ኮሮናቫይረስ በመላዋ ቻይና መዛመቱ ተነገረ፤ የሟቾችም ቁጥር እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቻይና አንድ ግዛት ውስጥ የተቀሰቀሰው የኮሮናቫይረስ መላዋን ቻይናን ማዳረሱንና በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርም 170 መድረሱ ተነገረ።
የቻይና የጤና ባለስልጣናት እንዳስታወቁት እስከ ትላንት ድረስ በአገሪቱ ውስጥ 7711 በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች አሉ።
በሽታው ከቻይና ባሻገር በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ቢያንስ 16 አገራት ውስጥ መዛመቱም ተገልጿል።
የዓለም የጤና ድርጅትም ዛሬ ተሰብስቦ በወረርሽኙ ላይ እንደሚመክርና በሽታው ያለበት ደረጃ ዓለም አቀፍ የጤና ስጋት መሆን አለሚሆኑን ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ትናንት እንደተናገሩት "ባለፉት አምስት ቀናት ውስጥ በተለይም በአንዳንድ አገራት ውስጥ በዋናነት ከሰው ወደ ሰው የታየው የበሽታው ስርጭት አሳስቦናል" ብለዋል በተለይም ጀርመንን፣ ቬትናምንና ጃፓንን ከዚህ አንጻር ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረውም "ከቻይና ውጪ ያለው የበሽታው ስርጭት በአንጻራዊነት ትንሽ ቢሆንም፤ ከፍተኛ ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችል ዕድል አለ" ብለዋል።
ምንም እንኳን እስካሁን በሽታውን የሚፈውስ መድሃኒትም ሆነ የሚከላከል ክትባት የለም።
ኮሮና ቫይረስ የከፋ የመተንፈሻ አካላት ህመምን በማስከተል እስከ ሞት የሚያደርስ ሲሆን በተለይም በሽታው ቀደም ሲል ህመም በነበረባቸው በዕድሜ የገፉ ሰዎች ላይ እንደሚጸና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
እስካሁን ድረስ ቻይና ውስጥ በበሽታው መያዛቸውና መሞታቸው የተረጋገጠው አብዛኞቹ ሰዎች ሁቤይ የምትባለው ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው ወረርሽኙ በተቀሰቀሰባት የዉሃን ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
በአሁኑ ጊዜ በከተማዋ ያሉ ሰዎች እንዳይወጡ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ ሲሆን ቻይና የበሽታውን መስፋፋት ለመግታት በግዛቶቿ ውስጥም በርካታ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን ጥላለች።
በሁቤይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት ምንም ስጋት እንደሌለው እኪረጋገጥ ድረስ የዕት ከዕለት ሥራቸውን ከቤታቸው ሆነው እንዲያከናውኑ በአሰሪዎቻቸው ተነግሯቸዋል።













