በኮሮናቫይረስ የተያዙት ቶም ሃንክስና ሪታ ዊልሰን ከሆስፒታል ወጡ

ቶም ሃንክስ እና ሪታ ዊልሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው የሁለት ጊዜ የኦስካር አሸናፊ ተዋናይ ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ በአውስትራሊያ ህክምና ሲከታተሉ ከነበረበት ሆስፒታል መውጣታቸው ተዘገበ።

ጥንዶቹ በአውስትራሊያዋ ጎልድ ኮስት የተገኙት የኤልቪስ ፕሪስሊ ሕይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ፊልም ለመስራት ነበር።

የ63 ዓመቱ ቶም ሃንክስ ባለፈው ሐሙስ እሱም ባለቤቱም በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ያሳወቀው ከዚያው ነበር።

ቶም ሃንክስና ባለቤቱ በሆስፒታል አስፈላጊው እርዳታ ተደርጎላቸው ቢወጡም አሁንም እዚያው አውስትራሊያ ክዊንስላንድ ውስጥ በተከራዩት ቤት ራሳቸውን ለይተው እንደሚቀመጡ ተገልጿል።

የኦስካር ተሸላሚው ቶም ሃንክስ ብቻ ሳይሆን በኮሮናቫይረስ የተያዘው እንግሊዛዊ-ሴራሊዮናዊ ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባም በቫይረሱ መያዙን በትናንትናው እለት በትዊተር ገፁ ላይ አስታውቋል።

ኢድሪስ ኤልባ እንዳለው ምንም ዓይነት የህመም ስሜት ባይኖርበትም አግኝቶት የነበረ ሰው በቫይረሱ ስለተያዘ እንደተመረመረና በውጤቱም እሱም ኮሮናቫይረስ እንደያዘው መታወቁን ገልጿል።

"ጥሩ ነኝ እስካሁን ምንም ምልክት የለኝም አትደናገጡ" ብሏል ኢድሪስ በትዊተር መልዕክቱ።

ምንም እንኳ የሰው ዘር የተከፋፈለ ዓለም ላይ የሚኖር ቢሆንም በእንዲህ ያለው ጊዜ ግን አንዱ ለሌላው አጋርነቱን ማሳየት አለበት የሚል መልዕክቱንም አስተላልፏል።

ኢድሪስ ካለፈው አርብ ጀምሮ ራሱን ለይቶ መቆየቱንም ተናግሯል።