ቶም ሐንክስ እና ባለቤቱ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸውን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኦስካር አሸናፊው ተዋናይ ቶም ሐንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን አውስትራሊያ ውስጥ ተመርምረው ኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ገለፁ።
ሐንክስና ዊልሰን ብርድ በመታመማቸው ነበር ህክምና ፈልገው ኩዊንስላንድ ወደሚገኝ ሆስፒታል የሄዱት።
አሁን ራሳቸውን በቤታቸው ነጥለው መቀመጣቸውን በኢንስታግራም ገፁ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ላይ አስታውቋል ሃንክስ።
ቶም ሐንክስ ወደ አውስትራሊያዋ ጎልድ ኮስት ያቀኑት የኤልቪስ ፕሪስሊን የሕይወት ታሪክ ለመስራት ነበር።
በትናንትናው ዕለት ፣ ዕሮብ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ደረጃ ላይ መድረሱን መግለጫ ሰጥቶ ነበር።
ቶም ሐንክስ በኢንስታግራም መልዕክቱ ላይ " ድካም ይሰማን ነበር፤ ልክ ብርድ እንደታመመ ሰው፣ ሰውነታችንንም ይቆረጣጥመን ነበር። ሪታ ሄደት መጣ የሚል ብርድ ብርድ የማለት ስሜት ነበራት" ብሏል።
ከዚህ በኋላ ነው ምርመራ ለማድረግ ወስነው የተመረመሩት። የምርመራቸው ውጤት እንደሚያሳውም ሁለቱም ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ቶም ሐንክስ ፎረስት ጋምፕ እና ሴቪንግ ፕራይቬት ራያን በተሰኙ ፊልሞቹ የሚታወቅ ሲሆን አካዳሚ አዋርድ አሸናፊም ነው።
ከቶም ሐንክስ ጋር ፊልሙን እየሰራ የነበረው ኩባንያ " የኩባንያችን አባላት ጤንነትና ደህንነት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው፤ እንዲሁም ከእኛ ጋር በዓለም ዙሪያ ለሚሰሩ ሁሉ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉና መከላከል እንዲችሉ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለን" ብለዋል።
አውስትራሊያ ውስጥ እስካሁን ድረስ 130 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ሞት ግን አልተመዘገበም።
አውሮፓ ውስጥ እስካሁን ድረስ ማንኛውንም እንቅስቃሴ የገደበችው ጣሊያን ስትሆን ከምግብ መሸጫ መደብሮችና ከመድሃኒት ቤቶች ውጪ ሁሉም ነገር ተዘግቶ ፀጥ ረጭ ማለቱ ተሰምቷል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ከአውሮፓ ወደ አሜሪካ የሚደረጉ ማንኛውንም የአየር ጉዞዎች አግደዋል።













