የአውስትራሊያ ተመራማሪዎች ሰውነታችን የኮሮናቫይረስን ሊከላከል የሚችልበትን መንገድ መለየት ቻሉ

በሽታን ተከላካይ ህዋሳት መታየት ከጀመሩ በኋላ የበሽተኛው ሳንባ ሲያገግም የሚያሳይ ራጅ

የፎቶው ባለመብት, PETER DOHERTY INSTITUTE

የምስሉ መግለጫ, በሽታን ተከላካይ ህዋሳት መታየት ከጀመሩ በኋላ የበሽተኛው ሳንባ ሲያገግም የሚያሳይ ራጅ

የአውስትራሊያ ሳይንቲስቶች የሰውነታችን በሽታን የመከላከል ሥርዓት እንዴት አድርጎ ኮቪድ-19 [ኮሮናቫይረስን] ሊዋጋው እንደሚችል ለመለየት ችለዋል።

'ኔቸር' በተሰኘው የህክምና መጽሔት ላይ ዛሬ በወጣው የምርምር ግኝት መሰረት፤ ሰዎች ከኮሮናቫይረስ እየዳኑ ያለው ከጉንፋን በሚድኑበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አረጋግጠዋል።

ባለሙያዎቹ እንዳሉት በዚህ ወቅት የትኞቹ የሰውነት በሽታን መከላከያ ህዋሳት እንደሚታዩ መለየት በቀጣይ ክትባት ለመስራት ያግዛል።

በዓለም ዙሪያ እስካሁን ከ160 ሺህ በላይ በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ሲኖሩ ከ6500 በላይ ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን በወረርሽኙ አጥተዋል።

"በምርምር ለማወቅ የተቻለው ጠቃሚ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ይህ የሰውነት የመከላከያ ሥርዓታትን በምን መልኩ የኮሮናቫይረስን እንደሚዋጋ በመረዳት በኩል የመጀመሪያው በመሆኑ ነው" ሲሉ የምርምሩ አካል የሆኑት ካትሪን ኬደዜርስካ ተናግረዋል።

ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አንጻር ተመራማሪዎች የደረሱበት ይህ ግኝት "ፈር ቀዳጅ" እንደሆነ ተነግሮለታል።

የሜልበርን ፒተር ዶሬቲ የበሽታዎችና በሽታን የመከላከል ተቋም ውስጥ የሚገኙት ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች ባገኙት ውጤት አድናቆትን አግኝተዋል።

አስካሁን በርካታ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች የዳኑ ሲሆን፤ ይህም የሰው ልጅ በሽታን የመከላከል ሥርዓት በተሳካ ሁኔታ ቫይረሱን ተቋቁሞ ማሸነፍ ይችላል ማለት ነውም ተብሏል።

በዚህ የምርምር ግኝትም ለመጀመሪያ ጊዜ ኮቪድ-19ን ሊከላከሉ የሚችሉ አራት አይነት የተፈጥሮ በሽታን መከላከል የሚችሉ ህዋሳትን ለይተው አግኝተዋል።

ህዋሳቱ ቀደም ያለ ሌላ የጤና ችግር የሌለባቸውና ከቀላል እስከ መካከለኛ ሁኔታ ውስጥ ያሉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በመከታተል መለየት እንደተቻለም ታውቋል።

ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ በበሽታው ተይዘው አውስትራሊያ ወደሚገኝ ሆስፒታል የመጡ የ47 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሴት በ14 ቀናት ውስጥ ከቫይረሱ መዳናቸው ተገልጿል።

የጥናት ቡድኑም የእኚህን ሴት "አጠቃላይ በሽታን የመከላከል አቅም" መፈተሹን ፕሮፌሰር ካትሪን ኬደዜርስካ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታማሚዋ በጤናቸው ላይ መሻሻል ከመታየቱ ሦስት ቀናት ቀደም ብሎ በደማቸው ውስጥ የተለየ ህዋስ እንደታየ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል። ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ህዋስ በኢንፍሉዌንዛ በተያዙ ሰዎች ላይ ከበሽታው ከመዳናቸው ቀደም ብሎ መታየቱን ፕሮፌሰሯ ጠቅሰዋል።

የአውስትራሊያ ጤና ሚኒስትር ግሬግ ሃንት ስለአዲሱ ግኝት እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙን ለመከላከልና በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ለማከም የሚያስችል መፍትሔን በቶሎ ለማግኘት ይረዳል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

ኮሮና