የዓለም የጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስን የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት መሆኑን አወጀ

የፎቶው ባለመብት, evn
የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ የወቅቱ አሳሳቢ የምድራችን የጤና ስጋት ነው ሲል አውጇል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክትር ዶክትር ቴድሮስ አድሃኖም ይፋ እንዳደረጉት ለዚህ ውሳኔ ዋነኛው ምክንያት "በቻይና የተከሰተው ነገር ሳይሆን በሌሎች አገሮች እየሆነ ያለው ነው" ብለዋል።
የዓለም የጤና ድርጅት የበሽታ ወረርሽኝ ተከስቶ ከዚህ አይነት ውሳኔ ላይ ሲደርስ ይህ ስድስተኛው ሲሆን ከዚህ ቀደም ኤችዋን ኤን ዋን የተባለው ኢንፍሉዌንዛ፣ ኢቦላ፣ ፖሊዮ፣ ዚካና በድጋሚ የተከሰተው ኢቦላ ምክንያት ነበሩ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ተጠርጥረው የደም ናሙናቸው ለተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ ወደ ደቡብ አፍሪካ ተልኮ የነበሩት አራቱ ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ጉዳዩ ያሳስበኛል ያለው በተለይ ቫይረሱ ዝቅተኛ የጤና ሽፋን ባለቸው አገራት ቢከሰት ጉዳቱ ከባድ ይሆናል በማለት መሆኑን ገልጿል።

አሜሪካ ዜጎቿ ወደ ቻይና እንዳይሄዱ አስጠንቅቃለች።
አሁን ባለው ሁኔታ ቻይና ውስጥ በበሽታው ቢያንስ 213 ሰዎች ሲሞቱ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል። የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከሆነ እስካሁን የሞተ ባይኖርም በሌሎች 18 አገራትም 98 የቫይረሱ ተጠቂዎች ተለይተዋል።
አብዛኞቹ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቫይረሱ በተከሰተባት የቻይናዋ ዉሃን ከተማ የነበሩ ናቸው። ቢሆንም ግን በሰው ለሰው ንክኪ ምክንያት የተያዙ 8 ሰዎች በጀርመን፣ ጃፓንና ቬትናም መኖራቸው መረጋገጡን ድርጅቱ አስታውቋል።
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ቴድሮስ አድሃኖም "ታይቶ የማይታወቅ ወረርሽኝ" በማለት የገለጹት ይህን ቫይረስ "የተለየ ፈጣን ምላሽ ያስፈልገዋል" ብለዋል።
የሌሎች አገራት ዝግጅት ምን ይመስላል?
መቋቋም በማይችሉት አገራት ውስጥ ቫይረሱ ቢከሰት ምን ሊሆን ይችላል?
ብዙዎቹ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በሽታውን የመለያ መሳሪያ ያጥራቸዋል። ይህ በመሆኑም በሽታው በማይታወቅ ሁኔታ ወደ እነዚህ አገራት ገብቶ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ይህ በሽታ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለዚያውም ከፍተኛ ጥረት በምታደርገው ቻይና ውስጥ 10 ሺህ የሚጠጉ ግለሰቦችን አጥቅቷል። ይህ ቀላል ቁጥር እንዳልሆነ እየተነገረ ነው።
በ2014 በምዕራብ አፍሪካ የተከሰተው የኢቦላ ቫይረስ በታሪክ አስከፊው ወረርሽኝ ነበር። ይህ የሆነው ደግሞ ድሃ አገራት ለጉዳዩ የሚሰጡት ምላሽ ካላቸው አቅም ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ለእንደዚህ ዓይነት ችግር ድሃ አገራት በእጅጉ ተጋላጭ መሆናቸውን ያሳያል።
አስቸጋሪው ኮሮናቫይረስም እንደዚህ አይነት አገራት ውስጥ ከተከሰተ ውጤቱ አስከፊ ሊሆን እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።
አሁን ሌሎች አገራት ቻይና ባለችበት ደረጃ አይደሉም። 99 በመቶ የሚሆነው የቫይረሱ ስርጭትና ተጠቂዎች ያሉት ቻይና ውስጥ ነው። ስለዚህ "ሌሎች አገራት ቻይና ወደገባችበት ችግር ውስጥ እንዳይገቡ ርብርብ ማድረግ ያለባቸው ቫይረሱ እዚያው ቻይና ውስጥ እንዲከስም በማድረግ ነው" በማለት የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
በተመሳሳይ የዓለም ጤና ድርጅት ቫይረሱን በአሳሰቢ ደረጃ መፈረጁ ድሃ አገራት የቁጥጥር ስራቸውን እንዲያጠናክሩና ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ለማስቻል ነው ተብሏል።
ለመሆኑ ይህ አዋጅ ያልተለመደ ነውን?
የዓለም ጤና ድርጅት እንደዚህ ዓይነት አዋጅ የሚያውጀው "በጣም የተለየ ነገር ሲከሰትና በዓለም አቀፋዊ ስርጭት መጠን ለሌሎች አገራትም ከፍተኛ ስጋት ሲደቅን ነው።"
ከአሁን በፊት አምስት አስቸኳይ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት አዋጅ በዓለም የጤና ድርጅት ታውጇል።
- በ2009 የተከሰተውና 2 መቶ ሺህ ሰው በገደለው ኤችዋን ኤንዋን
- በ2014 በፖሊዮ ምክንያት
- በ2016 ዚካ ቫይረስ በተለይ በአሜሪካ በስፋት መሰራጨቱን ተከትሎ እና
- በ2014 እና በ2019 በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተው ኢቦላ ቫይረስ ምክንያት ሲሆን ይህም ቫይረስ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ገድሏል።
ቻይና ወረርሽኙን እንዴት እየተቆጣጠረችው ነው?
ቫይረሱ 'ቲቤት' ውስጥ ተገኘ ማለት በቻይና ሁሉም አካባቢዎች ተዳርሷል ማለት ነው። የአገሪቱ የጤና ሚንስቴር እንዳስታወቀው እስካሁን 9 ሺህ 6 መቶ 92 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።
ማዕከላዊዋ ግዛት ሁቤይ በሁሉም በኩል በሮቿ እንድትዘጋ የተደረገ ሲሆን ቫይረሱ ከዚችው ግዛት የተከሰተ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ሟቾች የሁቤይ ነዋሪዎች ናቸው።
60 ሚሊዮን ዜጎች በግዛቷ ይኖራሉ።
በዚያች ግዛት የሚኖሩ ሰዎችም መሻሻል እሰኪኖር ድረስ ቤታቸው ውስጥ ሆነው እንዲያሳልፉ ተነግሯቸው፤ ቤታቸውን ቆላልፈው ተቀምጠዋል።
ወደ አገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎች በመሰረዛቸውና ከቻይና የሚመጡ ተጓዦች ላይም እገዳዎች እየተጣለ በመሆኑ የዓለማችን ሁለተኛዋ ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ባለቤት ቻይና ላይ ቫይረሱ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል።
የዓለም ምላሽ ምን ይመስላል?
የውጭ አገር ዜጎችን በፈቃደኝነት ላይ ከዉሃን ከተማ የማውጣቱ ሂደት እንደቀጠለ ነው።
እንግሊዝ፣ አውስትራሊያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖርና ኒውዚላንድ ቢያንስ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ዜጎች ለ2 ሳምንታት ያህል በጊዜያዊ ማቆያ ውስጥ እንዲሆኑና ሙሉ በሙሉ ነጻ እስኪሆኑ በመጠበቅ ስርጭቱን እየተከላከሉ ነው።
አውስትራሊያ የተጠረጠሩ ዜጎቿን ከዋናው የአገሪቱ ክፍል ወደ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር አርቃ በክሪስማስ ደሴት ለማቆየት ወስናለች።
ሌሎች አገራትም ከምርመራ ጋር በተያያዘ የመጨረሻ ውጤት ያልተገኘላቸውን ዜጎቻቸውን ለብቻ እየለዩ ነው።
- ኢጣሊያ ሁለት የቻይና ቱሪስቶች በሮም የቫይረሱ ምርመራ እየተደረገላቸው በመሆኑ ወደ ቻይና የሚደረጉ በረራዎቿን ሰርዛለች። ከ6 ሺህ በላይ የመርከብ ተጓዦችም ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ጊዜያዊ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር።
- በአሜሪካ 200 አካባቢ አሜሪካዊያን ከዉሃን ከተማ መመለሳቸውን ተከትሎ በቺካጎ ውስጥ አንድ ከሰው ወደ ሰው የተላለፈበት የቫይረሱ ተጠቂ መገኘቱን ተከትሎ እነዚሁ ሰዎች ቢያንስ ለ72 ሰዓታት ለብቻቸው እንዲቆዩ ተደርጓል።
- ሩሲያ ከቻይና ጋር የሚያዋስናትን 4 ሺህ 3 መቶ ኪሎ ሜትር ድንበር ለመዝጋት ወስናለች።
- ሁለት በረራዎች ከቻይና ወደ ጃፓን ቶክዮ ተደርገዋል። በተደረገው ምርመራ ሦስት የቫይረሱ ተጠቂዎች ጃፓን ውስጥ ተገኝተዋል።
- 250 የፈረንሳይ ዜጎች የሚገኙበትን የአውሮፓ ኅብረት ዜጎች ቡድን በሁለት በረራ ከቻይና ወደ አውሮፓ ለመመለስ ዝግጅት እየተደረገ ነው።
- ህንድ ዉሃን ውስጥ ሲማር የነበረ አንድ ተማሪዋ ወደ አገሩ ሲመለስ በቫይረሱ የተጠቃ መሆኑን አረጋግጣለች።














