ኮሮናቫይረስና የነዳጅ ዘይት ምን አገናኛቸው?

ነዳጅ ጫኝ መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስ የማይነካው ነገር እንደሌለ እየታየ ነው። በየሰበብ አስባቡ እያሻቀበ የነበረውን ነዳጅ ዘይትን ሊነካው ዳርዳር እያለ ነው።

በሽታው አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ጊዜ የዓለማችን ትልልቆቹ የነዳጅ አምራች አገራት በሽታው ካስከተለው ችግር ለመቋቋም በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ምርታቸው ሊቀንስ ይችላል እየተባለ ነው።

የነዳጅ ዋጋን ለመደገፍ እርምጃ እንዲወሰድ እየተጠየቀ ባለበት በአሁኑ ወቅት የነዳጅ አምራች አገራት ማህበር የሆነው ኦፔክ እና አጋሮቹ በዚህ ሳምንት ስብሰባ እንደሚቀመጡ እየተጠበቀ ነው።

በጥር ወር መጀመሪያ ላይ የነዳጅ ዋጋ በዓመት ውስጥ ከታየው ከፍ ብሎ በ20 በመቶ ካሻቀበ በኋላ አሽቆልቁሎ ዝቅተኛው ዋጋው ላይ ይገኛል።

ስለምን ይህ የቫይረስ ወረርሽኝ እንዲህ ያለው ከፍተኛ ተጽእኖን በዓለም አቀፉ የኃይል ገበያ ላይ ሊያስከትል ቻለ?

የነዳጅ ዋጋ ለምን በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ?

የቻይናዊያን አዲስ ዓመት የበዓል ጊዜ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል በበሽታው ምክንያት በመራዘሙና የጉዞ እገዳ በመደረጉ ፋብሪካዎች፣ ቢሮዎችና መደብሮች ዝግ ሆነው ይገኛሉ።

ይህም ማለት አስከ 14 ሚሊዮን በርሜሎችን በቀን ውስጥ የምትጠቀመውና የዓለማችን ትልቋ የድፍድፍ ነዳጅ ገዢ አገር የሆነችው ቻይና ማሽኖቿን ለማንቀሳቀስ፣ ለተሽከርካሪዎችና ለኤሌክትሪክ ኃይል ወትሮ ከምትፈልገው ነዳጅ ዘይት በእጅጉ የቀነሰውን እንድትጠቀም አድርጓታል።

በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጓቸውን በረራዎች በማቋረጣቸው የተነሳና በቻይና ውስጥ ባለው የጉዞ እገዳ ሳቢያ በረራዎች በመቀነሳቸው ለአውሮፕላን ነዳጅ ያለው ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል ተብሎ ይታሰባል።

ብሉምበርግ በዚህ ሳምንት እንደዘገበው የቻይና ዕለታዊ የድፍድፍ ነዳጅ ፍጆታ በ20 በመቶ ቀንሷል። ይህም ማለት ብሪታኒያና ጣሊያን በአንድ ላይ በቀን የሚያስፈልጋቸውን ነው።

በዚህም ሳቢያ በቻይና መንግሥት የሚተዳደረው የእስያ አህጉር ትልቁ የነዳጅ ማጣሪያ ሲኖፔክ በየቀኑ የሚያጣራውን የድፍድፍ ነዳጅ መጠን በ600 ሺህ በርሜሎች ቀንሷል። ይህም ከሥራው 12 በመቶው አቁሟል ማለት ሲሆን ከ10 ዓመታት በላይ ባለው ጊዜ ውስጥ ከፍተኛው ቅናሽ ነው።

በነዳጅ ዘይት ላይ የታየው ከፍተኛ ቅናሽ የኃይል ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳሳሰበው የዘርፉ ባለሙያዎች እየተናገሩ ነው።

የወረርሽኙ ተጽእኖ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ

በነዳጅ ፍላጎት ላይ የተከሰተው ከፍተኛ ቅናሽ በቻይና ውስጥ የተከሰተውን የሥራ መቀዛቀዝን የሚያሳይ ግልጽ ምልክት ነው። በተጨማሪም ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ቻይናን ካጋጠማት የኢኮኖሚ ዕድገት መቀነስ ክስተት ውስጥ ዝቅተኛው ማጋጠሙ ደግሞ የነዳጅ ፍጆታዋን የበለጠ ይቀንሰዋል ተብሏል።

የተባሉት በቻይና የሳይንስ አካዳሚ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑነት ዣንግ ሚንግ እንደሚሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ባሉት ሦስት ወራት የአገሪቱን ዓመታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከ5 በመቶ በታች ሊያወርደው ይችላል።

ያደጉት አገራት እድገታቸውን ለማጠናከር ትግል በሚያደርጉበት ጊዜ ቻይና የዓለማችን ሁለተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚና ለዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ናት።

የዓለም ገንዘብ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ክሪስታሊና ጆርጂዮቫ ባዚህ ሳምንት እንዳሉት ወረርሽኙ ቢያንስ ለአጭር ጊዜ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገትን ያቀዛቅዘዋል፤ ነገር ግን የወደፊቱን ለመናገር አሁን ጊዜው ገና እንደሆነም አመልክተዋል።

ነዳጅ አምራቾች ምን ማድረግ አለባቸው?

እያሽቆለቆለ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ለማሳደግ ታላላቆቹ የዓለም ነዳጅ ዘይት አምራቾች ለገበያ የሚያቀርቡትን ምርት በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንደሚወያዩ እየተነገረ ነው።

የኮሮናቫይረስ ክስተት ለነዳጅ የለውን ፍላጎት እንዲቀንስ በማድረጉ ምክንያት የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ማኅበር የሆነው ኦፔክ አባል የሆነችው ኢራን ሰኞ ዕለት እየወደቀ ያለውን የነዳጅ ዋጋ ለመደገፍ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በይፋ ጠይቃለች።

የኦፔክ አባል አገራትና ሩሲያ በዚህ ሳምንት ያደርጉታል ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ ላይ በቀን ለገበያ ከሚያርቡት የነዳጅ ምርት ከ500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን በርሜል የሚደርሰውን ለመቀነስ ይወያያሉ ተብሏል።