንዴት እንደተጨነቅን ለማወቅ በጣም አስቸጋሪ ነው።"
"ምንጩ ከየት እንደሆነ እስኪረጋገጥ ድረስ ነገሮች ከባድ እንደሆኑ ይቀጥላሉ" ብለዋል በቫይረሱ ላይ እየተመራመሩ ያሉት ዶ/ር ጎልዲንግ።
ሌላኛው በዘርፉ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ባል በበኩላቸው ደግሞ "ማንኛውም የሰው ልጅን የሚያጠቃ አዲስ ቫይረስ በመጣ ቁጥር ሊያስጨንቀን ይገባል፤ ምክንያቱም የመጀመሪያ የመከላከያ ደረጃውን አልፏልና" ይላሉ።
"አንዴ ቫይረሱ በሰው ህዋስ ውስጥ ከገባ በኋላ ለራሱ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በፍጥነት የሚራባበትን መንገድ ያመቻችና በጣም አደገኛ ይሆናል።
"ቫይረሱ እንዲስፋፋ ዕድል ሊሰጠው አይገባም" ይላሉ።
ክትባት ወይም መድሃኒት አለው?
እስካሁን ባለው የለውም።
ምንም እንኳ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሥራዎች በሂደት ላይ ያሉ ቢሆንም፤ ምርምሮች እንደሚያሳዩት ሜርስ በተባለው የኮርኖ ቫይረስ ላይ የተቀመመው ክትባት ሥራውን ሊያቀለው ይችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።
ሆስፒታሎችም የጸረ ቫይረስ መድሃኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳላቸውና እንደሌላቸው የማረጋገጥ ሥራ እየሰሩ ነው።
ሎፒናቫይር እና ሪቶናቫይር ከተባሉ ሁለት መድሃኒቶች የተቀመመው መድሃኒት የሳርስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ነበር። በቻይናም ሙከራ ተደርጎበታል።














