የዓለም ጤና ድረጅት ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊሆን እንደሚችል አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የአለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በቻይና የተቀሰቀሰው ኮሮናቫይረስ ወሳኝ ምእራፍ ላይ እንደደረሰና ወረርሽኝ የመሆን አቅም እንዳለው ገለፁ።
በአሁኑ ወቅት ጣልያንና ኢራን የቫይረሱ ስርጭት አዲስ ማእከሎች መሆናቸው እየተነገረ ነው።
የኢራን ከፍተኛ ባለስልጣናት በቫይረሱ ተይዘዋል።
ዶ/ር ቴዎድሮስም አሁን ትልቅ ስጋት የሆነው በቻይና ያለው ሁኔታ ሳይሆን ቫይረሱ በተቀሰቀሰባቸው ሌሎች አገሮች ያለው ሁኔታ ነው ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በ50 አገሮች 80 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፤ 2ሺህ 800 የሚሆኑ ደግሞ ሞተዋል። ብዙዎቹ ሞቶች የተመዘገቡት ቫይረሱ በተቀሰቀሰባት የቻይናዋ ሁቤ ግዛት ነው።
ዶ/ር ቴዎድሮስ መንግሥታት የቫይረሱን ስርጭት በአፋጣኝ መግታት ይቻል ዘንድ ከፍተኛ ስራ እንዲሰሩ አሳስበዋል።
"በጣም ስሱ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ለሁኔታው ምላሽ እንደምንሰጥበት መንገድ የቫይረሱ ስርጭት ባልታሰበ አቅጣጫ ሊሄድ ይችላል" በማለት የሁኔታውን አስቸጋሪነት አመልክተዋል።
ቢሆንም ግን ጊዜው ዓለም በፍርሃት የሚሸበብበት ሳይሆን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ወሳኝ እርምጃ የሚወስድበት መሆን እንደሚገባውም ገልፀዋል።
አገራት ምን አይነት እርምጃ እየወሰዱ ነው?
ጃፓን እና ኢራቅ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በማሰብ ትምህርት ቤቶችን ዘግተዋል። ይህ በቻይና የተለያዩ አካባቢዎችም ተተግብሯል።
ሳውዲ አረቢያ ለመንፈሳዊ ጉዞ ማንም አይምጣ ስትል እገዳ የጣለች ሲሆን እገዳው ቀጣዩን የሃጅ ጉዞ ይመልከት አይመልከት አልታወቀም።
ኢራን ዜጎቿ የሚያደርጓቸውን አላስፈላጊ የአገር ውስጥ ጉዞዎች እንዲሰርዙ ያሳሰበች ሲሆን በመዲናዋ ቴህራን እና በሌሎች ከተሞች የአርብ ፀሎትን ሰርዛለች።
አውስትራሊያ ከቻይና የሚነሱ ተጓዦች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ አግዳለች።
በቫይረሱ 17 ሰው የሞተባት ጣልያን 11 ከተሞችን ዘግታለች።
ግሪክ ፌስቲቫሎችን በሙሉ ሰርዛለች።
















