ኮሮናቫይረስ፡ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ነን ያሉት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ላኩ

ወደ አገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን

የፎቶው ባለመብት, Social media

ኮሮናቫይረስ በተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ሁቤ ግዛት ዉሃን ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች 'ወደ አገራችን እንመለስ' ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ደብዳቤ መፃፋቸውን የተማሪዎቹ ኅብረት ፕሬዝዳንት ዘሃራ አብዱልሃዲ ለቢቢሲ ገለፀች።

በዉሃን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ኅብረት 'ወደ አገራችን መልሱን' የሚለውን የተማፅኖ ደብዳቤ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም መላካቸውን ጠቁመዋል።

ተማሪዎቹ ቤይጂንግ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሳምንታት በፊት ወደ አገራቸው ለመመለስ ጥያቄ ማቅረባቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

የቻይና መንግሥት በወረርሽኙ ምክንያት መውታትም ሆነ መግባት ከከለከለባት የዉሃን ከተማ መውጣት የሚችሉበትን ሁኔታ ቢያመቻች አብዛኞቹ ተማሪዎች ወጪያቸውን ራሳቸው ሸፍነው ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደሚፈልጉ ኅብረቱ ለተማሪዎቹ አሰራጭቶት በነበረው መጠይቅ ለማረጋገጥ ችሏል።

ምንም እንኳ የቻይና መንግሥት አስፈላጊ ነገሮችን እያቀረበላቸው ቢሆንም ተማሪዎች ከባድ የሥነ ልቦና ጫና ላይ በመሆናቸው የግድ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ ለመፃፍ መገደዳቸውን ዘሃራ ትናገራለች።

በዋጆንግ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ያለች ስሟ እንዲገለፅ ያልፈለገች ተማሪ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስለምትኖር የምግብ አቅርቦት ቢኖራትም ከአንድ ወር በላይ በአንድ ክፍል ውስጥ በርና መስኮት ተዘግቶ "በቫይረሱ ከአሁን አሁን ተያዝኩ አልተያዝኩ" በሚል ከባድ የሥነ ልቦና ስቃይ ውስጥ እንዳለች ለቢቢሲ ገልፃለች።

"በቀን ሦስት ጊዜ ከሚመጣው ምግብ በየትኛው ምክንያት በቫይረሱ እያዝ ይሆን ብዬ በጣም እጨነቃለሁ። ምክንያቱም ቫይረስ ነው አይቼ ምጠርገው ነገር አደለም፤ አየሩን ይቀይርልኛል ብዬ ኤሲ አበራለሁ ብሶብኝ መስኮት ከከፈትኩ በጭንቀት ጌታ ሆይ አደራህን እያልኩ ነው" በማለት ያለችበትን ሁኔታ ለማስረዳት ትሞክራለች።

ወረርሽኙ በፈጠረው ተመሳሳይ የሥነ ልቦና ጫና ምክንያት ከቅርብ ጓደኞቻቸው ጋር እንኳ መግባባት ያቃታቸው ተማሪዎች መኖራቸውን የምትናገረው የተማሪዎቹ ኅብረት ፕሬዝዳንት ዘሃራ "የቀን ቅዥት ደረጃ የደረሱ ተማሪዎች አሉ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ዘሃራ እንደምትለው የአንዳንዶቹ ተማሪዎች የሥነ ልቦና ችግር ህክምና ወደሚያስፈልግበት ደረጃ የደረሰ በመሆኑ የዩኒቨርሲቲ ኃላፊዎችን ማነጋገር ሁሉ ግድ ሊል ይችላል። በተለይም በነገሮች ይደናገጡና ይረበሹ የነበሩ ልጆች አሁን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል።

አንድ ክፍል ውስጥ አብሮት የሚኖር ጓደኛው ምን ዓይነት የሥነ ልቦና ችግር ላይ እንዳለ የገለፀልን አንድ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ "በዚህ ሳምንት ያየሁበት ነገር አብሬው የኖርኩት ጓደኛዬ አልመስል ብሎኛል። ነገሩ በጣም ሲያሳስበን ለዩኒቨርሲቲው አሳውቀናል" ያሉበትን ሁኔታ ገልጿል።

በተጨማሪም ከአራት ቀናት በፊት የካዛክስታን ዜጋ የሆነች ተማሪ በቫይረሱ መያዝ ደግሞ ይበልጥ ብዙዎቹን እንደረበሻቸው ይህ ተማሪ ይናገራል።

በዉሃን የተማሪዎች ኅብረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደብዳቤውን የላከው ከትናንት በስቲያ ሲሆን ደብዳቤው ለመድረሱ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ማረጋገጫ እንደደረሳቸው የኅብረቱ ፕሬዝዳንት ዘሃራ ገልፃለች።

ምንም እንኳ ተመሳሳይ ማረጋገጫ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ባይደርሳቸውም ደብዳቤያቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መድረሱን በሌላ መንገድ ማረጋገጣቸውንም ተናግራለች።

ቢቢሲ የተማሪዎቹን ደብዳቤና ጥያቄ በተመለከተ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የበሽታውን ጉዳይ በዋናነት ከሚከታተለው ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ በቻይና የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች ወደ አገራቸው ለመመለስ በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ መንግሥት መጀመሪያ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል የሚል ምላሽ መስጠቱ የሚታወስ ነው።

በግልፅ ባይሆንም እስካሁን በመንግሥት እየተሰጣቸው ያለው ምላሽ ተማሪዎቹን ላይቶ ማስቀመጥ የሚቻልበት ቦታ የለም የሚል እንደሆ ዘሃራ ትገልፃለች።

ተማሪዎቹ መንግሥት ወደ አገራቸው መልሷቸው በለይቶ ማከሚያ ቢያስቀምጣቸውም ሆነ ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን ለማድረግ የሚያስችለውን እርምጃ ቢወስድ ተባባሪ እንደሆኑ ኅብረቱ በደብዳቤው ላይ አስፍሯል።

ተማሪዎቹ ለቢቢሲ እንደገለጹት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላት በሚል ከመንግሥት ለእያንዳንዳቸው የተላከላቸውን 400 ዶላር ከትናንት ጀምሮ እየወሰዱ ነው።