ሞሮኮ እንደ ፍልውሃ ያሉ የጋራ መታጠቢያ አገልግሎቶችን አገደች

ሞሮኮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሞሮኮ ሃማምስ የተሰኙትን እንደ ፍል ውሃ ያሉ የህዝብ ገላ እጥበት አገልግሎቶችን የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሲባል አገደች።

የህዝብ መታጠቢያ ቦታዎቹን እገዳ ይፋ ያደረገው የሞሮኮ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር ነው።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ተጨማሪ እገዳዎችንም የጣለ ሲሆን ካፍቴሪያዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሲኒማዎችና መስጂዶችም ጭምር ዝግ እንዲሆኑ ወስኗል።

አስፈላጊ የሚባሉ ቁሳቁሶች የሚገኙባቸው ገበያዎች ወይም የሚሸጡ ሱቆች እንዲሁም ወደ ቤት የሚወሰድ ምግብ የሚያቀርቡ ሬስቶራንቶች ግን ከእገዳው ውጭ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

እስካሁን በሞሮኮ 29 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው ተረጋግጧል።

ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን እያገኙ መሆናቸውን ተከትሎ የጉዞን ጨምሮ የተለያየ እገዳ እየጣሉ ነው።

ቀደም ሲል ኬንያ ከየትኛውም ኮሮናቫይረስ ከተገኘበት አገር ወደ ኬንያ የሚደረግን ጉዞ ማገዷ ሲሰማ የኬንያን ፈለግ በመከተል ደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ እገዳ ጥላለች።

የደቡብ አፍሪካ እገዳ ቻይና፣ ኢራን፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ እንግሊዝና አሜሪካን ይጨምራል።

ጋናም የኮሮናቫይረስ ከፍተኛ ስርጭት ካለባቸው አገራት ተጓዦች እንዳይመጡብኝ ብላለች። የኮሮናቫይረስ ኬዝ ያልተመዘገበባቸው ጅቡቲና ታንዛኒያም ጭምር ዓለም አቀፍ በረራዎችን አግደዋል።

በኮሮናቫይረስ የተያዙ 28 ሰዎች የተገኙባት እንዲሁም ሞት የተመዘገበባት ሞሮኮም ዓለም አቀፍ በረራዎችን አግዳለች።

አልጄሪያ ከነገ ጀምሮ ወደ ፈረንሳይ የሚደረግን በረራ እንደምታቆም ስታስታውቅ ሞዛምቢክ ባለስልጣናቷ ወደ ውጭ አገር ጉዞ እንዳያደርጉ ከልክላለች።

በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ በ26 የአፍሪካ አገራት እንደተገኘ ተረጋግጧል።