በኬንያ ስለኮሮናቫይረስ ሃሰተኛ መረጃ ያሰራጨው ግለሰብ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, DCI KENYA
የኬንያ ፖሊስ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በትዊተር ሃሰተኛ መረጃ አሰራጭቷል ያለውን የ23 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ስር አዋለ።
ወጣቱ ኤላሻ ሙቱይ ኪቶኒዮ በምስራቅ ኬንያ ምዌንጊ ከተማ በቁጥጥር ስር የዋለው በአገሪቱ የተመዘገበውን የመጀመሪያ የኮሮናቫይረስ ኬዝ በተመለከተ መንግሥት የተዛባ መረጃ ሰጥቷል ሲል ባሰራጨው መረጃ እንደሆነ ተገልጿል።
ሃሰተኛ ነው በተባለው የትዊተር አድራሻ የተላለፈው ሃሰተኛ መረጃ ቅዳሜና እሁድ በስፋት ሲዘዋወር የነበረ ሲሆን የመጀመሪያዋ የኮሮናቫይረስ ተያዥ መንግሥት እንዳለው በለንደን በኩል ከአሜሪካ ሳይሆን ከጣልያን ሮም የመጣች ነች የሚል ነበር።
የግለሰቡን መታሰር የኬንያ የወንጀል ምርመራ በትዊተር ገፁ አረጋግጧል።
ወጣቱ ህብረተሰቡን ድንጋጤ ውስጥ ሊከት የሚችል ሃሰተኛ መረጃ በማተም ክስ እንደሚመሰረትበት የተገለፀ ሲሆን ጥፋተኛ ከተባለ በ50 ሺህ ዶላር ወይም እስከ አስር ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጣ ይችላል።
ትናንት እሁድ ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ኬንያዊያን ስለ ኮሮናቫይረስ ሃሰተኛ መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ አስጠንቅቀዋል።












